ኢትዮጵያ
ውስጥ ዴሞክራሲን ያለ
ደም ማምጣት ይቻላል
ወይስ?
ያስተሰርያል
ምናልባት “የጠፋውን ትውልድ” ፖለቲካዊ ምኞት የሚወክል አንድ ነገር ጥቀስ ብባል መጀመሪያ ከሚመጡልኝ ነገሮች አንዱ የቴዲ አፍሮ “ያስተሰርያል” ነው። የዚህ ዘፈን ልቀት ግጥሙ ወይም ዜማው አይመስለኝም፤ መልእክቱ ነው። አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ! የምርጫ 97 መንፈስ ቀደም ሲል እንዳልኩት በመሆኑ ይፈልግ የነበረው “ስርየትን” ነበር፤ ደም የማይፈስበት ስርየት። አለመታደል ሆኖ መሣሪያውን የታጠቀው የፖለቲካ ቡድን ስርየትን ያለደም ማሰብ የማይችል ድንጉጥ አማኝ ነው፤ ስለዚህም ደም ፈሰሰ፣ ለዚያውም “ስርየት” ላያመጣ።
የነጻነትን እና የዴሞክራሲን “ስርየት” ያለ ደም መፍሰስ ማግኘት እንዳልቻለ የተመለከተው “የጠፋው ትውልድ” በምርጫው ማግስት ብዙ ዋጋ ከፈለ። ይህን ተከትሎም እንደገና ወደ ጥንቸል ስጋቱ ተመለሰ። ኢሕአዴግም አገዘው፤ በአንድ በኩል ከጥቅማ ጥቅም ጋራ የተያያዘ የምልመላ ስትራቴጂ አምጥቷል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተቃዋሚነት ቀርቶ ብዙዎችን ሊያደራጅ በሚችል መልኩ የተለየ አስተያየት መያዝ የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል። በቤተሰብ፣ በንግድ፣ በትምህርት ወዘተ ሐላፊነቶች የተያዘው “የጠፋ ትውልድ” ፖለቲካን በጥንቸላዊ ጥንቃቄ ወደማየቱ መመለሱ ወደ ቀደመ ቤቱ እንደመመለስ ነው። ነገር ግን የአሁኑ ዘመን የተለየ ነው፤ አፈናውን ማቅለልና ማለፍ የሚችልባቸው አማራጮች አሉ። ስለዚህም እንደ ደርግ ዘመን መንግሥት የሚለውን ብቻ የመስማት ግዴታ የለበትም፤ ፖለቲካዊ ተሳትፎውንም በተለያየ መልኩ “ስሙን ሳይገልጽ፣ ድሙጹን ሳያሰማ” በለሆሳስ መቀጠል ችሏል።
የኢሕአዴግ አያያዝ “ያለደም ስርየት የለም” የሚለውን የብሉይ ሕግ የሚያጸና ሆኗል። ለታይታና ለዲፕሎማሲያዊ ፍጆታ ከሚሆነው በቀር እውነተኛ የዴሞክራሲ እና የመቻቻል ምልክቶች ጨርሰው ሊጠፉ የቀራቸው እጅግ ጥቂት ነው። “ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ያለ ደም ማምጣት ይቻላል ወይስ አይቻልም?” የሚለውን ክርክር በድጋሚ የፖለቲካችን ቁልፍ አጀንዳ እያደረገው ያለውም ራሱ ኢሕአዴግ ነው። “የጠፋው ትውልድ” ተስፋውን አልጣለም፤ ከደርግ ጊዜ በተለየ ፖለቲካዊ ሐሳቡን በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማረመድ ስለመቻል አለመቻሉ ግን እርግጠኛ አይደለም። ስለዚህም በክርክሩ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል። በፖለቲካው ተስፋ ቆርጦ ሌላ ሕይወቱን ስለማሸነፍ ብቻ ለማሰብ የወሰነ አለ፤ ፖለቲካውን እንደ ትግል በማየት ተሳትፎውን የቀጠለ ጥቂት አለ፤ የሚከፍለውን ዋጋ በሚቀንስ መንገድ በዴሞክራሲ ግንባታ መሳተፍ የሚመኝ ነገር ግን መንገዱ ጠፍቶት ግራ የተጋባ አለ፤ ራሱን ኢሕአዴግን በመቀላቀል ጥቅማ ጥቅሞችን እያገኙ በዚያውም ከውስጥ ለውጥን መጀመር ይቻል እንደሆነ ብሎ የሚያስብም አይጠፋም…። የኢሕአዴግን አመራር እያደነቀ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚል የዚሁ ትውልድ አባል የማያውቅ ሰው ካለ አንዱን ድረ ገጽ ይጎብኝ።
“የጠፋው ትውልድ” የሽግግር ዘመኖች ትውልድ ነው፤ ለዚያውም የከሸፉ ሽግግሮች። ይህ ጠቃሚ ጎኖች ቢኖሩትም ጉዳቶችም አሉት። አንዱ ጉዳቱ ትውልዱ በፖለቲካው ውስጥ አሻራውን የሚተውበት እድልና ጊዜ ማጣቱ ነው። ሆኖም ይህ ትውልድ ደርግ እና ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ መኖር ያልነበረባቸው፣ ድጋሚም መምጣት የሌለባቸው የፖለቲካ ስርአቶችና አመራሮች መሆናቸውን ኖሮ አይቷቸዋል። ይህ ትውልድ ሁሉንም ፖለቲካዊ ጽንፎች በአያቶላዎቹ ሲተነተኑ ሰምቷል፤ በፊት አውራሪዎቹ ሲተገበሩ አይቷል፣ ኖሯቸዋልም። ይህ ትውልድ የፖለቲካ ሐላፊነቱን ካልተወጣ አገራችን አዳዲስ ደርጎች እና አዳዲስ ኢህአዴጎችን ማስተናገዷ እንደማይቀር እሰጋለሁ። ያን ጊዜ ብዙ መንግሥቱዎች ወይም ብዙ መለሶች ይወሩናል፤ አያርግብንና! “የጠፋው ትውልድ” ከዚህ ልምድ የሚቀስመው ትምህርት አገሪቱን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚያሸጋገር ቀመር እና ፖለቲከኞች እንዲያፈራ ይረዳው ይሆን? እስከዚያ ድረስ “እንደ ጠፋ” ትውልድ እንቆጥረዋለን፤ ልክ በጣም አልፎ አልፎ እንደምናገኘው ሰው፤ “ምነው ጠፋህ?” እንደማለት! አይዞን!
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ
ኢትዮጵያ
በክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments:
Post a Comment