Thursday, August 6, 2015

Level and Effect of Drought in Ethiopia

Level and Effect of Drought in Ethiopia

August 6, 2015
Amateur cameraman captured many dead animals in Afar Regional State of Ethiopia.
The video caption posted on facebook read “One more shocking video that recorded during my travel to Semera partially showing the level and effect of drought at “Endifo”, Somali special Kebele of Afar Regional State, Ethiopia”.
The Ethiopian government didn’t talk about the drought or acknowledged about it.

አቤላ!

(በዘላለም ክብረት)
የእስረኛ ፊት ብዙ ነው፡፡ ታሪኩም ብዙ ነው፡፡ ብሶቱም ብዙ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹ዎክ› የሚያደርግበትመንገድ እንኳን ብዙ ነው፡፡ የሆነ በፅሁፍ ለመግለፅ የሚያስቸግር ከአራት እስከ ስድስት የሚሆኑ ርምጃዎችን ተጉዞ መመለስ ከዛ እንደገናመመለስ … ከዛ እንደገና መመለስ …በጣም በተደጋጋሚ … የሚደረገው ‹ደረስ - መለስ› የዎክ አይነት ግን የእስር ቤት መገለጫ ነው፡፡አብዛኛው እስረኛ ወደ ሰፊው ‹ማረፊያ ቤት› ከመምጣቱ በፊት በፖሊስ ጣቢያዎች ስለሚቆይና ጣቢያዎች ደግሞ ጠባብ በመሆናቸው ምክንያትወይም በራቸው ተዘግቶ ስለሚውል እዛው እዛው ‹ደረስ - መለስ› ዎክማድረግ እዛ ጣቢያ የተለመደ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የዎክ አይነት በተለየ ደግሞ ማታ ቆጠራ ከመካሔዱና ‹በየበዓታችን› ከመስፈራችንበፊት ባሉት ደቂቃዎች በዛ ያለ ሰው አንድ ላይ ሁኖ ክብ ሰርቶ የሚርመሰመስበት ‹አዙሪት› የዎክ አይነት አለ - በኢትዮጵያ እስርቤት፡፡ በአብዛኛው እኔና አቤላ የዚህ አዙሪት አካሎች ነበርን፡፡

አንድ ቀን አዙሪቱ መሃል እየተጓዝን እያለ አቤላ ‹ፖሊስ ጣቢያ› በነበርንበት ወቅት መጀመሪያ የተደበደበበትንምክንያት ሲነግረኝ፤ ‹የሱማሌ ተራ ልጅ ነኝ› በማለቴ ምክንያት ‹አንተ ማነህ ብሔር የለኝም የምትል?› ተብየ ነበር መጀመሪያ የተደበደብኩት፡፡ዞላ ከ40 እና 50 ዓመታት በፊት ሰዎች ‹ብሔሬ እንትን ነው› በማለታቸው ይሰቃዩ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ‹ዜግነት እንጅ ብሔር የለኝም›ማለት የሚያስገርፍ ሀጢያት ሁኗል›› አለኝ፡፡ ተከዝን፡፡ አቅማችን ‹ሕምምም› ማለት ብቻ ነበርና ‹ሕምምም› ከማለት ውጭ አማራጭአልነበረንም፡፡ መሬት በፀሃይ ዙሪያ ትሽከረከራለች ማለትም ያስገርፋል፡፡ ፀሃይ በመሬት ዙሪያ ትሽከረከራለች ማለትም ያስገርፋል፡፡‹ሕምምም›፡፡ ከአቤላ ጋር ብዙ ትካዜዎችን አሳልፈናል፡፡
ሌላ አንድ ቀን ደግሞ እስር ቤት ካገናኝናቸው በጣም ብዙ ሰዎች አንዱ ወዳጃችን ‹ገ› እኔና አቤላወዳለንበት መጣና ‹ክሳችሁ ምንድን ነው› ብሎ ጠየቀን፡፡እኛም ‹ሽብርተኝነት› አልነው፡፡ እሱም ትንሽ ደንገጥ በማለት ‹እንዴ ኢትዮጵያዊያንአይደላችሁም እንዴ› አለን፡፡ ‹ኧረ ኢትዮጵያዊያን  ነን› አልነውእየሳቅን፡፡ ‹አይዋ! ብረት (መሳሪያ ማለቱ ነው) እና ፌፍ - ዎን (የቦምብ አይነት ነው) ተይዞባችኋል ማለት ነው?› አለን፡፡በፍፁም! እኛ (አቤላም እኔም) የታሰርነው ከቢሯችን ከስራ ላይ ተይዘን እንደሆነ ነገርነው - ለየዋኹ ‹ገ›፡፡ እሱም በጣም ተገርሞታዲያ ‹በሽብርተኝነት› እንዴት ተከሰሳችሁ› ሲለን ሳቃችን መቆጣጠር አልቻልንም ነበር፡፡ ሳቅን፡፡ ከአቤላ ጋር በእውነት ብዙ ሳቆችንተካፍለናል፡፡ በሳቅ ሆዳችን ታሟል፡፡

Frank MacCourtን አንብበን በሳቅ ጠሽ ብለናል፣ Robert Fiskን አንብበን ስለ ዓለምብዙ አውርተናል፣ Tariq Ramadanን አንበብን በለውጥ ሰባክዎች ቀንተናል…፡፡ ብቻ አብረን ያሳለፍናት እጅግ በጣም አጭር አንድዓመት የምታስቀና ነበረች፡፡

ብዙ ጠያቂዎቻችን ሊጠይቁን ይመጡና ጓደኝነት ማለት ‹ታቦት አብሮ ማንገስን› አልያም ‹ሶላት አብሮመስገድ› ይመስል ሃይማኖት እያነሱ ‹እንዴት ተመቻችታችሁ ትኖራላችሁ› አይነት ነገር ሲሉን ብዙ እንገረም ነበር፡፡ ጓደኝነት እኮበጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከአንድ የመሰሎች ጎራ ወደ ሌላው የሚያሸጋግር ድልድይ!

ሰዎች ያለፍንበት ከአንድ ዓመት የሚበልጥ አስቸጋሪ ጊዜ (እነ አቤል አሁን ያሉበት) ብዙ የሚያበሳጨንይመስላቸው ይሆናል፣ በፍጹም፡፡ አቤላ ፍ/ቤቱን ተዳፍረሃል ተብሎ ቅጣት በተወሰነበት ጊዜ እየሳቀ መጥቶ ‹3 ዳገት ተለመጥኩ›(በእስር ቤት ቋንቋ ‹3 ዓመት ተፈረደብኝ› እንደማለት ነው) ነበር ያለን፡፡ እኛም ቀልድ መሆኑን ተረድተን ወደ ብስጭትና ቁጭትአልገባንም፣ ይልቁን ስለ Freedom of speech in the court of law እያነሳን ተወያየን እንጂ፡፡ ምንም እንኳንታላቁ ዳኛ Justice Holmes “The court is not a market of ideas” ቢሉም ከእርሳቸው ተከትለው የመጡትዳኞች ደግሞ “A judge should show a higher moral character which refuse to be offendedin every statements”  እያልን ነበር የምንሳሳቀው፡፡ በጣምየሚገርም ዓመት እኮ ነው አብረን ያሳለፍነው፡፡

አቤላ ወዳንተ ስመጣ፣
ይህችን አጭር ሜሞ ባልተመቻቸ ሁኔታ መንገድ ላይ ሁኜ ነው የምፅፍልህና በማጠሯ አትዘንብኝ እሺ፡፡

እንዲህ ነው፣
እኔም አንተም በማናዉቀው ምክንያት እኔ ተፈትቼ አንተና ወንድሞቻችን አሁንም አበሳችሁን እያያችሁነው፡፡ ለዚህ ልቤ ይደማል፡፡ ምን ላድርግ? ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል የተባሉ ሊቅ ስለ ወዳጅነት ምን አሉ?

“ወዳጅ ‘ማ ማለት አብሮ ባካኝእንጂ፤
እንደ አይን፣ እንደ ዦሮ፣ እንደ’ግርእንደ’ጅ፡፡

አቤላ እኔ አሁን አይንም፣ ዦሮም፣ እጅም፣ እግርም ላልሆንህ ካንተ ርቄያለሁ፡፡ ያማል፡፡ ግን ቢያንስሃሳቤ ውስጥ ትመላለሳለህ፡፡
በመጨረሻ ልደትህን ከአምናው ለየት የሚያደርገው አምና መሬት ላይ “እየተደቦቅን” (እየተኛን) ነበርያከበርነው ዘንድሮ ግን አልጋ ላይ ሁነህ ማክበርህ ነው፡፡ GTP -2ን ያስታውሷል፡፡

መልካም ልደት አቤላ!

ወንድምህ ዘላለም

Source: Zone9

Wednesday, August 5, 2015

የሀይማኖት መብታችን የሚከበረው በነፃነት ትግል ነው!

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ለስልጣን ለሚያሰጋው ድርጅትና ተቋም ለራሱ ስልጣን የሚበጀውን ሌላ ድርጅትና ተቋም በመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ ልዩነት ከፋፍሎ ሲገዛ ቆይቷል፡፡ ለመምህራን ማህበር ለመምህራን ሳይሆን ለእሱ የሚመች ማህበር፣ ለፖለቲካ ድርጅቶች ለህዝብ የሚቆም ሳይሆን ለአገዛዙ መሳሪያ የሚሆን ድርጅት፣ ለሰብአዊ መብት ድርጅቶችም እንዲሁ ለኢትዮጵያውያን የሚቆሙ ሳይሆን ከእሱ ጋር የሚወግኑ ድርጅቶችን በማቋቋም እውነትና ከእውነተኞችን ሲታገል ኖሯል፡፡ ከዚህም አልፎ አሁን በሀይማኖት ውስጥ ለእሱ የሚመች ሌላ ሀይማኖት በመቋቋም ላይ ነው፡፡
የቆየው የአገዛዙ እኩይ ባህሪ ስልጣን ላይ ለመቆየት በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ በሀይማኖት ተቋማትም ጭምር ጣልቃ በመግባት እሱ የሚፈልገውን እምነት በመደገፍ፣ ሌላው ላይ ቅጣት በመጣል ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም አገዛዙ ባለፉት ሶስት አመታት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ እያደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት መመልከት በቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ኢህአዴግ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብ ንቅናቄ ማድረግ በጀመሩበት ወቅት ስርዓቱ ለመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው እውቅና ሰጥቶ ሲደራደር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁንና በሚፈልገው መንገድ አልሄድለት ሲል የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴ አባላትን አስሯል፡፡ ‹‹አሸባሪ›› ብሎ ከሷል፡፡ ሀምሌ 27/2007 ዓ.ም እውቅና ሰጥቶ ሲደራደራቸው የነበሩትን የሙስሊሙ ማህበረሰብ አመራሮች ከ7 እስከ 22 አመት እስራት ፈርዶባቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ‹‹ሽብር›› የሚባለው ክስ ስርዓቱ ያልፈለገውን የሚያስርበት መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ክስ ሰላማዊ ታጋዮችን ጥፋተኛ የሚለው ፍርድ ቤትና ህግም የአገዛዙ ዋነኛ መሳሪያ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ የፖለቲካ ሰነድ ከሆነው ህገ መንግስት ላይ በቅዳሚነት ከሚሰፍሩት መብቶች መካከል አንዱ የሆነው የሀይማኖት (የሰብአዊ መብት) ጥያቄ እንደሆነ ያምናል፡፡ ይህም በመሆኑ ስርዓቱ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህን እመን፣ ይህን አትመን በሚል እምነት ወደመወሰን ጣልቃ ገብነት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ትክክል እንዳልሆነ ለማስገንዘብ ጥሯል፡፡ ሆኖም ለሀገርና ለህዝብ ከሚጠቅመው ሀሳብ ይልቅ የስልጣኑ ጉዳይ ብቻ የሚያሳስበው ኢህአዴግ የሚሰማ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ኢህአዴግ ሰላማዊ ታጋዮችን በፈጠራ ሽብር ወንጀል ከሶ ሲያስር፣ ለፖለቲካ ድርጅቶችና ለተቋማት ለእሱ የሚመቹትን በመፍጠር አባዜው ሀገራችንን አደጋ ውስጥ እየጣላት ይገኛል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሌላ አደጋ ውስጥ እንድንገባ እያደረገም ነው፡፡
ከአሁን ቀደም ካሉት በርካታ ተሞክሮዎች ለመረዳት እንደሚቻለው አገዛዙ ምክርና ትችት አዳምጦ ማስተካከያ ከማድረግ ይልቅ በእልህና በማን አለብኝነት እያባባሰ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ አሁንም በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የፈፀመው በደል ተተችቶ የሚያስተካክለው ነው ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ ይልቁንም ሀገራችንን አደጋ ላይ ለመጣል በየ ጊዜው የፈፀማቸውና ወደፊትም ለመፈፀም ወደኋላ የማይላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ብቸኛው አማራጭ በጋራ መታገል ነው፡፡ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ስርዓቱ እንደመሆኑ ለየብቻችን የምናስመልሳቸው መብቶች አይኖሩም፡፡ የሰብአዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ልናስከብር የምንችለው ዋነኛው የችግሮቹ ምንጭ የሆነውን ስርዓት ታግለን ለኢትዮጵያችን የሚበጅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስንገነባ መሆኑን ተገንዝበን ሰላማዊ የነፃነት ትግሉን መቀላቀል ይኖርብናል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አገዛዙ እየፈፀመበት ያለውን በደል በመቃወም ሲያደርግ የቆየውን ሰላማዊ ትግል ያደንቃል፡፡ በኮሚቴው ላይ የተወሰደው እርምጃ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ይበልጡን ትግሉን አጠናክሮ፣ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ተባብሮ አምባገነንነትን ከምንጩ ከማድረቅ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ በመሆኑን ሰላማዊ ትግሉን በመቀላቀል በሰብአዊነታችን፣ በዜግነታችን ከዚህም አለፍ ሲል በሀገራችን ላይ እየፀመው ያለውን አደጋ በመገናዘብ፣ የፖለቲካ ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኑ! ራሳችን ነፃ በማውጣት የሀገራችንን እጣ ፋንታ እንወስን!
ሀምሌ 29/2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለ3ኛ ጊዜ አቶ አንዳርጋቸውን አላቀረበም

‹‹ቤተሰቦቼ አሸባሪ ተብለው ቤት የሚያከራያቸው አጥተዋል፤ ልጆቼ በረንዳ ላይ ወድቀዋል፤ ቤተሰባችን ተበትኗል››
ም/ኢንስፔክተር ሙልዬ ማናዬ ረታ (7ኛ ተከሳሽ)
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ (2ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) እና አቶ አንሙት የኔዋስ (5ኛ ተከሳሽ) ዋስ እንዲሆኑ ለዛሬ ሀምሌ 29/2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የደረሰው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡
ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት የፌደራል አቃቤ ህግ ‹‹ከአንዳርጋቸው ፅጌና ፋሲል የኔዓለም እንዲሁም ከሌሎቹ የአሸባሪው ድርጅት አመራሮች ጋር በአካልና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በመገናኘት ስለ ሽብር ተግባሩ አፈፃፀም በመግባባት፣ ኤርትራ ወደሚገኘው የግንቦት ሰባት ካምፕ ሄደው ስልጠና በመውሰድ፣ ተልዕኮ ተቀብሎ ወደ ሀገር ውስት በመመለስ፣ ....›› የሚል ክስ ስለመሰረተባቸው ነው፡፡
የልደታ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለሚገኙት ተከሳሾች ሀምሌ 13/2007 ዓ.ም ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ወስኖ የነበር ቢሆንም ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚላከው ማዘዢያ እንደዘገየ በመግለጽ ለሀምሌ 15/2007 ዓ.ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም አቶ አንዳርጋቸው ሀምሌ 15/2007 ዓ.ም ያልቀረቡ ሲሆን ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዙ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት መጻፍ ሲገባም ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተብሎ ስተለጻፈ ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጾ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ማዘዢያው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተብሎ እንዲፃፍ አዝዞ ለሶስተኛ ጊዜ ማረሚያ ቤቱ ለሀምሌ 29/2007 ዓ.ም አቶ አንዳርጋቸውን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና በዛሬው ዕለትም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ምስክር እንዲሆኑ ከወሰነ ጊዜ ጀምሮ ይቀርባሉ ተብለው ሳይቀርቡ ሲቀሩ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡
በዛሬው ዕለት የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ እንዲያብራራ፣ እንዲሁም በዛው ቀን ለምስክርነት እንዲያቀርብ ሲል ለጥቅምት 12/2008 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ በሌሎች መዝገቦች የሚሰሙ ምስክሮች ስላሉና ከነሀሴ 15/2007 ዓ.ም በኋላ ፍርድ ቤት ስለሚዘጋ በሚል አቤቱታቸውን አልተቀበለውም፡፡
በሌላ በኩል በማረሚያ ቤትና በፍርድ ቤቱ ችግር አቶ አንዳርጋቸውን ለምስክርነት ማቅረብ ባለመቻሉ እየተጉላሉ መሆናቸውን ተከሳሾቹ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ ም/ኢንስፔክተር ሙልዬ ማናዬ ‹‹የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በመባሉ በሚል ተልካሻ ምክንያት ለምን እንጉላላለን? እኛ ፍትህ ፈላጊ ነን፡፡ ቃሊቲና ቂሊንጦ በአንድ ደቂቃ የስልክ ግንኙነት መገናኘት እየቻሉ በቀጠሮ እየተጉላላን ነው›› ብለዋል፡፡
ተከሳሹ አክለውም ‹‹እኔ የመከላከያ ምስክሬን ያቀረብኩት የዛሬ አመት ነው፡፡ ለእኔ ብለው ቤተሰቦቼ በሬያቸውን ሸጠዋል፡፡ ግን አሁንም ድረስ እየተጉላላሁ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ አሸባሪዎች ናቸው ተብለው ቤት የሚያከራያቸው አጥተዋል፡፡ ልጆቼ በረንዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ ቤተሰባችን ተፈትቷል፡፡ ምስክሩን ማቅረብ ካልቻሉ ለምን ክሱን ውድቅ አታደርጉትም?›› ሲሉ የፍርድ ሂደቱ በመጓተቱ እየደረሰባቸው የሚገኘውን በደል ገልጸዋል፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ ‹‹የአማራ ክልል ወጣቶች ፕሬዝደንት ሆኖ ባለበት በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም በኬንያ አድርጎ ከሀገር ከወጣ በኋላ የአሸባሪውን የግንቦት 7 ልዩ ኃይል (Popular Force) ታጥቆ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ›› በሚል በሌለበት ክስ የመሰረተበት የዠመነ ካሴ ክስ መዝገብ 10 ተከሳሾቹ የተከሰሱ ሲሆን 10ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሙሉ ሲሳይ መቆያ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆና ግንቦት 19/2006 ዓ.ም በነፃ ተለቃለች፡፡

Tuesday, August 4, 2015

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ድርቅ መግባቱ ታወቀ




ሐምሌ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዘጋቢዎቻችን እንዳሉት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ ድርቅ ተከስቷል።በሰሜን ሸዋ፣በዋግ ህምራና በወሎ በርካታ ቦታዎች ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቅ ገብቷል፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጉዳዩን በዝግ ስብሰባዎች ቢወያዩበትም ፣ መረጃው ወደ አደባባይ እንዳይወጣ ጥረት እያደረጉ ነው። በዋግ ህምራ አካባቢ ለሶስተኛ ጊዜ እርሻ እየተገለበጠ በመታረስ ላይ መሆኑን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው ደግሞ በግንቦት ወር በሶስተኛዉ የወሩ ሳምንት በሰ/ሸዋ ዞን 8 ወረዳዎች ማለትም በባሶናወራና፣ አንፆኪያ፣ ሲያደብር ዋዩ፣ መርሃቤቴ፣ መንዝላሎ፣ ሃገረማርያም፣ ቀወትና አንኮበር፣ በደቡብ ወሎ ዞን 16 ወረዳዎች እና በደቡብ ጎንደር ዞን 6 ወረዳዎች ስርጭቱ ያልተስተካከለ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ዝናብ ያገኙ ቢሆንም ፣ ሌሎች 64 የክልሉ ወረዳዎች ዝናብ እንዳልነበራቸው ታውቆአል፡፡
በትግራይ ደግሞ ወሩ በገባ የመጀመሪያዉ ሳምንት ቆራሮና ኢሮብ ወረዳዎች ከ1-2 ቀናት ስርጭቱ ያልተስተካከለ አነስተኛ ዝናብ እንዲሁም በተምቤን፣ እንደመሆኒ፣ አህፈሮም ወረዳዎች ለውስን ቀናት ከባድ ዝናብ የነበራቸው መሆኑን ከክልሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለተኛዉ ሳምንት በኋላ በታህታይ ኣድያቦ ወረዳ በ10 ቀበሌዎች እንደመሆኒና ኦፍላ ወረዳዎች፣ በደቡብ ምስራቅ ዞን ሳምረ ወረዳ፣ በማእከላዊ ዞን አድዋና በማይጨው ወረዳዎች፣ በተምቤን ወረዳ፣ በሰሜን ምእራብና በምእራብ ዞኖች በቆራሮ፣ አስገደ ጽምብላ፣ ጸለምቲ፣ አዲያቦ፣ እንዲሁም በአወዛጋቢዎቹ ወልቃይትና ፀገዴ ወረዳዎች ከነበረዉ አነስተኛ ዝናብ በስተቀር በአመዛኙ በቀሪዎቹ ሳምንታት የነበረዉ ዝናብ አመርቂ አለመሆኑን መረጃው አመልክቷል።
በደቡብ ደግሞ በወሩ ዉስጥ በአብዛኛዉ የክልሉ አካባቢዎች ስርጭቱ የተስተካከለ ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ዝናብ የዘነበ ሲሆን ፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም አልፎ አልፎ ከበድ ያለ ዝናብ ጥሎአል። ይሁን እንጂ በጋሞ ጎፋ ዞን ዛላ፣ ከምባ፣ ምእራብ አባያ እና የጸሐይ ወረዳዎች፣ በስልጤ ዞን በአሎቾ ወሪሮ ወረዳ እና ሀዲያ ዞን በአመዛኙ ስርጭቱ ያልተስተካከለ ዝናብ ያገኙ እንደነበረ እና በነዚሁ ዞኖች አንዳንድ ቀበሌዎች ላይ ዝናብ እንዳልነበረ ከግብርና ሚኒስቴር መረጃ ማወቅ ተችሏል።
በአፋር በወሩ ዉስጥ በአመዛኙ ዝናብ ያልነበረ ሲሆን፣ በወሩ የመጀመሪያ ሳምንት ከግብርና ስራዎች አንፃር ጠቀሜታው በጣም አነስተኛ የሆነ ዝናብ ዘንቧል። በሱማሌ በአመዛኙ ዝናብ ያልነበረ ሲሆን በግንቦት ወር ሁለተኛ ሳምንት የጂጂጋ ወረዳ በከፊል አነስተኛ ዝናብ ሲያገኝ በወሩ ሶስተኛ ሳምንት ጂጂጋና ሽንሌ ዞኖች ስርጭቱ ከቦታ ቦታ የተለያየ መካከለኛ ዝናብ እንዳገኙ ታውቋል።
የክረምቱ ዝናብ ስርጭት አለመስተካከል ጋር ተያይዞ የምግብ እህል ተረጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተቀማጭነታቸው በአዲስአበባ የሆኑ ለጋሽ ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን ስጋት ውስጥ መውደቁ ታውቆአል፡፡
እስካሁን ድረስ የተፈናቀሉ ዜጎች ይኑሩ አይኑሩ የታወቀ ነገር የለም። የዝናብ ስርጭቱ በሚቂጥሉት ሳምንታት ካልተስተካከለ፣ በአገሪቱ በሰው እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
በትግራይ ህወሃት በቅርቡ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በማውጣት የህወሃትን 40ኛ አመት በአል ሲያከብር ፣ ኦህዴድም ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ አውጥቶ 25ኛ አመት በአሉን አክብሯል። ብአዴንም 35ኛ አመት በአሉን ለማክበር
ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። በሁሉም ክልሎች በድርቅና በኑሮ ውድነት ዜጎች እለታዊ ወጪያቸውን ለመሸፈን ተስኖአቸው በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ ከፍተኛ የአገር ሃብት ለክበረበአላት እየወጣ በመባከን ላይ መሆኑን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።
Source: Ethsat

ሰማያዊ አንድነት ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ

ጋዜጣዊ መግለጫ
ሰማያዊ ፓርቲ በአገራችን ካሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በዲሞክራሲ ወገንኝነቱ የሚታወቅና በጠመንጃ አፈሙዝ ሀገሪቱን ላለፉት 25 አመታት በመግዛት ላይ ያለውን አምባገነን ስርአት በሰላማዊ ትግል በማስወገድ በዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚመራ መንግስት ለመመስረት የሚታገል ፓርቲ ነው። የፓርቲው ዋና መመሪያ የሆነውና በሰላማዊ ትግል በመታገዝ የዲሞክራሲያዊ ስርአትን መመስረት የሚለው ይህው አላማው በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ኧንዲያገኝ አስችሎታል። መንግስት በአንድ ወቅት ጠንካራ የነበረውን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በህገወጥ መንገድ ኧንዲፈርስ ሲያደርግ አባላቱ የጀመሩትን ትግል ለመቀጠል ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸው ለዚህ አባባላችን በቂ ማስረጃና የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ይህንኑ ፈለግ በመከተልም በውጪ የሚገኙ የሰማያዊና የአንድነት ፓርቲዎች ድጋፍ ሰጪዎች ለሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የሚውል ፋይናንስ በጋራ የማሰባሰቡን ተግባር በአግባቡ ተወጥተዋል። ከዚህ ባለፈም ተዋህደው ኧንደ አንድ አካል የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በዚሁ መሰረት ባሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ኧና የአንድነት ዲሲ ሜትሮ ቻፕተር ተዋህደው የሰማያዊ አንድነት ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ በሚል ሰያሜ ስር መሆናቸውን ስናበስር ታላቅ ደስታ ይሰማናል።
የሰማያዊ አንድነት ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ ዋና አላማዎችም ሰማያዊ ፓርቲን በሁለንተናዊ መልኩ መደገፍ፤ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የትግሉ አካል በመሆን የበኩላቸውን ድርሻ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን ፎረም ማመቻቸት፤ የተለያዩ አርቲክሎችን ማዘጋጀት ኧንዲሁም በኢትዮጲያ ጉዳይ ዙሪያ ያሉ ወቅታዊ መረጃዎችን በማሰባሰብ በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ማሰራጨት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።
የህወሃት ኢህአዴግ አፈናና ጭቆና ኧየጨመር በሄደ መጠን ለነጻነት የሚደረገው ትግል በላቀ ሁናቴ ሊፋፋም ይገባዋል። ለዚህ ኧውን መሆን ደግሞ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል። በመሆኑም የሰማያዊ አንድነት ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ በሰላማዊ ትግል ዲሞክራሲን ኧውን ለማድረግ፤ የሰብአዊ መብቶች ኧንዲከበሩ፤ የነጻ ፕሬሱ ኧንዲያብብና መልካም አስተዳደር ኧንዲሰፍን ኧንዲሁም የነጻ ገበያ ስር አት ኧንዲያብብና ብሄራዊ አንድነታችን ኧንዲጸና ለሚታገሉ ተቃዋሚዎች ሁሉ መሳሪያ ሆኖ ኧንደሚያጋለግል ኧምነታችን የጸና ነው።
ሐምሌ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም

Semayawi Andnet (Semayawi) Support North America (SASNA)
Press Release
Semayawi (Blue) Party is one of the foremost pro-democracy political parties in Ethiopia that is conducting a non-violent struggle to establish a democratic system of government in a country that has been ruled with an iron fist by a totalitarian regime for the past 25 years. The party’s main principle of non-violent struggle to democratize Ethiopia enjoys broad public support. It is to be remembered that after the regime illegally banned the once strong Andenet Party, most of its members joined Semayawi Party in order to continue their struggle.
Following their footsteps and recognizing the need for unified support, Andenet and Semayawi Support Groups have been fundraising in support of Semayawi Party during its campaign for election. In addition to this collaboration, the groups have been working towards merger. Today, we gladly announce that Semayawi Support North America and Andenet DC Metro Support Chapter have finalized the process and completed the merger. The new unified support group will operate under the name Semayawi Andnet (Semayawi) Support North America (SASNA).
Semayawi Andnet (Semayawi) Support North America (SASNA) mission is to provide all rounded support to Semayawi Party; to provide a forum for Semayawi supporters and other like-minded individuals in North America to get involved in the struggle; to disseminate research articles and/or materials and information which have relevant bearings on Ethiopia, Semayawi supporters, and the Ethiopian Diaspora in North America.
As the repression level of the TPLF/EPRDF regime continues, the need for more intensified struggle for freedom becomes necessary; and for these efforts to succeed, the support of Ethiopians in the diaspora will continue to play a vital role. It is our belief that SASNA will serve as an instrument in supporting the effort of non-violent opposition political parties in promoting democracy, human rights, free press, good governance, free market, and national unity.

Saturday, August 1, 2015

የናትናኤል ማስታወሻ -ጥቂት ስለ ማዕከላዊ

ከቂሊንጦ እስር ቤት)
ናትናኤል ፈለቀናትናኤል ፈለቀ
ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ ዓላማዬ ማዕከላዊ ያሉ ሥራቸውን አክብረው የኢትዮጵያውያንን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የሚሰሩ ጥቂት ፖሊሶችን (ምናልባትም በአንድ እጅ ጣቶች ተቆጥረው የሚያልቁ መርማሪዎችን) ለማበረታታት አይደለም፡፡ይህን ዓላማ በሌላ ጽሁፍ እመለስበት ይሆናል፡፡ ለነገሩ ሥራቸውን አክብረው የሚሰሩ ባለሙያ ፖሊሶች የኔ ማበረታታትን የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ያሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በኃላፊነት ማሰብ የቻሉ ስለሆኑ፡፡
ስለዚህ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በተቋሙ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትተዳደርባቸውን ሕጎች ለማክበር(የተላለፉትን ለይቶ ለማስቀመጥና በስህተት የተጠረጠሩትን ነጻ ለማውጣት) ሳይሆን የአገዛዙን ዕድሜ ለማርዘም የሚሰሩትን አብዛኞቹን ሙያቸውን የማያከብሩ ፖሊሶች ‹‹ምርመራ›› ሴራቸውን እንዴት እንደሚፈትሉ ለማሳየት፣ ቢያንስ ሌላ ስልት እስኪፈጥሩ ድረስ በሀገሪቷጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን አንዴ በተቋሙ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሊገጥማቸው የሚችለውን የተንኮል መረብ ለማስረዳት እና ቀድሞለማዘጋጀት ያሰበ ነው፡፡
እውነት ለመናገር እነዚህ የስርዓቱ ጠባቂ ሎሌዎች የህዝብን ደህንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ወንጀልን እና ወንጀለኞችን ለይተው አውቀው ፍትህ እንዲያገኙ አድርገው ጭራሹንም አያውቁም ማለት አልችልም፡፡ ስለዚህ አሁን የማብራራው ጉዳይ ለወንጀለኞችም መዘጋጃ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ወንጀለኞች ከፍትህ እንዲያመልጡ ጠብታ ውሃ ማቀበል አልፈልግም፡፡አንድ ነጻ ሰው ባልሰራው ወንጀል ከሚቀጣ መቶ ወንጀለኞች ቢያመልጡ ይሻላል የሚለው የህግ መርህ የበለጠ አቋሜን ያስረዳል፡፡
ሁለት ማሳሰቢያዎች አሉኝ፤ አንደኛ፡-እኔ ተይዤ ማዕከላዊ እስክገባ ድረስ ልታሰር እንደምችልአስቀድሜ ባውቅም ሊጠብቀኝ የሚችለውን የ‹‹ምርመራ›› ሂደት (የሴራ መረብ የበለጠ ይገልጸዋል) አጽንዖት ሰጥቼ አላሰብኩበትም፡፡የምርመራው ሂደትን ተንተርሼ የማነሳቸውን ሀሳቦች የተረዳሁት በምርመራ ውስጥ ካለፍኩ በኋላ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ጽሁፍየሚያነቡ ሰዎች እኔ በፍርሃት ያላደረኳቸውን ነገሮች እንዲያደርጉ (በምርመራ ሂደት) የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ይህንን ጽሁፍ በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል እና ሀሳቡን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች በሚፈቅዱት መሰረት በነጻነት የሚገልጽ ሁሉ ጊዜ ሳይሰጥ ቢያነበው እመክራለሁ፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሀሳብ የአቃቤ ህግ ምስክር ከተሰማ በኋላ በብይን የተለቀቁ ሙስሊምወንድሞች መጻፋቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ያ ጽሁፍ የተሻለ የተደራጀ ነው ብየ ስለማስብ እንዲነበብ እጋብዛለሁ፡፡ በተጨማሪም ስርዓቱንየሚደግፉ ሰዎች ይህንን ጽሁፍ በማንበብ ወንጀለኞች ከሚጠቀሙበት ለተሻለ አላማ ያውሉታል ብዬ ስለማስብ ሁለቱም ባያነቡት ይሻላቸዋል፡፡
ወደ ዋናው ሀሳብ ልግባ፤ ከተያዝኩ በኋላ በነበሩ የመጀመሪዎቹ ቀናት ውስጥ የነበሩት‹‹ምርመራዎች›› እውነቱን እና የማውቀውን ብቻ በመናገር እራሴን ነጻ ማውጣት እንደምችል መተማመኛ መስጠትን ያለሙ ነበሩ፡፡ ለምሳሌሚያዝያ 18/2006 (በተያዝኩኝ በማግስቱ ቅዳሜ) የነበረውን ምርመራ ም/ሳጅን መኮንን በተረጋጋ ሁኔታ የምርመራው ሂደት በመከባበርእንደሚቀጥል፣ ልክ እኔ የዕለት ስራየን ለማከናወን ሙያ እንደሚጠይቀው ያክል የፖሊስ ምርመራም ተመሳሳይ እንደሆነ፣ በቁጥጥር ስርየዋልኩት ተጠርጥሬ ብቻ እንደሆነ እና በምርመራው ሂደት ወንጀል አለመፈጸሜ ከተረጋገጠ በነጻ ወደቤቴ እንደምሄድ ነበር ያስረዳኝ፡፡ይንቁናል የሚል ስሜት አስቀድሞ ስለሚያድርባቸው ተቋሙን እና እራሳቸውንም ከፍ የሚያደርግ ነገር በነዚህ የመጀመሪያ ‹‹የምርመራ››ቀናት ይናገራሉ፡፡
‹‹ይህ የወረዳ ጣቢያ አይደለም፡፡ የክልልም አይደለም፡፡ ይህ የፌደራል ወንጀል ምርመራነው፡፡ ሚኒስትር ደረጃ የደረሱ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀር እዚህ ተመርምረዋል›› ነበር ያለኝ ም/ሳጅን መኮንን በአጽንኦት፡፡ከዚህ ገለጻ በኋላ ነበር ስለህይወት ታሪኬ በመጠየቅ ቃል የመስጠት ሂደቱን የጀመርኩት፡፡
ማስታወሻ- 1. ቃል ያለመስጠት መብት
ቃሌን ያለመስጠት መብት ስላለኝ ቃሌን አልሰጥም ለማለት መጀመሪያ መብቱ እንዳለ ማወቅይጠይቃል፡፡ በወቅቱ ይህ መብት እንዳለኝ ማወቄን እጠራጠራለሁ፡፡ አውቅ ከነበረም ግን በፍጹም ትዝ አላለኝም፡፡ ቃል አለመስጠትአንድ ለምርመራ ሂደቱ ተባባሪ አለመሆንን ማሳያ ነው፡፡ ለተቋሙ የጭቆና መሳሪያ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ እንዳለ አምነን ተጨማሪ ማረጋገጫዕድል (benefit of the doubt) መስጠት የማንፈልግ ከሆነ ይህ ትክክለኛው አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ከግምት መግባት ያለበትቃል በመስጠቱ ሂደት ውስጥ ፖሊስ በእርግጠኝነት ስህተት መስራቱ አይቀርም፡፡ ይህም የማይቀረው ክስ ሲመጣ ተቋሙን ማጋለጥ እንደስልት የሚወሰድ ከሆነ እንደማስረጃ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በኛ ጉዳይ የቀረበብን ክስ የሽብር ቡድን በኅቡዕ አደራጅተዋል በሚልሲሆን ሁላችንም ቃል ስንሰጥ የተጠየቅነው እና ስናብራራ የነበረው ግን በይፋ ስንጽፍበት እና ዘመቻዎቻችንን ስናካሂድበት ስለነበረውዞን 9 ነው፡፡
አቃቤ ህግ በክሱ እያለ ያለው የከሰስኳችሁ በመጻፋችሁ እና መብትን የሚጠይቁ ዘመቻዎችንበማድረጋችሁ (በአጠቃላይ ከዞን-9 ጋር በተያያዘ) ሳይሆን ሌላ የህቡዕ ቡድን መስርታችሁ ለሽብር ዓላማ ስትንቀሳቀሱ ስለነበር ነው፡፡የሰጠነው ቃል እና ክሱን ለመደገፍ የቀረቡት ማስረጃዎች ግን ስለ ዞን-9 አውርተው አይጠግቡም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ቀናት የሚነግረውን‹‹ተቋሙ ገለልተኛ ነው፣ ሰዎችን ወንጀለኛ ለማድረግ ሳይሆን እውነትን ፈልፍሎ አግኝቶ ነጻ ሰውን ወደቤቱ ይሸኛል›› የሚለውን ዕምነትበቀላሉ ማስረጽ ከቻሉ የሚቀጥሉት ጥርጣሬ ወደመዝራት ይመስለኛል፡፡ በቀላሉ ያሉትን የማያምኑ ከሆነ ግን የተጠርጣሪውን በራስ መተማመንለመሸርሸር ህገ-ወጥ ተግባራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
‹‹ምርመራ›› በጀመርኩ በአራተኛው ቀን የተከሰተው ይሄው ነው፡፡ ሚያዝያ 21/2006ዓ.ም ምሽት ድረስ ‹‹በምርመራው›› ሂደት ውስጥ ስሳተፍ የነበረው በሙሉ የራስ መተማመን ነበር፡፡ ለምሳሌ ም/ሳጅን መኮንን፣ ም/ሳጅንእቴነሽ፣ እና ሳጅን ፈይሳ በነበሩበት ታስሬ ‹‹እየተመረመርኩ›› ያለሁት ሀሳቤን በነጻነት ለመግለጽ ባለመፍራት ነው፡፡ ያኔ ‹‹ፖሊስለህዝብ የሚሰራ ተቋም ነው የምትሉትንም አላምንም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ፖሊስ እንደ ተቋም እየሰራ ያለው አገዛዙን ስልጣን ላይ ለማቆየትነው›› ብያቸዋለሁ፡፡
ከላይ በጠቀስኩት ቀን ማታ ግን ሌላ ሊከሰት እንደሚችል የማውቀው፣ ግን ከምር ያልተዘጋጀሁበትነገር ተከሰተ፡፡ ምሽት 1፡00 አካባቢ የተጀመረው ‹‹ምርመራ›› ቶሎ ኃይለ ቃል ወደመሰንዘር እና ዛቻ ተለወጠ፡፡ በወቅቱ ም/ሳጅንመኮንን፣ የመጀመሪያ ቀን ፍርድ ቤት የወሰደን እና በየመተላለፊያው ሳገኘው ጭምር ቤተሰብ እንዲያገኘን መብት አለን፣ ፍርድ ቤትአዝዞልን ሳለ ለምንድነው የማታገናኙን እያልኩ ስጠይቀው የቆየሁት ሳጅን ምንላርግልህ እና ማዕረጉን የማላስታውሰው ፀጋየ (በቅጽልስሙ ጥጋቡ) የሚባል መርማሪ ነበሩ፡፡ የ‹‹ምርመራ››ውም ዋነኛ አጀንዳ የዞን 9 ድብቅ ግብ እና የውስጥ የስራ ክፍፍል (መዋቅር)በተመለከተ ነበር፡፡ በሁለቱ ጉዳይ ላይ እውነተኛው የማውቀው መልስ ‹‹መዋቅር የለውም›› የሚለው ነበር፡፡ ዞን 9 ድብቅ ግብምመዋቅርም ኖሮት አያውቅም፡፡ ሳጅን ምንላርግልህ መልሴ አላጠገበውም፡፡ ‹‹እኔ እንደሱ እንዳልመስልህ (የእኔን ጉዳይ በዋነኛነትወደያዘው ም/ሳጅን መኮንን እየጠቆመ) አለቅህም! ሽባ ነው ማደርግህ! ልብስህን አስወልቄ ሳልለጠልጥህ እውነቱን ብትነግረኝ ይሻልሃል!››የሚሉ ዛቻዎች ደረደረ፡፡ እኔ ግን መዋቅሩን በተመለከተ ስራ ለማቅናት ሲባል ምክረ ሀሳብ ቀርቦ እንደተወያየንበት፣ ነገር ግን ሀሳቡውድቅ እንደተደረገ ከማስረዳት በቀር የምጨምረው የማውቀው እውነት አልነበረም፡፡ ም/ሳጅን መኮንን እና ፀጋየ (ጥጋቡ) በየተራ ክፍሉንለቀው ከወጡ በኋላ ሳጅን ምንላርግልህ ከወንበሩ በመነሳት ምቾት በሚነሳ ሁኔታ ከተቀመጥኩበት ፊት ተጠግቶኝ ቆሞ ጥያቄዎችን ይደረድርጀመር፡፡
ጥያቄ፡- ‹‹ለምንድነው እነ ርዕዮትን ብቻ የምትጠይቁት?››
መልስ፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ስለሆኑ እና የታሰሩት በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ነው ብለንስለምናምን፡፡››
ጥያቄ፡- ‹‹(በቁጣ) ባንክ የዘረፈውስ ኢትዮጵያዊ አይደለም? ለምንድነው ሌላውን ወንጀለኛየማትጠይቁት?››
በእውነት እዚህ ጋ ሳቄ መጥቶ ነበር፡፡ በርግጥ የታሰረን ሁሉ ከተቻለ መጠየቅ ለህሊናየሚያስደስት ስራ ነው፡፡ እግዜርም ይወደዋል፡፡ ግን ርዕዮትን ስጠይቅ እንዲሰማት የምፈልገው፣ ትግሏ ዋጋ እንዳላጣ እና እንዳልተረሳችነው፡፡ ይህም ትንሽም ቢሆን ብርታት ይጨምርላታል ከሚል ተስፋም ጭምር ነው፡፡ ተመሳሳይ ነገር የባንክ ዘራፊ እንዲሰማው በፍጹምአልፈልግም፡፡ ጥያቄው ቀጠለ፣
‹‹ዝዋይ ለምን ሄዳችሁ?››
‹‹እነ ውብሸትን ለመጠየቅ››
‹‹አትዋሽ! በቀለ ገርባን ለመጠየቅ ነበር?››
‹‹አዎ በቀለንም ለመጠየቅ ነበር፡፡››
‹‹በቀለ ምን እንደሚል ታውቃለህ? ለምን እንደታሰረ ታውቃለህ? ኦሮምኛ ትችላለህ?››
‹‹አልችልም››
‹‹በቀለ እኮ የሚለው ኦሮምኛ የማይችሉ ሰዎች በሙሉ ይታረዱ ነው፡፡››
ስለ በቀለ ገርባ የማውቀው ጥቂት ነገር ከሚለኝ ጋር ፍጹም የሚጣጣም ስላልነበር የፊቴንመለዋወጥ መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ፊት ለፊቴ ተደንቅሮ የጥያቄ ዝናብ ሲያወርድ የነበረው ሳጅን ምንላርግልህ አሁን ማድረግ የሚፈልገውንለማድረግ በቂ ምክንያት አገኘ፡፡ የመጀመሪያዋን ጥፊ ሰነዘራት፡፡ መብቴን እየነካ እንደሆነ ስነግረው ‹‹ይህንን ነው አይደል ፈረንጆቹወስደው የሚያሰለጥኗችሁ?›› በማለት ስራውን ቀጠለ፡፡ ድብደባው እዚያ ቤት ከሚፈጽሙት ሰቆቃዎች (torture) አንጻር ትንሽ ቢሆንምአሸነፈኝ፡፡ አሁን የሚጸጽቱኝንም ቃላት ተናገረኝ፡፡ ከውጭ የነበሩት ሁለቱ መርማሪዎች ድብደባ ሲፈጸምብኝ በነበረበት ወቅት በመሐልመጥተው ገላጋይ ሆነው ነበር፡፡ ምንላርግልህ ግን ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ፡፡

ማስታወሻ፡-2. መርማሪዎች አንድ አላማ ነው ያላቸው
ሁለትና ከዚያ በላይ ሆነው ሲመረምሩ የትኛውንም ማመን አያስፈልግም፡፡ በኋላ ላይ ከሌሎችተጠርጣሪዎች ጋር ሳወራ የተረዳሁት ይህ የተለመደ አሰራር መሆኑን ነው፡፡
ሌላ ተጠርጣሪ ሲመረመር ሳጅን ምንላርግልህ ገላጋይ ሌላኛው ደግሞ እምቡር እምቡር ይላል፡፡ከዚያም ፀጋየ (ጥጋቡ) እኔ ላይ ሲያደርግ እንደነበረው ገላጋይ የሚሆነው መርማሪ ‹‹እኔ ችግር ውስጥ እንድትገባ አልፈልግም፤ ለምንእውነቱን አትነግረንምና ራስህን አትጠብቅም? ደግሞ ዘጠኝ ሆናችሁ ለሰራችሁት ስራ አንተ ብቻህን ለምን ትጎዳለህ? ሌሎቹ እኮ እየተናገሩነው፤ አይደለም ዘጠኝ ሰው የሚያውቀው ነገር ይቅርና ለሌላ አንድ ሰው የነገርከው ነገር እኮ ሚስጥር መሆኑ ያበቃል›› የሚሉ ማግባቢያዎችበመደርደር ምስኪን ምስኪን ሊጫወት ይሞክራል፡፡
የዛን ምሽት ምርመራ ሲጠናቀቅ የሁለት ሰዓት ማሰቢያ ጊዜ ተሰጥቶኝ የዞን 9 ግብ ምንእንደሆነ እና የመዋቅራችንን እያንዳንዱን የስራ ዘርፍ እንዳስታውስ የቤት ስራ ተሰጥቶኝ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ተመልሼ እንደምጠራተነግሮኝ ነበር ወደ ማረፊያ ቤት ውስጥ የተመለስኩት፡፡
በተለምዶ ሳይቤሪያ የሚባለው ማረፊያ ቤት ባለአንድ ፎቅ ህንጻ ሲሆን የታችኛው ወለል በኮሪደርተከፍሎ በግራና በቀኝ አምስት አምስት ክፍሎች አሉት፡፡ ኮሪደሩ መሀል ላይ አንዱ የግድግዳ ሰዓት ተሰቅሏል፡፡ የመጀመሪያ ሰሞንልብ ስላልኩት ሰዓት የማውቀው ምርመራ ክፍል ካሉት ሰዓቶች በመነሳት በግምት ነበር፡፡ ከሳጅን ምንላርግልህ በተሰጠኝ የቤት ስራመሰረት ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲል ተመልሼ ወደምርመራ እጠራለሁ፡፡ ከምርመራ ከተመለስኩ ጀምሮ በአዕምሮዬ ሲመላለስ የነበረው ነገርተጨማሪ መልስ ልሰጣቸው እንደማልችል እና በዚህ ምክንያት ተመልሼ ከሄድኩ በኋላ የሚደርስብኝ ሰቆቃ ማብቂያ ምን እንደሚሆን ማሰብነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ በምርመራ በማሳለፌ ድካም የነበረብኝ ቢሆንም እንቅልፍ ሊወስደኝ ግን አልቻለም፡፡ ራሴን አረጋግቼ በተሰጠኝሁለት ሰዓት እረፍት መውሰድ ብፈልግም ምንም ዓይነት ድምጽ በሰማሁ ቁጥር አምስት ሰዓት የሆነ እየመሰለኝ እባንን ነበር፡፡ እነምንላርግልህ ግን አልፈለጉኝም፡፡ አይነጋ የለም ሌሊቱም ነጋ፡፡ ጠርተው ቢደበድቡኝ ይሻል ይሆን እንደነበር እንጃ!
ማስታወሻ፡- 3. እራስን አረጋግቶ በቂ እረፍት መውሰድ
መርማሪዎቹ መቼም ቢሆን ምርመራ ጨርሰናል ደህና እደሩ ብለው አይሸኙም፡፡ ሁል ጊዜ‹‹በኋላ እንገናኛለን፤ አስብበት›› ብለው ነው የሚጨርሱት፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቀጠሮ መሰረት ምርመራው ይቀጥላል፡፡ አንዳንድ ጊዜደግሞ የውሃ ሽታ ይሆናሉ፡፡ በቀጠሮ መሰረት ብጠራም ባልጠራም ያለችውን ጊዜ በቂ እረፍት ለማድረግ መጠቀሚያ ማድረግ የሚያዋጣውአማራጭ ነው፡፡ ከድብደባው በባሰ የሚጎዳው የማያቋርጥ ጭንቀት እና የእረፍት እጦት ነው፡፡ ከአሁን አሁን ወደምርመራ ተጠራሁ ብሎመጨነቅ ጥሪውን የማዘግየትም የማስቀረትም አቅም የለውም፡፡ ‹በኋላ እንገናኝ› የምትለዋ ቀጠሮ እረፍት መንሻ ዘዴ ናት፡፡
በመቀጠል የምርመራው ዓላማ የነበረው ከጓደኞቼ ያገኟቸውን መረጃዎች በመጠቀም ብዙ እንደሚያውቁጥያቄ የሚጠይቁትም ከኔ ይምጣ ብለው እንጂ ሁሉ ነገር ላይ መረጃ እነዳላቸው ለማሳመን መጣር ነበር፡፡ በወቅቱ የእኔ ምላሽ የነበረውሁሉንም የሚያውቁ ከሆነ ለኔ ጥሩ እንደሆነ እና ምንም ጥፋት እንደሌለብኝ ከዛ በላይ ማስረጃ እንደሌለ የሚያስረዳ ነበር፡፡
ማስታወሻ፡-4. አብረው የሚሰሩ ጓደኛሞች ወጥ መልስ ለመስጠት አስቀድመው ስምምነት ላይ መድረስ
ስለ አንድ ጉዳይ ሁለት ጓደኛሞች የተለያየ መልስ ከሰጡ ሰቆቃው ሁለቱም ላይ የጠና ነው፡፡አንደኛው ወደሌላኛው መልስ የሚጠጋ ነገር እስካልተናገረ ድረስ ሁለቱም ይሰቃያሉ፡፡ በኛ ምርመራ ወቅት አስቀድመን ምንም የምንደብቀውወይንም የምንዋሸው ነገር እንዳይኖር ስንነጋገር ስለከረምን በተነጋገርነው መሰረት የአንዳችን ቃል ከሌላችን የጎላ ልዩነት አልነበረውም፡፡
በጓደኞች መሀከል ክፍተት ለመፍጠር ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ለበፍቄ ‹‹ናትናኤል እኮእውነቱን ነግሮናል፡፡ በፍቃዱ ነው አብዮት እና አመጽ እንድንጠራ የሚገፋፋን ብሏል፡፡ አንተ ለምንድነው እንዲህ የምትደብቅላቸውእነሱ እውነቱን እየተናገሩ›› ብለውታል፡፡ ቀዳዳ ካገኙ ቅያሜ በመፍጠር ከጓደኛሞች መሀል አንዱን መስካሪ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ማስፈራሪያዎችበታጨቁበት ምርመራ መሀል እራሴን ነጻ ማውጣት ቀላሉ አማራጭ እንደሆነ ደጋግመው ይነግሩኝ ነበር፡፡ ፀጋዬ (ጥጋቡ)፣ ም/ሳጅን መኮንንእና ኢንስፔክተር አሰፋ እየመረመሩኝ በነበሩበት ወቅት ፀጋዬ ተራ ስድቦችን እና ዛቻዎችን ከሰነዘረ በኋላ በዛው አፉ እኔን ማቆየትእንደማይፈልጉ እና የሚፈልጉትን ካልኩላቸው ወዲያውኑ ወደቤቴ እንደሚሸኙኝ አባቴንም መንከባከብ እንደሚሻለኝ ሲነግረኝ ነበር፡፡ የአባቴጤንነት እንዳሳሰበኝ ስለገባቸው ባገኙት አጋጣሚ ለምርመራው ግብአትነት ይጠቀሙበት ነበር፡፡
አብዛኛው የምርመራ ጊዜ በተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና ተደጋጋሚ መልሶች የሚያልፍ ነው፡፡ ይህምምርመራዎችን እጅግ አድካሚ እና አሰልቺ ያደርጋቸዋል፡፡ ዝርዝር ጉዳዮችን በተደጋጋሚ በመጠየቅ ከምሰጠው መልስ ላይ ልዩነት ለማግኘትይህንንም ተጠቅሞ ሌላ አዲስ ነገር ለማውጣጣት ይጥሩ ነበር፡፡ የተሳካላቸው ግን አይመስለኝም፡፡ በተቻለኝ አቅም ቀዳዳ ሳገኝ የማምንበትንአቋም ከመናገር ወደኋላ አላልኩም፡፡ የማውቀውን ለማካፈልም እንደዚያው፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 39ን የሚቃወም መርማሪአግኝቼ ለምን ልክ ነው ብዬ እንደማምን አስረዳኋቸው፡፡ በተለያየ ጊዜ የወሰድኳቸው የበይነ መረብ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችንምበተመለከተ ያብራራሁለትም መርማሪ ነበር፡፡
ማስታወሻ፡-5. በተገኘው አጋጣሚ አቋምን ማስረዳት
መርማሪዎቹ በተደጋጋሚ ስለተነገራቸው ብቻ የሚያምኑት ብዙ ነገር አለ፡፡ ኢህአዴግ ትግልላይ በነበረበት ወቅት ጭራቅ ተደርጎ ይሳል እንደነበረው አሁንም የነጻነት ትግል እያደረጉ ያሉትን ሰዎች እንደ ሰው በላዎች የሚቆጥሯቸውመርማሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ በነዚህ መርማሪዎች ይህን ከተማ (አ.አ) ተወልዶ ያደገ ሰው ፖለቲካ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ተደጋግሞ ሲነሱልኝከነበሩት ጥያቄዎች መሀል ይህ መንግስት ምን በድሎሃል (በግል) እንዴት እንደዚህ አይነት አቋም ልትይዝ ቻልክ? የሚለው እንደነበርአስታውሳለሁ፡፡ መልሴ ግን አጭር ነበር፡፡ ነጻነቴን ዋጋ እሰጠዋለሁ!!
ከምክትል ሳጅን መኮንን ጋር በነበረን ጊዜ የተረዳሁት ስለ አቋሞቼ በጥልቀት ማወቅ ቢፈልግምእንደ ጦር እንደሚፈራቸው ነው፡፡ ገና ማስረዳት ስጀምር ቶሎ ብሎ ‹ወደጉዳያችን እንመለስ፣ ዳግም ወደ አንተ ልትስበኝ ነው?› ይለኝነበር፡፡ ሌሎችም መርማሪዎች ተመሳሳይ ፍላጎት አይቸባቸዋለሁ፡፡ አንድ የማይረሳኝ ምሳሌ ከኢሜሌ ላይ የተገኘውን የዜና መጽሔት በተመስጦሲያነብ የነበር አንድ መርማሪ አለቃቸው ድንገት ቢሮውን ከፍቶ ሲገባ ወረቀቱን በድንጋጤ ወርውሮታል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የቻልኩት እነዚህን በአንድ በኩል መረጃ የተደፈኑ ሰዎች ሌላኛውን ጎን ማሳየት በሌላ አማራጭ የማያገኙት መረጃ ምንጭ መሆን ስለሆነ በምርመራወቅት እንደ አንድ ዓላማ ሊወሰድ እንደሚገባ ነው፡፡
አልፎ አልፎ ከሌላ ቦታ የሚመጡ (ከደህንነት መስሪያ ቤት) መርማሪዎች ለመመለስ አደጋችየሆኑ ውስብስብ ጥያቄዎችን ከመጠየቃቸው ውጭ የሚጠየቁት ጥያቄዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ መርማሪዎች የሚጠይቋቸውጥያቄዎች ለራሳቸውም ግልጽ አይደሉም፡፡ ጥያቄዎችን የሚያበጁት ከጀርባ ሆነው ምርመራውን የሚመሩት አለቆቻቸው ናቸው፡፡ አልፎ አልፎለመመለስ አደጋች የሚመስሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ለምሳሌ ሚያዝያ 27 ቀን (የአርበኞች ድል ቀን) ኢንስፔክተር አሰፋ እና አንድየደህንነት ባልደረባ ሆነው ባካሄዱብኝ ምርመራ ወቅት አንድ አስቸጋሪ ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡-
የደህንነት ባልደረባው፡- ‹‹ዞን 9 ምን ማለት ነው?››
መልስ ፡- ‹‹ዞን 9 ማለት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱንየተነጠቀ ታሳሪ ነው ለማለት የተጠቀምንበት ስም ነው፡፡››
‹‹እኔም የዞን 9 አባል (ነዋሪ) ነኝ ማለት ነው?››
‹‹አዎ!››
‹‹ጥሩ! ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን የተነጠቀ ከሆነ መቼ እና እንዴት ነው ዞን9 ነጻ የሚወጣው?››
ይህ ጥያቄ ትንሽ ለመመለስ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በርግጥ እንደማነኛውም ግለሰብ የኢትዮጵያህዝብ ነጻነቱን መቼ ያገኛል ለሚለው ጥያቄ የራሴ አስተያየት ቢኖረኝም በዚህ ምርመራ ወቅት ሀሳቤን በነጻነት ብናገር የሚያመዝነውአደጋው ነበር፡፡ ስለዚህ ማለት የቻልኩት ዞን 9 የሚለውን ተምሳሌታዊ ስያሜ አምነንበት ብንጠቀምም የዞን 9 ነዋሪዎችን ነጻ ማውጣትግን እንደ ግብ ያስቀመጥነው እና እንዲሳካም ኃላፊነት ወስደን የሰራንበት ጉዳይ እንዳልነበር ነው፡፡
አጠቃላይ የእስር ቤቱ የአያያዝ ሁኔታና የምርመራው አሰልቺነት በየዕለቱ መርማሪዎቹ ከሚነግሩኝየራሳቸው እውነት ጋር ተደማምሮ ሊያሸንፈኝ ዳር ዳር ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በተባራሪየምንሰማቸው ጓደኞቻችን እና መታሰራችን የሚቆረቁራቸው ሰዎች የሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ እና የበይነ መረብ ዘመቻ ተጨማሪ የጥንካሬምንጭ ሆነውኛል፡፡ የማታዎቹ ምርመራዎች ለዚህ ምቹ ናቸው፡፡ ካስተዋልኩት የተረዳሁት የማታውን (የሌሊቱን) የምርመራ ጊዜ መርማሪዎቹለሚከፈላቸው ተጨማሪ ገንዘብ እና ስላመሹ መ/ቤቱ ለሚያቀርብላቸው ቆሎ እና ውሃ ካልሆነ በስተቀር አይፈልጉትም፡፡
በማታው ምርመራ ወቅት ቶሎ የመሰላቸት እና የኃይል እርምጃ ወደመውሰድ ይሄዳሉ፡፡ ብዙ ማውራት አይፈልጉም፡፡ ስለዚህአለቆቻቸው የሰጧቸው ጥያቄዎች ሲያልቁባቸው የተለያዩ ስፖርታዊ ቅጣቶች በማዘዝ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አማካኝነት ጨዋታ(game) ይይዛሉ፡፡ ወይንም ሌላ ክፍል ምርመራ ላይ ካለ ጓደኛቸው ጋር በኢንተር ኮም ወግ ይይዛሉ፡፡ በተመርማሪዎች ላይ ያላግጣሉ፡፡በማታዎቹ ምርመራዎች ወቅት ለሚነሱ ጥያቄዎች ረዘም ያሉ መልሶችን መምረጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ መልሶችንም በህገ-መንግስቱ ስለተፈቀዱመብቶች፣ ስለ ተቋማት ነጻነት አስፈላጊነት፣ እና መሰል ፖለቲካዊ ጉዳዮች ወደማብራራት ማጠጋጋት፣ ከተቻለ የመርማሪዎቹን ቀልብ ለመሳብእና ከሚወስዷቸው አላስፈላጊ የኃይል እርምጃዎች መከላከል ይቻላል፡፡

ማስታወሻ፡-6. አቤቱታ ማሰማት
የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ፍርድ ቤት በሚወሰዱበት ጊዜ ያለውን አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተለምዶ ፍርድቤት በፖሊስ የአያያዝ በደል ተፈጽሞብኛል ብሎ የሚያመለክት ሰው ከፍርድ ቤቱ መልስ ተመልሶ ማዕከላዊ እንደሚገባ ስለሚያውቅ የባሰአደጋ ለመቀነስ በሚል አቤቱታ ከማቅረብ ሊቆጠብ ይችላል፡፡ ነገር ግን አቤቱታውን አቀረበም አላቀረበም ሰብዓዊ መብቱን ከመረገጥአይድንም፡፡ ልዩነቱ የሚሆነው የፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ የመብት ጥሰቱ ተመዝግቧል ወይስ አልተመዘገበም የሚለው ነው፡፡
እዚህ ላይ የምመክራቸውን ነገሮች ያለማድረግ ቁጭት በእኔ ብቻ ሳይሆን ብዙ ታሳሪዎች ላይ ያስተዋልኩት ነው፡፡ ያላደረግሁትንአድርጉ ብሎ የመጠየቅ ይሉኝታም ጽሁፉን ልጻፍ ወይስ ይቅርብኝ ብዬ እንዳንገራግር አድርጎኝ ነበር፡፡ ውስጤ ከሚብላላ ግን ጽፌውአንብቦ ቢያንስ አንድ ሰው የተለየ መንገድ ተከትሎ ጉዳት ቢቀንስ የተሻለ ነው የሚለው ሀሳብ የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ሌሎቹምጓደኞቼ ተመሳሳይ መንገድ አልፈዋል፡፡ የነሱንም የምርመራ ሂደት ይጽፉታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እስከዛው ድረስ መታገስ ያልቻለየሀገር ውስጥ ነዋሪ ግን ወደ ቂሊንጦ ጎራ ብሎ ከራሳቸው አፍ ጠይቆ መረዳት ይችላል፡፡ እኔ ቀረኝ የምለው ነገር ካለኝ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
ማስታወሻ፡-7. የማዕከላዊ ቤቶችን (ክፍሎች) ይተዋወቁ
ማዕከላዊማዕከላዊ
በግቢው ውስጥ ሶስት የእስረኛ ማቆያ ቦታዎች አሉ፡፡ በተለምዶ ጣውላ ቤት፣ ሳይቤሪያ እና ሸራተን በመባል ይታወቃሉ፡፡ጣውላ ቤት አምስት ክፍሎችን በተርታ የያዘ ሲሆን የምርመራ ቢሮዎች ያሉበት ህንጻ ጀርባ ምድር ላይ ያሉ ክፍሎች ናቸው፡፡ እኛ ማዕከላዊታስረን በነበርንበት ወቅት ሶስቱ ክፍሎች ለሴት ተጠርጣሪዎች ማቆያ ሲሆኑ ቆርቆሮ መከለያ ተደርጎለት፣ ደግሞ የተቀሩት ሁለቱ ምስክርለመሆን የተስማሙ ወንድ ተመርማሪዎች ማቆያ ነው፡፡ ማሂ እና ኤዶም ከሶስቱ ክፍሎች በአንደኛው ከሌላ ሴት ታሳሪዎች ጋር እንዳይገናኙሁለቱ ብቻ ተለይተው ነበር፡፡ ጣውላ ቤት ፊት ለፊት የክፍሎቹ ወለል ጣውላ መሆኑ ነው ጣውላ ቤት የሚል ስያሜ ያሰጠው፡፡ ይህንንማቆያ ቤት አልፎ አልፎ ሂልተን በማለት የሚጠሩት ሰዎች ገጥመውኛል፡፡
ሳይቤሪያ የሚባለው የእስረኛ ማቆያ በቅዝቃዜው ምክንያት ነው ስሙን ያገኘው፡፡ ይህ ባለአንድ ፎቅ ህንጻ ምድር ላይየሚገኘው ማቆያ ቦታ በረጅም ኮሪደር የተከፈለ ሲሆን በግራና በቀኝ ከ2 ቁጥር እስከ 10 ቁጥር የተለጠፈባቸው አምስት አምስት ክፍሎችአሉት፡፡ 8 ቁጥር ከተለጠፈበት ውጭ ሌሎቹ ወጥ ክፍሎች ሲሆኑ 8 ቁጥር የተለጠፈበትን በር ተከፍቶ ሲገባ ግን ሌሎች ራሳቸውን የቻሉአራት ክፍሎች አሉት፡፡ የበለጠ ቅጣት እንዲቀጣ የሚፈልጉት ተመርማሪ እነዚህ ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር የሆነ ጨለማ ክፍል ውስጥያስሯቸዋል፡፡ ሳይቤሪያ የምርመራ ግለቱ እስኪሰክን ድረስ ተመርማሪዎች የሚቆዩበት ቦታ ሲሆን ሁሉም ክፍሎች ከኤሌክትሪክ መብራትውጭ ምንም አይነት ብርሃን አይደርሳቸውም፡፡ የክፍሎቹ ግድግዳዎች ወለሉና ጣራው ከኮንክሪት የተሰራ ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ከውጭ ተዘግቶየሚውለው ክፍል በቀን ለሶስት ጊዜ ያክል ይከፈታል፡፡
ሳይቤሪያ ውስጥ ያሉ ክፍሎች ጠዋትና ማታ በተራ በተራ እየተከፈቱ ተመርማሪዎች በጋራ ወደሚጠቀሙት ባለስድስት ክፍል ሽንት ቤት እና መታጠቢያ ቤት እንዲሄዱና ተጠቅመው እንዲመለሱ ለደቂቃዎች ፈቃድ ያገኛሉ፡፡ ለሌሎች ጥቂት ደቂቃዎች ደግሞ የፀሐይብርሃን ለማግኘት ይፈቀድልን ነበር፡፡ ፀሐይ የምናገኘው በጣውላ ቤት እና በህክምና ክሊኒኩ መሐከል ባለ ክፍት ቦታ ላይ ነበር፡፡ጣውላ ቤት ያሉት ክፍሎች በር ክፍት ስለሚሆን ከማሂ እና ኤዶም ጋር በዓይን እና በምልክት ብቻ እናወራ ነበር፡፡ የሳይቤሪያ ክፍሎች በየተራ በሳምንት አንድ ቀን የሚጸዱ ሲሆን ባለችን መታጠቢያ ጊዜም የምናገኘው በነዚህ ቀናት ብቻ በሳምንት አንዴ ነው፡፡
ሸራተን ለ12 ሰዓት ፀሐይ የሚገኝበት፣ ቲቪ የሚታይበት እና የሽንት ቤት እና የመታጠብ ፍላጎት ያለው ሰው የፈለገውን ማድረግ የሚችልበት ቦታ ነው፡፡ የምርመራው ሂደት ሲጠናቀቅ ቀለል ባለ ጉዳይ የሚመረመር ሰው ወይንም ደህና ባለስልጣን ዘመድ ያለውሰው ሸራተን ሆኖ የማዕከላዊ ቆይታውን ያጠናቅቃል፡፡
በመጨረሻም አንድ እብሪተኛ መርማሪ በተናገረኝ ንግግር ማስታወሻየን ላጠናቅቅ፡፡ እንዲህ ነበር ያለኝ፣ ‹‹መንግስትብዙ ዓይኖች እና ጆሮዎች አሉት፡፡ እናንተ ደግሞ ስታወሩ የነበረው በእኛው ስልክ፣ ከሀገር ስትወጡ የነበረው በእኛው በሀገራችንአየር መንገድ እና በቦሌ በኩል ነበር፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችሁን መረጃ አለን፡፡ አንተ አሁን እየደበቅህን ነው፡፡ ይህ ደግሞለአንተ አይጠቅምም፡፡ እኛ ምርጫ እንሰጥሃለን፡፡ ሕይወትህን ወደብርሃን መውሰድ የምትፈልግ ከሆነ ወደዚያው እንመራሃለን፡፡ አይአልፈልግም የምትል ከሆነ ደግሞ መውጣት ወደማትችለው ድቅድቅ ጨለማ እንከትሃለን፡፡ ምርጫው የአንተ ነው፡፡››

Source: Zone9