Sunday, May 18, 2014

ፓርቲው በዩኒቨርስቲዎች የጠፋው ህይወት እንዲጣራና ተጠያቂዎች ለህግ እንዲቀርቡ ጠየቀ

“የአኖሌ” ሃውልትን አጥብቄ እቃወማለሁ ብሏል ሰማያዊ ፓርቲ የሻማ ማብራት ስነ-ስርአት ያካሂዳል
       በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮምያ ልዩ ዞን ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በተከሰተው ግጭት የሞቱ ሰዎችን አስመልክቶ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ባወጣው መግለጫ፤ እርምጃውን የወሰዱ የፀጥታ ሃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ አሳሰበ፡፡ ያለፈን የታሪክ ጠባሳ አጥልቶ በማውጣት በብሄረሰቦች መካከል ጥላቻ እንዲነግስ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው፤ በቅርቡ በአርሲ ዞን የተገነባውን “አኖሌ” ሃውልት አጥብቆ እንደሚቃወም ገልጿል፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባለ 8 ነጥብ መግለጫ ያወጣው አትፓ፤ ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ባቀረቡት ተቃውሞ በተነሳው ግጭትና አመፅ፤ በመንግስት ፀጥታ ሃይሎች የተወሰደው እርምጃ ከመጠን በላይ በመሆኑ ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚኮንን አስታውቋል፡፡
ለተፈጠረው ቀ ውስ መነሻው ማስተር ፕላኑ ይሁን እንጂ ለቀውሱ መባባስ ኢህአዴግ የሚከተለውየኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሙስና መስፋፋት፣ ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ የበይ ተመልካች መሆናቸው የፈጠረው እምቅ ብሶት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ፓርቲው ያምናል ያለው መግለጫው፤ በልማትና ኢንቨስትመንት ሰበብ አርሶ አደሩን ከየትኛውም የሃገሪቱ ክልል ማፈናቀል እንዲቆም ጠይቋል፡፡ የኑሮ ውድነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጣን ማስተካከያ እንዲደረግባቸው፣ በነጻ ፕሬስ ላይ አፈናው ቆሞ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ አባላት እንዲፈቱ ሲልም ጠይቋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሔር በተቧደኑ ወገኖች መካከል እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ወደ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ሳያመራ ብሄራዊ እርቅን ማምጣት ያስፈልጋል ያለው ፓርቲው፤ ገዥው ፓርቲ በብሄሮች መካከል የቆየን ቁርሾና ጠባሳ እንደ አዲስ በማጉላት አዲሱን ትውልድ በቂም በቀልና በተበዳይነት ስሜት እንዲብሰከሰክ በማድረግ፤ ከመፋቀር ይልቅ ጥላቻ እንዲሰፍን ከአንድነት ይልቅ መለያየት እንዲስፋፋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየሰራ ነው ሲል ወቅሷል፡
በተለይ በቅርቡ በአርሲ ዞን “አኖሌ” በሚል ስያሜ የተገነባው ሃውልት፤ የአማራና ኦሮሞ ብሔር ቁርሾ እንዲያገረሽ የሚደርግ በመሆኑ አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ፤ ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ በተነሳ ተቃውሞ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ህይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ለማሰብ ዛሬ ከ9 ሰዓት ጀምሮ የሻማ ማብራት ስነ-ስርአት እንደሚያካሂድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ “ከማስተር ፕላኑ ጋር ብቻ ሳይሆን በጎንደርና በባህርዳርም ከመሬት ጋር በተያያዘ ግጭት የሞቱ ሰዎች አሉ” ያሉት አቶ ዮናታን፤ በሻማ ማብራት ስነ- ስርአቱ እነዚህም ዜጎች እንደሚታሰቡ ተናግረዋል፡፡ በሻማ ማብራት ስነ-ስርአቱ ላይ እንግዶች መጋበዛቸውን የተናገሩት አቶ ዮናታን፤ “እግረ መንገዳችንንም ሰዎች የትኛውንም ጥያቄ ቢያነሱ መልሱ ግድያና መሳሪያ መምዘዝ ሊሆን አይገባም” የሚለውን አቋማችንን ደጋግመን እናንጸባርቃለን ያሉ ሲሆን ግድያ የፈፀሙ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡም ጥሪ እናስተላልፋለን ብለዋል፡፡
Source: addisadmassnews

No comments: