Thursday, March 6, 2014

በአባይ ጉዳይ… ውጥረቱ ተባብሷል (የግብጽ እና ሱዳን ባለስልጣናት ሳይስማሙ ተለያዩ)

በአባይ ጉዳይ… ውጥረቱ ተባብሷል (የግብጽ እና ሱዳን ባለስልጣናት ሳይስማሙ ተለያዩ)

(EMF) በያዝነው ሳምንት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ከርቲ ከግብጹ አቻቸው ነቢል ፋህሚ ጋር በአባይ ጉዳይ ተነጋግረዋል:: በዚህ ስብሰባ ላይ የሱዳን እና የግብጽ ልኡካን ቡድን መግባባት ላይ አልደረሱም:: ይልቁንም ሱዳን ለኢትዮጵያ የምታግዝ መሆኑን በመግለጽ ግብጻውያን በሱዳኖቹ ባለስልጣናት ላይ ቅሬታቸውን ገልጸዋል::
የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ከርቲ ከግብጹ አቻቸው በተጨማሪ ከግብጹ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አድሊ መንሱር ጋር ከመነጋገር ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበረ ቢሆንም; ግብጻውያኑ ባለስልጣናት ገና ከመጀመሪያው ከሱዳኖቹ ጋር መስማማት ላይ መድረስ አልቻሉም:: አልፎ ተርፎም ግብጻውያኑ ሱዳኖቹ ላይ ወቀሳ አብዝተውባቸዋል:: “የቆየውን ወንድማማችነት ማቆየት አለብን” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል አባባል ነው ከግብጽ ባለስልጣናት ተደጋግሞ የሚሰማው::
ሱዳን በኢትዮጵያ ግድብ ጉዳይ ጠንካራ አቋም ያልያዘች መሆኑን ግብጻውያኑ በተደጋጋሚ ይናገራሉ:: በዚህም ምክንያት… የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ከርቲ ከግብጹ ፕሬዘዳንት ጋር ተይዞ የነበረውን ቀጠሮ ጭምር ሰርዘውታል:: ይህ ለሱዳኖች እንደስድብ የሚቆጠር ቢሆንም ወደ አገራቸው ከመመለስ ውጪ ሌላ አማራጭ አላገኙም::
በሌላ በኩል ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት ቀጥላለች:: በሰራዊት ግንባታም በኩል በተለይ ከአሜሪካ በ’ርዳታ የሚሰጣት F 16 የጦር አውሮፕላኖች በበቂ ሁኔታ እየተዘጋጁ መሆናቸውን የግብጽ አየር ሃይል ምንጮችን በመጥቀስ የካይሮ ጋዜጦች እየዘገቡ ናቸው:: በተለይም ኢትዮጵያ ከአንድ ወር በኋላ ግድቡን ለመጀመር የሲሚንቶ አርማታ መሙላት የምትጀምረው በሚቀጥለው April ወር ላይ መሆኑ ግብጽ ውስጥ ውጥረትን ፈጥሯል::
ባለፈው አመት የኢህአዴግ አስተዳደር ግንቦት 20 እስኪደርስ ጠብቆ የአባይ ወንዝን አቅጣጫ ቀይሮ እንዲሄድ በማድረግ የግድቡን ስራ መጀመሩ ይታወሳል:: ኢህአዴግ ግድቡን የኢትዮጵያ ህዝብ ከማድረግ ይልቅ የአንድ ፖለቲካ ድርጅት የስራ ውጤት በማድረግ የፖለቲካ ጥቅም እና ደጋፊ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት ብዙዎችን ቅር ሲያሰኝ የቆየ ነው::

No comments: