Sunday, December 21, 2014

ጋዜጠኞችን በማሠር ኢትዮጵያ አሁንም ከአፍሪካ 2ኛ ሆናለች

መራው አበበ
አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ 2014 አመት በመላው ዓለም 220 ጋዜጠኞች መታሠራቸውንና ቻይና በቀዳሚነት የጋዜጠኞች ሲኦል መሆኗን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ ያመለከተ ሲሆን ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሠር በአለም 4ኛ፣ በአፍሪካ ኤርትራን አስቀድማ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
eskinderandreeyotcropped
በኢትዮጵያ በ2014 እ.ኤ.አ የታሣሪ ጋዜጠኞች ቁጥር ከአምናው ከሰባት እጥፍ በላይ ጨምሮ ወደ 17 ከፍ ማለቱን የድርጅቱ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ ጦማሪያን ጭምር መታሰራቸውንና ከወትሮው በተለየ በርካታ ጋዜጠኞች መሠደዳቸውንም አመልክቷል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞችን በማሰር ተወዳዳሪ ያልተገኘላት ቻይና፤ 44 ጋዜጠኞችን ዘብጥያ እንዳወረደች በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ አምና በሀገሪቱ ታስረው ከነበሩት 32 ጋዜጠኞች ሌላ ዘንድሮ 12 ተጨማሪ ጋዜጠኞች መታሠራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ቻይና ለጋዜጠኞች ሲኦል መሆኗን አጠናክራ ቀጥላለች ብሏል፡፡ ሁሉም ጋዜጠኞች የመንግስትን ፖሊሲና አሰራር በመንቀፋቸውና አበክረው በመተቸታቸው ለእስር እንደተዳረጉም ተጠቁሟል፡፡ ኢራን ደግሞ ከቻይና ለጥቃ በሁለተኛነት ተቀምጣለች፡፡
የታሣሪ ጋዜጠኞች ቁጥር ከዓምናው በአምስት ያህል ቢቀንስም አሁንም ከዓለም ለጋዜጠኞች የማትመች ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች ብሏል – ሪፖርቱ፡፡ አምና በኢራን 35 ጋዜጠኞች ታስረው የነበረ ሲሆን ዘንድሮ አምስቱ ተለቀው 30ዎቹ በእስር ላይ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች የታሰሩበት ምክንያት እንደማይታወቅ ተገልጿል፡፡
በአለም ላይ ጋዜጠኞችን በማሠር የሚስተካከላቸው አልተገኘም ተብለው ከተለዩት 10 ሀገራት መካከል ኤርትራና ኢትዮጵያ በ3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን እነሱን በመከተል ቬትናም፣ ሶሪያ፣ ግብፅ፣ በርማ፣ አዘርባጃንና ቱርክ ተጠቅሰዋል፡፡ በኤርትራ ስለታሰሩት 23 ጋዜጠኞች ጥናት ለማድረግ መሞከሩን የጠቆመው ሲፒጄ፤ ለበርካታ አመታት የታሠሩ ጥቂት ጋዜጠኞች በህይወት መኖራቸውን ከማረጋገጡ ውጪ በምን ምክንያት እስከዛሬ እንደታሠሩ ለማወቅ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ ከቀደመው አመት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ ጋዜጠኞችን እንዳሰሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ግብፅ የአልጀዚራ ጋዜጠኞችን ጨምሮ 12 ጋዜጠኞች ማሠሯን ጠቅሶ የታሠሩበት ምክንያት ግን አልታወቀም ብሏል፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰር በ8ኛ ደረጃ የተቀመጠችው በርማ፤ “መንግስትን ተቃውማችኋል” በሚል 10 ጋዜጠኞችን ያሰረች ሲሆን፤ አብዛኞቹም የ10 አመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
በአዘርባጃን 9 ጋዜጠኞች ወህኒ ቤት የሚገኙ ሲሆን ዘንድሮ ብቻ አራት የማህበራዊ ሚዲያ “የመብት ተሟጋቾች” በሀገሪቱ ያለውን ሙስናና የሠብአዊ መብት ጥሰት በመተቸታቸው ከያሉበት ተለቃቅመው ለእስር መዳረጋቸው ተጠቁሟል፡፡ ከሁለት አመት በፊት ጋዜጠኞችን በማሠር በ1ኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ቱርክ፤ ዘንድሮ በርካታ ጋዜጠኞችን ከእስር በመልቀቅ ደረጃዋን አሻሽላ፣ 10ኛ ሆናለች፡፡ በአሁን ሰአት በቱርክ 7 ጋዜጠኞች ታስረው እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በአህጉር ደረጃ ለጋዜጠኞች ተስማሚ ሆናለች ተብላ የተጠቀሰችው አሜሪካ ነች፡፡ የኩባና የሜክሲኮ መንግስታት እያንዳንዳቸው አንድ ጋዜጠኛ ከማሠራቸው ውጪ አህጉሪቱ ሠላማዊ ነች ብሏል – ሪፖርቱ፡፡
የCPJ ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ከ2012 ወዲህ በመላው ዓለም 220 ጋዜጠኞች የታሰሩ ሲሆን፤ 132ቱ መንግስትን ተቃውማችኋል ወይም ሽብርተኛ ናችሁ በሚል ለእስር ሲዳረጉ፣ 45ቱ የታሠሩበት ምክንያት አይታወቅም ተብሏል፡፡ ከታሣሪዎቹ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች እንደሆኑ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ቁጥራቸው 83 እንደሚደርስም ጠቅሷል፡፡ የተቀሩት ተቀጣሪ ያልሆኑ እንዲሁም የሬዲዮ፣ ዌብሣይት፣ ቴሌቪዥንና ማህበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኞች እንደሆኑ ገልጿል፡፡
የታሳሪ ጋዜጠኞችን ቁጥር በየዓመቱ እያበራከቱ ነው ተብለው ከተጠቀሱት ሃገራት መካከል ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ባንግላዲሽ፣ ታይላንድ፣ አዘርባጃን፣ ባህሬን፣ ግብፅ፣ እስራኤልና ሳውዲ አረቢያ እንደየቅደም ተከተላቸው ከ1ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን ዘንድሮ አንድም ተጨማሪ ጋዜጠኛ ባለማሰራቸው ከተጠቀሱት መካከል ካሜሩን፣ ስዊዘርላንድ፣ ሜክሲኮ፣ ኩባ፣ በርማና ቤላሩስ ይገኙበታል፡ ፡ ሲፒጄ እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2014 “በአለማቀፍ ደረጃ የጋዜጠኞች ሁኔታ ምን ይመስላል?” በሚል ባካሄደው ጥናት፤ 404 ጋዜጠኞች በደረሰባቸው ጫና የትውልድ ሃገራቸውን ጥለው ለመሰደድ እንደተገደዱ አረጋግጧል፡ ፡ በእነዚህ ዓመታት ጋዜጠኞች በብዛት ከተሰደዱባቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ4ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ 41 ጋዜጠኞች ሃገር ለቀው ወጥተዋል ተብሏል፡፡ 76 ጋዜጠኞችን ለስደት በመዳረግ ፊትአውራሪ የሆነችው ደግሞ ኢራን ናት፡፡ ሶርያ 44፣ ሶማሊያ 42 ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ በማድረግ በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኤርትራ 29፣ ኩባ 18፣ ፓኪስታን 15፣ ሲሪላንካ 14፣ ሩዋንዳ 11፣ ጋምቢያ 10 ጋዜጠኞች ከሃገር እንዲሰደዱ በማድረግ ከ5-10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘውታል፡፡ ስደተኛ ጋዜጠኞች የተቀበሉ ሃገራት ተብለው ከተለዩ 10 ሃገራት መካከልም ኢትዮጵያ የምትገኝ ሲሆን ዘጠኝ ስደተኞች በመቀበል ከዓለም በ9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ አሜሪካ፣ ኬንያ፣ ቱርክ፣ ፈረንሳይ፣ ኡጋንዳ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ሱዳን፣ እንግሊዝ ከ1-8ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ሊባኖስ 10ኛ ሆናለች፡፡ አፍሪካ ብዙ ጋዜጠኞች ከተሰደዱባቸው አህጉራት ቀዳሚዋ ስትሆን 165 ጋዜጠኞች በተጠቀሱት አመታት አገራቸ ውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ መካከለኛው ምስራቅና የእስያ አገራት ይከተላሉ ተብሏል፡፡ በጥናቱ እንደተጠቆመው፤ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጋዜጠኞች እስራትና ክስ ሽሽት ከሃገራቸው የወጡ ሲሆን የስደት አገር ከገቡ በኋላ 21 በመቶ ያህሉ ብቻ በሚወዱት የጋዜጠኝነት ስራ የመቀጠል እድል አጋጥሟቸዋል፡፡

temesgen desalegn
ከተሰደዱት ጋዜጠኞች ውስጥ ወደ ትውልድ ሃገራቸው መመለስ የሚፈልጉት 5 በመቶ ብቻ እንደሆኑም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያን ያላካተተው “ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን” ሪፖርት በአለማቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞች በሙያቸው የሚጋፈጧቸውን ጫናና ተግዳሮቶች እየመዘገበ በየዓመቱ ሪፖርት የሚያቀርበው “ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን” (Reporters without Borders) ዘንድሮ (በ2014) በአለም ዙሪያ 66 ጋዜጠኞች መገደላቸውንና 119 ታፍነው መወሰዳቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው ቡድኑ፤ ሶርያን “የጋዜጠኞችን ህይወት የበላች ሃገር” በማለት በቀዳሚነት አውግዟታል፡ ፡ በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት በምትታመሰው ሶርያ ዘንድሮ ብቻ 15 ጋዜጠኞች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
Source: Zehabesha

No comments: