Saturday, March 15, 2014

የኢህአዴግ ማመልክቻ ድጋሚ ውድቅ መደረግ አለበት!

የኢህአዴግ ማመልክቻ ድጋሚ ውድቅ መደረግ አለበት!

በመጀመሪያ አፋኝ ሕጎች መሠረዝ አለባቸው!
eiti



የተፈጥሮ ሃብትን በትክክለኛ መንገድ ለሕዝብ ጥቅም መዋሉን በመከታተል ለአገራት እውቅና የሚሰጠው The Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) ለተሰኘ ዓለም ዓቀፋዊ ተቋም ኢህአዴግ በድጋሚ ያቀረበው የእውቅና ጥያቄ ማመልከቻ ውድቅ መደረግ እንዳለበት ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት (Human Rights Watch) ድርጅት አስታወቀ፡፡ ኢህአዴግ የእውቅና ማመልከቻ አስገብቶ ውድቅ ተደርጎበት የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ የታወጁት አፋኝ ሕጎች እስካልተወገዱ ድረስ ድጋሚ ማመልከቻው ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባው ጨምሮ ተነግሯል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከሳምንታት በፊት “ኢህአዴግ ራሱ ባወጣው አፋኝ ሕግ ታፈነ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና ጉዳዩን በስፋት ዘርዝሮ ነበር፡፡ “EITI የዛሬ 11ዓመት አካባቢ የተቋቋመ በተፈጥሮ ሃብት ዙሪያ ዕውቅና የሚሰጥ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ የተፈጥሮ ሃብት የህዝብ መሆኑን የሚያምን ሲሆን ማንኛውም የተፈጥሮ ሃብት – ማዕድን፣ ዘይት፣ ብረታብረትና ጋዝ – ከመሬት በሚወጣበት ጊዜ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚኖረውን ያህል ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለባቸው አገራት ድርጊቱ ለሙስና እና ግጭት በር እንደሚከፍት ይናገራል፡፡ በመሆኑንም ድርጅቱ (EITI) አገራት ለሚያቀርቡት የዕውቅና ጥያቄ ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ልማትና እድገት በሚል ሰበብ የሕዝብ ሃብት የሆነውን የተፈጥሮ ሃብት በማውጣት የህዝባቸውን መብት ለሚረግጡ አገራት የሚያቀርቡትን የዕውቅና ማመልከቻ ውድቅ ያደርጋል፡፡”
በወቅቱ ጎልጉል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው “ኢህአዴግ ያቀረበው የእውቅና ጥያቄ ውድቅ መደረጉ እውነት ነው። ምንጩ እንዳሉት ኢህአዴግ በውሳኔው በመበሳጨት ይግባኝ ለመጠየቅ በዝግጅት” ላይ መሆኑን ጠቁሞ ነበር፡፡
የEITI ዕውቅናን ለማግኘት ቋምጦ የነበረው ኢህአዴግ በድርጅቱ ውሳኔ ባለመደሰት ጥቂት ዓመታትን ቆጥሮ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በአቶ ሃይለማርያም በመመራት በድጋሚ የዕውቅና የማግኘት ዘመቻውን ማጠናከር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የማዕድን ሚ/ር መ/ቤትም የEITI ዕውቅና ማግኘቱ በጣም የሚያስፈልግ እንደሆነ በይፋ በመናገር ዘመቻውን አጧጡፎ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ለዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን አሠራር በዓለምአቀፉ ድርጅት ላይ ተግባራዊ በማድረግ ኢህአዴግ Ethiopia Revenue Transparency Initiative (ERTI) የሚባል “ተለጣፊ” ተቋም በመመሥረት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ለEITI በጻፈው ደብዳቤ ላይ መግለጹንጎልጉል ጨምሮ ዘግቦ ነበር፡፡
clare
ክሌር ሾርት
ዛሬ የወጣው የሰብዓዊ መብት ድርጅት መግለጫ ይህንኑ የኢህአዴግን ጥያቄ የሚያስረዳ ሲሆን በአፋኝ ህጎቹ ላይ አንዳችም ለውጥ ያላሳየው ኢህአዴግ ማመልከቻው ውድቅ መደረግ እንዳለበት መግለጫው በአጽዕኖት ይናገራል፡፡ ምክንያቱንም ሲጠቅስ “የኢትዮጵያ መንግሥት ሚዲያውን አፍኗል፤ (ሰብዓዊ መብት እንዲከበር) እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሁሉ አድቅቋል” በማለት ያስረዳል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ በፊት ባስገባው ማመልከቻ ላይ የEITI ቦርድ ውሳኔውን ሲያስተላልፍ “የመያዶች ሕግ የተሰኘው አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆን እስካልተደረገ” ማመልከቻው ሊታይ እንደማይገባው በዋንኛነት ማመልከቻው ውድቅ እንዲደረግ የተደረገበት ምክንያት እንደነበር የጠቀሰው የሰብዓዊ መብት ድርጅት መግለጫ EITI አሁንም ይህንኑ ውሳኔውን እንዲያከብር ጠይቋል፡፡
ማመልከቻው እንደገና እንዲታይና የቦርዱ የቀድሞ ውሳኔ እንዲቀለበስ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የቀድሞ የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ ትብብር ሚ/ር የሆኑት ክሌር ሾርት መሆናቸውን መግለጫው ያስረዳል፡፡ እኚህ ግለሰብ የአፍሪካ አምባገነኖችን በመደገፍ የሚታወቁ ሲሆን ይህ ከጥቅማቸው ጋር የተሳሰረው ግንኙነታቸው አሁንም ኢህአዴግን እንዲደግፉ እንዳደረጋቸው ይነገራል፡፡ እንዲሁም በሌሎች ኢህአዴግ ባቋቋማቸው ዓለምአቀፋዊነት ሽፋን በተላበሱ ድርጅቶች ውስጥ የአመራር አባል በመሆን ሚስ ሾርት እንደሚያገለግሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማ አባል በነበሩበት ወቅትም ያላወጡትን ወጪ አውጥቻለሁ በማለት በብዙ ሺዎች የሚገመት ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ መሆናቸው በወቅቱ ዴይሊ ቴሌግራፍ ባወጣው መረጃ አጋልጦ ነበር፡፡ የተወሰነውን ገንዘብ የመለሱ ቢሆንም ጋዜጣው በወቅቱ ያወጣው መረጃ ግለሰቧ የሕዝብን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው የተጠቀሙ “ሙሰኛ” መሆናቸውን ያስረዳል፡፡
ከእነዚህና ሌሎች መረጃዎች አኳያ ኢህአዴግ በየቦታው እየደለለ “ባስቀመጣቸው” በመጠቀም የፈለገውን ለማድረግ ሲሞክር ዝም ሊባል እንደማይገባው በዚሁ ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቀሳቀሰውን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን ጠቅሶ ጎልጉል መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ መሠረት ኢህአዴግ የEITI አባል መሆን ከፈለገ ያወጣቸውን አፋኝ ሕጎች በሙሉ መሠረዝ እንዳለበትና የመናገር መብትን፣ የፕሬስ ነጻነትን፣ የመሰብሰብ፣ ወዘተ መብቶችን በይፋ ማክበር እንዳለበት እና የEITI የአባልነት ቅድመ መስፈርቶችንም በሙሉ ማሟላት እንደሚገባው ጨምሮ ገልጾዋል፡፡
http://www.goolgule.com/

No comments: