አባይ የማን ነው?
አባይን እንደ ኢትዮጵያዊነት መገለጫ የምንቆጥረው ሰዎች መቼም ጥቂት የምንባል
አይደለንም፡፡ ታዲያ በወያኔ ጽ/ቤት ህንጻ ላይ የተሰቀለው ትልቅ ቢል ቦርድ የታላቁን
የህዳሴ ግድብ እና አባይን ከጀርባው ያደርግና ከላዩ ላይ ትልቅ የፓርቲውን አርማ
በብሔር ብሔረሰቦች ባንዲራ አጅቦ የተለመደውን የግድቡን ግንባታ ቅስቀሳ የመሰለ
መፈክር ያስቀምጣል፡፡ ይህ አባይን የፓርቲ የማድረግ አባዜ እነ ኢቴቪን እና ፋናን
በመሳሰሉ የፓርቲ ልሳኖች ሲገለጽ ከርሞ አሁን ቢልቦርዱ ጠቅልሎ ስለገለጸልኝ ነው፤
‹አባይ የማን ነው?› የሚለውን ጥያቄ ያነሳሁት፡፡ እሺ! ኢህአዴግን ያልመረጠስ? የፓርቲ
አባል ያልሆነስ? አባይ የእርሱ አይደለምን? የአባይን መገንባት ሲፈልጉ የኖሩት ወያኔ እና
ተቀጥጽላዎቹ ብቻ ናቸው? ይህ ህዝባዊ የጋራ መገለጫን ነጥቆ የፖለቲካ ጨዋታን
ማድመቂያ ማድረግ የተለመደ የፓርቲው አካሄድ ቢሆንም (የባንዲራ ቀንን
ያስታውሱዋል) የህዳሴው ግድብ ነገር ግን ከፓርቲ አመራሮች ጨዋታና የኢቲቪ
ፕሮፖጋንዳ ባለፈ የእያንዳንዱ ካድሬ ንግግር ማሟሻ እና መለማመጃ ሆኖ ከራቀን
ቆይቶዋል፡፡
በየትኛውም የሲቪል ሰርቪስ ስራ ውስጥ የቢሮክራሲው አንዱ አካል እየሆነ የመጣው
ግድብ የእኛ ያልሆነ እና ለፓርቲው ብቻ የተሰጠ ይመስል በባለቤትነት የያዙት ካድሬዎች
ብዛት ሳያንስ በየግርግዳው ላይ አባይን የሚያሞግሱ ፉከራዎችን (የማይገናኙ ጉዳዮች
ማገናኛም ጭምር ሆኖ) ለማግኘት አቅራቢያዎ የሚገኝ ወረዳ ጽ/ቤት ጎራ ማለት
ይበቃል፡፡ ገፋ ሲልም ለግል ጉዳይዎ አገልግሎት ለማግኘት የሄዱበት የሲቪል ሰርቪስ
መሥሪያ ቤት የህዝብ አገልጋይ ከአገልግሎቱ በላይ ስለግድቡ ለደቂቃ አለመቋረጥ
ሲጨነቅ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡
ከአገር ኩራትነት እና ግርማነት ቁልቁል ወርዶ የካድሬ ጉዳይ፣ የፖስተር ማድመቂያ፣
የንግግሮች መክፈቻ እና መዝጊያ ሲሆን “ኧረ ተው አባይ እኮ የእኛም ነው” የምንለው
ለማን ነው?
ለሰከንዶች እንዳይቋረጥ…
ሰሞኑን የምንሰማቸው ካድሬያዊ ንግግሮች አቅጣጫ የሳቱት አባይን የእኛ ጉዳይ
እንዳልሆነ በማስመሰላቸው ብቻ አይደለም፡፡ ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ፍሬ ነገሮችን
በመቀላቀል የግድቡ መገንባት ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ አድርገው ማቅረባቸውም ጭምር
ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ የክ/ከተማ (ወረዳ) ስራ አስፈጻሚ “የግድቡ ግንባታ ለደቂቃ
እንዳይቋረጥ የእኛ ድርሻ ከፍተኛ ነው” የሚል ንግግር በስበሰባው ማጠቃለያ ላይ
ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ጉዳዩን የሚገርም የሚያደርገው በሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት
ሰጪው እና በግድቡ ግንባታ መቋረጥ እና አለመቋረጥ መካከል ጨርሶ ግንኙነት
አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን የግድቡ መቋረጥ እንደ አንድ የሚያሰጋ እውነት ሆኖ መቅረቡም
ጭምር ነው፡፡ “መቋረጥን ምን አመጣው?” ብለን ብንጠይቅ የግድቡን ተገንብቶ ማለቅ
በውስጠ አዋቂ የመጠርጠር ስሜት እየተሰማን እና እያሳየን እንዳለን ያሳብቅብናል፡፡
ይህ በቅጡ ያልተቃኘ ካድሬያዊ ፕሮፖጋንዳ እንዲባል የሚፈለገውን(መባል ያለበትን)
መልእክት መሳቱ እኛን ከማሰልቸቱ እና ወደ ዳር ከመግፋቱ ባሻገር ያለው ትልቁ ችግሩ
ነው፡፡ እስቲ አሁን አባይ እንዳይቋረጥ ሥራህን በስርዓት መስራት አለብህ የሚል
ኩርኩም የሚደርስበት ሲቪል ሰርቫንት (የደሞዙ ነገር ሳያንስ) አባይን ቢያኮርፈው
ይፈረድበታል፡፡
No comments:
Post a Comment