Sunday, April 20, 2014

የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የታሰሩ ሙስሊሞችን ክስ ተቀበለ

ጋምቢያ የሚገኘው የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሽብር ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙ “የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት ያቀረቡትን የክስ አቤቱታ እንደተቀበለ ምንጮች ገለፁ፡፡
የኮሚቴው አባላት የክስ አቤቱታውን ያቀረቡት ከወራት በፊት ሲሆን በእነ አቡበከር አህመድ መዝገብ በሽብር የተከሰሱት 28 ግለሰቦች፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከአወሊያ ት/ቤት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው አለመግባባት በመፍትሔ አፈላላጊነት የመረጣቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ መግባቱን በመቃወማቸው “አሸባሪ” ተብለው ለእስር መዳረጋቸውን ለኮሚሽኑ አመልክተዋል፡፡
“አህባሽ” የተሰኘውን የሊባኖስ አስተምህሮ በግድ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ለመጫን የተለያዩ ስልጠናዎች መሠጠታቸውን የጠቆመው የክስ አቤቱታው፤ ይህን “የመንግስት አካሄድ” የታሠሩትን ጨምሮ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በሠላማዊ መንገድ ቢቃወሙም መንግስት የተቃወሙትን በማሰር፣ የሃይማኖት መሪዎችን ከሃላፊነታቸው በማንሣት፣ እስላማዊ ት/ቤቱን በመዝጋት መንግስት አፀፋዊ እርምጃ እንደወሰደ ያስረዳል፡፡
በጥር 2004 ዓ.ም “የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት በችግሩ ዙሪያ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር ለመነጋገር መንግስት ከተስማማ በኋላ ቃሉን በማጠፍ፣ የኮሚቴውን አባላት እና ተቃውሞ ያሰሙትን አስሮ በአሸባሪነት ክስ እንደመሠረተባቸውም የክስ ማመልከቻው ያብራራል፡፡
በማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን የገለፁት ተከሳሾቹ፤  ከቤተሰቦቻቸው፣ ከህግ አማካሪዎቻቸው እና ከህክምና ባለሙያዎች ጋር እንዳይገናኙ መደረጉን፣ ቤተሰቦቻቸውም በፖሊስ ወከባ እንደደረሰባቸው በክስ ማመልከቻቸው ጠቁመዋል፡፡
ተቀማጭነቱን ጋምቢያ ያደረገው የአፍሪካ ሰብአዊና ህዝባዊ መብቶች ኮሚሽን የቀረበለትን የክስ አቤቱታ መርምሮ የሚያስተላልፈው ውሣኔ የሚጠበቅ ሲሆን የፍርድ ሂደቱን እስከማቋረጥ ሊደርስ የሚችል ውሣኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚገመት ምንጮዎች ጠቁመዋል፡፡
በ1987 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት ስር የተቋቋመው ኮሚሽኑ፤ የህብረቱ አባል አገራት የህዝባቸውን ሰብአዊ መብት ማስጠበቅ አለማስጠበቃቸውን የመመርመር ስልጣን ያለው ፍ/ቤት እንደሆነ ያመለከቱት ምንጮች፤ ከሌሎች መሰል የሰብአዊ መብት ተቋማት በተሻለ ውሳኔው በአባል ሀገራቱ ተቀባይነት እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት፣ የተከሣሾቹን ቃል የመስማት ሂደት ባለፈው አርብ ሚያዚያ 3 የተጠናቀቀ ሲሆን የመከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 4 ተቀጥሯል፡፡

Source: http://www.addisadmassnews.com

No comments: