Sunday, September 6, 2015

ከብሄር ፖለቲካ እንውጣ!

ethiopian
የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገንባ!
በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ኣቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሲናገሩ ኣገራችንን የሚበትኑ ኣጥፊ ዘሮች ያሏቸውን ሶስት ጉዳዮች ኣነሱ። ኣንደኛው ጠባብነት፣ ሁለተኛው ትምክህተኛነት፣ ሶስተኛው በሃይማኖት ሽፋን የሚራመድ ኣክራሪነት ናቸው ኣሉ። በመሰረቱ እነዚህን ጉዳዮች ኣቶ ሃይለማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሷቸው ጉዳዮች ኣይደሉም። በ”ኢህዓዴግ” ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ሁሌም ሲባሉ የነበሩ ናቸው። ኣቶ ሃይለማርያም ኣዲስ ነገር ኣልተናገሩም።
ለማናቸውም ግን እነዚህ ኣደገኛ ዘሮች ከየት መጡ? ኣገሪቱንስ ወዴት እየወሰዱ ነው? በርግጥ ከብሄር ፖለቲካው ኣዝማሪዎች ኣልፎ ወደ ታች ወርዶ የኔብጤው ተራው ህዝብ ኣካባቢ እነዚህ ዘሮች ጎልተው እየታዩ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይና ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ያለመቻሏ ጉዳይ፣ የሰብዓዊ መብት ኣያያዝ ጉዳይ ሃላፊነት ለሚሰማው ኢትዮጵያዊ፣ ለዓለማቀፍ ተቋማትና ለኢትዮጵያ ወዳጅ ሃገራት ዲፕሎማቶች በጣም ኣሳሳቢ ጉዳይ ሆኖባቸው ኣያለሁ።
ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግሩ እንመለስና በመጀመሪያ እሳቸው ራሳቸው ያመኗቸው እነዚህ ሶስት ጉዳዮች በሰፊው የሚታዮት በኣንድ ሃገር ውስጥ ፖለቲካው በጠባቡ ሲቀረጽ፣ ወይም በየቤትህ እደር ኣይነት የፖለቲካ ጨዋታ ሲጀመር ወይም የፖለቲካው ጥብቆ ሲጠብ ነው። ሳይንሳዊ በሆነ ኣገላለጽ የማንነት ፖለቲካ (Identity Politics) የሚባለው ሲሆን በተለይ ብዙህ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ይህ የፖለቲካ ስርዓት ሲዘረጋ የሚያመጣቸው ወይም ከዚያ የሚፈለፈሉ ችግሮች ብዙ ናቸው። የብሄር ፖለቲካ የማህበራዊ ካፒታል ምስጥ ነው። ለዚህም ነው ምሁሩ፣ ተማሪው፣ የተማረው፣ ያልተማረው ሁሉ ላለፉት ሃያ ዓመታት በላይ የብሄር ፖለቲካን ሲነቅፍ የነበረው:: የማንነት ፖለቲካ እነዚህን ኣደገኛ ነገሮች እንደሚያመጣ ብዙ ሳይንሳዊ ምርምር የሚጠይቅም ኣልነበረም። የብሄር ፖለቲካ ስነ- ልቦናው ራሱ ጠባብነት ነው። ከጎሳው ያላለፈ የፖለቲካ ስብእና ይዞ እንዲያድግ የሚያደርግ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ የተጫነው በመሆኑ የጠባብነት መነሻው ይሄው የብሄር ፖለቲካ ነው።
ትምክህተኝነት የሚባለውም ከዚሁ ከጠባብ ኣስተሳሰብ የሚመነጭ የኣንድ ዛፍ ቅርንጫፍ ነው። ሰው ጠባብ ሲሆን ነው የሚመካው። በወንዙ በጎሳው ሲመካ ጠባብ ሆኖ ነውና። ጠባቦች ሁል ጊዜም ትምክህተኝነት ኣያጣቸውም። ሁለቱም ባህርያት የተያያዙ ከኣንድ መራራ የብሄር ፖለቲካ ምንጭ የሚቀዱ ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲናገሩ ተማሪው ላይ ተጽእኖው ይታያል እንጂ እነዚህን ዘሮች የሚዘራው ኣስተማሪው ነው ኣሉ። ማን ነው የጠባብነትን ፖለቲካ የሚያስተምረው? ህወሃት “ኢህኣዴግ” ኣይደለምን? ህወሃት “ኢህዓዴግ” ከመምጣቱ በፊት ትግሬው፣ ዓማራው፣ ኦሮሞው ወዘተ ኣብሮ ቁጭ ብሎ ሲጫወት መች የብሄር ነገር ትዝ ብሎት ያውቅ ነበር? ቢታወሰውም እየተቀላለደ ከመኖር ውጭ መራራ ስር ኣልነበረውም። ለእነዚህ ኣደገኛ ዘሮች መፈጠርና ማደግ ጥሩ መፈልፈያ የሆነው ራሱ የፖለቲካው ቤት መሆኑን መረዳት ብዙ ምርምር ኣልጠየቀም።
ቡድኖች ለምንድነው የብሄር ወይም የሃይማኖት ማንነታቸውን ይዘው ወደ ፖለቲካ የሚሳቡት? ካልን የፖለቲካን ሃይል መሳሪያ በማድረግ የቡድንን የወል ጥቅምና የበላይነት ለማረጋገጥ ነው። የፖለቲካው ስልጣን የመሳሪያ ሃይል ያለውንና የኢኮኖሚውን ክፍል ስለሚያዝ ያንን ቡድኖች መቆጣጠር ከቻሉ ለቡድናቸው ኣቋራጭ እድገት ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ስለሚያዩት ነው። በዚህ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ኣክራሪነት፣ ልዮነትን ማድመቅ የመከሰታቸው እውነት ለምን ጥያቄ ውስጥ ይከተናል? ሃይማኖታዊ ኣክራሪነትም የሚከሰተው ኣጠቃላይ የፖለቲካው ቅርጽ በማንነት ላይ ሲረብብ ሃይማኖታዊ ማንነታቸውን ይዘው ወደ ስልጣን እንዲሳቡ የሚያደርግ ስነ ልቡናዊ ድባብ ሲፈጠር ነው። በመሰረቱ ሃይማኖትን ማጥበቅ ማለት ኣይደለም ኣክራሪነት ማለት። ሃይማኖታዊ ኣክራሪነት የሚፈጠረው በሃይማኖቱ መሰረት ላይ የቆመ ፖለቲካ ለመመስረት መጣርና በጋራ ህልውና (coexistence) ኣለማመን ነው። በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን እንዲህ ዓይነት ባህርያት ሲገለጹ ኣክራሪነት መጣ እንላለን። ይህ ኣክራሪነት በኢትዮጵያ ከታየ ኣካባቢያዊ ኣስተዋጾዎች እንዳሉ ሆነው ራሱ የፖለቲካው ተፈጥሮና የመንግስት ኣያያዝ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ማድረጋቸው ኣይካድም። በኣጠቃላይ ምንጩ የማንነት ፖለቲካ ሆኖ ሳለ ለምን የመንግስት ሰዎች እነዚህን ችግሮች እየጠቀሱ ኣጥፊዎች ናቸው እንደሚሉ ዶክተር ዳኛቸው በቅርቡ በ VOA እንዳስረዱት ለማንም ኣይገባም። “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” ነው ያሉት?
ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው እኮ ቢያንስ እንደ ብሄር ራሳቸውን የሚገልጹበት ታእታይ የፖለቲካ ስብእና ባይኖራቸውም በመልክዓምድር በተወሰነ የፖለቲካ ታእታይ ስብእና የታጠሩና ለፈጠራቸው ህወሃት ኣድርባይ ናቸው። የህወሃት ኣባላትም እንዲሁ የፖለቲካ ውስጣዊ ወይም ታእታይ ሰውነታቸው በብሄር ላይ የቆመ ጠባብ ነው። በርግጥ “ኢህዓዴግ” የሚባለውን ለብሰናል ለማለት ከሆነ ህዝቡ ኣይዋጥለትም። ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት “ኢህዓዴግ” የሚባል ድርጅትም በዓለም ላይ የለም። ለምን የለም? ከተባለ ከማንነት ፖለቲካ ተፈጥሮ ጋር ያለውን ፍልስፍናዊውን ጉዳይ ልተወውና ኣንድ ጥቂት ተግባራዊ ነገር በማንሳት ላሳይ።
የዛሬ 40 ኣመት ገደማ ሁሉም እንደሚያውቀው ህወሃት ይቋቋማል።በዚህ ወቅት ህወሃት ሲፈጠር የነበረውን ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ውሎ ኣድሮ ያስባል። ወደዚያ የሚያደርሰው ኣድራሽ፣ ኣድራሽ ብቻ ሳይሆን እስከ ፈለገው ጊዜ እንዲቆይ፣ ጊዜ እንዲያገኝ የሚያደርገው፣ የሚያግዘው የፕሮጀክት ግብዓት ፈለገ። ጥሩ ኣድራሽና ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚሆነው የተለያዩ ብሄሮችን ስም የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶችን መፈልፈል ሆኖ ኣገኘው። በመሆኑም እንደ ኦህዴድ፣ ብዓዴን የመሳሰሉትን ሁሉ ፈለፈለ። እነዚህ ድርጅቶች የህዝብ ብሶት የወለዳቸው፣ ህዝብ የጠየቃቸው ኣይደሉም። ህወሃት ራሱ ለፕሮጀክቱ ግብዓት ይሆኑለት ዘንድ በኣምሳሉ የቀረጻቸው ናቸው። በሌላ ኣገላለጽ እነዚህ ድርጅቶች ራሳቸው ህወሃት ናቸው። ምንምን እንኳን የተለያየ ብሄር ኣባላትን ይዘው ቢመሰረቱም ተገትረው ብናይም በህወሃት ብሶት፣ በህወሃት ራእይ፣ በህወሃት እጅ የተፈጠሩ በህወሃት የህወሃት ናቸው። ኣንዳንዶቹ ድርጅቶች በተለይም ኦህዴድ እንደሚወራው ኣንዳንድ መሪዎቹ የህወሃት ኣባላት ስማቸውን እየቀየሩ ኣመራር ላይ የነበሩበት ሁኔታም ነበር።
ኣቶ በረከት ስምዖን በህወሃት 40 ዓመት ላይ ንግግር ሲያደርጉ እንዲህ ኣሉ
እኛ ብአዴኖችም ሁሌም ቢሆን ራሳችንን ከህወሓት ነጥለን ያየንበት ጊዜ የለም። ሁላችንም “ወየንቲ ኢና” (ወያኔዎች ነንነው የምንለው።” (በረከት ስምዖን)
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ቴድሮስ ኣድሃኖም ደግሞ ይህንን ያስረግጡልናል።
አንዳንድ ወገኖች …. ስድብ መስሏቸው “ወያኔ” አሉኝ ከጥቂት አመታት በፊት ለተመሳሳይ ጉዳይ በረከት ስምዖን ያለውን አስታወሱኝሁላችንም ወያኔ ነን” አዎ አሁንም ሁላችንም ወያኔን ነን…..እኔ ወያኔ ኢህአዴግ ነኝ! Je Suis Woyane!…. በዚህም ኩራት ይሰማኛል፡፡እኔ ወያኔ ነኝሁላችንም ወያኔ ነንይህን ችግር የሚፈታውም በወያኔነት ነው…እንበርታ፡፡” (ቴድሮስ ኣድሃኖም)
በኣንጻሩ ከህወሃት ኣባላት መንደር ሁላችንም ኦህዴድ ነን ወይም ደህዴግ ወይም ብዓዴን ለማለት ጨርሶ ታስቦ የማያውቅ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ድርጅቶች እንደ ፖለቲካ ድርጅት በህወሃት ህሊና የሉምና። እንዴውም ኣቶ መለስ እንኳን ከዚህ ቡድን ተወለድኩ ብለው ጠባብና ትምክህተኛነታቸውን በኣደባባይ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር። ይሄ ነው ጠባብነት፣ ትምክህትና ኣክራሪነት የሚባለው።
በኣጠቃላይ የሆነ ኣጀንዳ ይዞ የተነሳው ህወሃት ሲሆን በየመንገዱ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆኑትን የፖለቲካ ድርጅቶችን የፈለፈለ ሲሆን እነዚህን ግብዓቶች ይዞ ሁዋላ ላይ “ኢህዓዴግ” የሚል ስያሜ ይዞ ብቅ ይላል። “ኢህዓዴግ” የራሱ የህወሃት ፕሮጀክት ማስፈጽሚያ ሲሆን እንደ ፖለቲካ ድርጅት ግን ኣለ ማለት ኣይቻልም። ለዚህም ነው ራሱ በኣድራሽነት የተሰራውና የሚኖረውም። ግንባር በተፈጥሮው ኣድራሽ ሲሆን ይህ በግንባርነት የተዋቀረ ቤት የዚሁ የህወሃት ሌላው የኣዲስ ኣበባ ቤት ነው።
በርግጥ ወደ ተራው ኣባል ኣካባቢ ስናይ የዋህነት ሊኖር ይችላል። ተሰብስበው ግምገማ ሲባል፣ እቅድ ኣውጡ ኣውርዱ ሲባል “ኢህዓዴግ” በህይወት ያለ ይመስላቸው ይሆናል። የለም። ተላላ መሆን ኣያስፈልግም። ህወሃት እነዚህን ድርጅቶች ሲያቆም ኣዲስ ኣበባን ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ከዚያ በሁዋላ ደህንነቱንና ወታደሩን እንዲሁም ኢኮኖሚውን እስኪቆጣጠር ግብዓት ስለሚሆኑት ነው። በርግጥም በኣሁኑ ሰዓት በነዚህ ድርጅቶች እገዛ ህወሃት እነዚህን ህልሞቹን ኣሳክቷል። ኣቅጣጫ ነው ያጣው። በመሆኑም የነዚህ ድርጅቶች ኣባላት መታለሉን ማቆም ኣለባቸው። መንቃትና ለለውጥ መነሳት ያስፈልጋል። በቂምና በበቀል ላይ ሳይሆን ሁሉን ነጻ የሚያወጣ የወደፊቱን በማሰብ ላይ የተመሰረተ ቢሆን ነው የሚሻለው።
በኣጠቃላይ የሚንስትሮቻችን የመሪዎቻችን ታእታይ የፖለቲካ መሰረት የወንዝ ፖለቲካ በመሆኑ ከዚህ የብሄር ፖለቲካ ዘር የሚወለደው ያው ጠባብነትና ኣክራሪነት ከመሆን ኣያልፍም።ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ቴድሮስ ኣድሃኖም ከፍ ሲል እንዳየነው እኔ “Je Suis ወያኔ ነኝ” ብለዋል። ይሄ እውነተኛ የፖለቲካ መሰረታቸው ሊሆን ይችላል። የሚገርመው ግን እኚህ ሰው ኣንድ ጊዜ ኒዮርክ በተደረገ ስብሰባ ላይ “ ኒውዮርክ ሜልቲንግ ፖት ናት” ብለው በስሜት ተናገሩ። መልቲንግ ፖት የህወሃት ኣስተሳሰብ ጸር ነው። ባህላዊ ውህደት ማለት ነው ሜልቲንግ ፓት ማለት። እኚህ ሰው ምን ኣልባት ተለውጠው ከሆነ ይህን ያሉት እንዳንል የኒውዮርኩን ንግግር ካደረጉ በሁዋላ ነው እኔ “ Je Suis ወያኔ ነኝ” የሚሉን። እሳቸው ይህን ይበሉ ፣ እኔ ደግሞ Je Suis ኢትዮጵያዊ! እናንተስ?
እንግዲህ ጠቅላይ ሚንስትር ኣቶ ሃይለማርያም ይህን ዘር ኣጥፊ ነው ብለው ካመኑ በዚህ የወንዜ ፖለቲካ ቤት ውስጥ መዋል ማደር የለባቸውም። ሌሎች ምስጢሩ ያልገባቸው የዋህ የህወሃት፣ የብኣዴን፣የደህዴግ ወዘተ ኣባላት ከዚህ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ወጥተው ጠባብነትን የህወሃትን የበላይነት መዋጋት ኣለባቸው። የጠባብነትና የትምክህት ዋና የሆነውን የብሄር ፓለቲካ ቤት ግድግዳውንና ጣራውን ለመንደል የውስጥ ኣርበኞች መሆን ኣለባቸው። ለለውጥ መነሳት ኣለባቸው።የተባበረችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት ትውልዱ ሁሉ ኣምርሮ መነሳት ኣለበት።የተባበረችውን ኢትዮጵያን የምንገነባው ደግሞ ከብሄር ፖለቲካ ስንወጣ፣ ስምምነት ውስጥ ስንገባ ነው። ይህ ስምምነት የህዝብ ውክልና በሌላቸው በዚህ ኣርባ ኣመት ባፈራናቸው እዚህም እዚያም በተኮለኮሉ ፓርቲዎች መካከል ኣይደለም። ወደ ባህላዊ ቡድኖች ታች ድረስ ወርዶ ህዝቡ ተወያይቶ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሉን ኣዋጥቶ ኣገሩን እንዲገነባ የሚያደረግ ሰፊ ስምምነት ነው።ለዚህ ደግሞ ኣገሪቱ የሆነ የጽሞናና የሽግግር ጊዜ የሚያስፈልጋት ሲሆን በዚህ ከፍተኛ ኣሳብ ላይ ሁሉም መጠቅለል ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ህወሃት የዘራው ዘር ከፍተኛ ኣደጋ ውስጥ ሊጥለን ይችላል።
ኣዲሲቱ የተባበረችው ኢትዮጵያ ከብሄር ፖለቲካ ወጥታ በተሻለ ውቅር ልትሰራ ይገባል። የማንነት ኪሳራ እንዳይመጣብን በኣንድ በኩል የተደራጀ የባህል መንግስት መስርተን ባህላችንን እየተንከባከብንና እየተደሰትን በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ቤት መስራት እንችላለን። እንደ ኢትዮጵያ ብዙ መልካም ታሪክና ባህላዊ እሴቶች ያሉዋትን ኣገር ለማስተዳደር የዚህ ዓይነት ሲስተም መዘርጋቱ ሰላምን፣ ልማትና ዴሞክራሲን ያፋጥንልናል። ከዚህም በላይ ለዜጎች ርካታን ይሰጣል።
ከልጅነት ጊዜየ ጀምሮ በእድሜ የበሰሉ ሰዎች የሚሰጡት ትምህርት ይማርከኝ ነበር። ኣረጋውያን ሲያወሩ ጠጋ ብሎ ማዳመጥ ርካታን ይሰጠኛል። ከእለታት ኣንድ ቀን እንዲሁ ኣንድ የእድሜ ባለጸጋ ኣገኘሁና በተፈታ ስሜት ወግ ጀመርን። እኚህ ሰው ከሚናገሩት የሚበዛው ያለፈው ዘመን ምን ያህል የተሻለ እንደነበር ነው። ምን ኣልባት በኢኮኖሚ ጥንት የተሻሉ ነበሩ ማለት ነው፣ ኣሁን ኑሯቸው ኣሽቆልቁሏል ማለት ነው፣ ብየ እንዳላስብ ኣይደለም። ልጆቻቸው የተሻለ ገቢ ኣላቸው። እሳቸውም ድሃ የሚባሉ እንዳይደሉ ኣውቃለሁ። ምንድነው ወደ ኋላ የሚጎትታቸው? ምን ኣጥተው ነው? የሚል ጥያቄ ይዞኝ ነበር። በሳቸው የልጅነት ጊዜ በእግር ነበር ይጓዙ የነበሩት፣ ኣሁን በመኪና ይሄዳሉ፣ የተሻለ ልብስ ፣ የተሻለ ጫማ፣ የተሻለ ምግብ፣ የተሻለ ነገር…. እንዳላቸው መረዳት ችያለሁ። እኚህ ሰውም ይህንን ሁሉ ይደሰቱበታል። ይሁን እንጂ ያጡት ነገር ደግሞ ወደ ሁዋላ ሲጎትታቸው ኣየሁና ሁዋላ ላይ ለራሴ የተረዳሁት ነገር እኚህ ሰው ያጡት ባህል ነው ማለት ነው ብየ ደመደምኩ። በለውጥ ስም የሚወዱዋቸውን ባህሎቻቸውን ኣጥተዋል። ኣንቱ የተባሉ ሽማግሌዎችን ከሰፈራቸው ኣያዩም፣ ክብረ በዓላትን ሲያዩ ይገረማሉ፣ የጠፉ ባህላዊ ተቋማት ይናፍቋቸዋል፣ ወዘተ።
እኚህ ሰው ዘመናዊውን ዴሞክራቲክ የሆነ መንግስት ማየት ይፈልጋሉ። በርግጥ ደግሞ ባህላዊ ተቋሞቻቸው ቢያንስ ከነ ሙሉ ሃይላቸውም ባይሆን በቅርስነት በህይወት ማየት እንደሚፈልጉ ተማርኩ። እኚህ ሰው ኢትዮጵያን ቢወዱም ኣገራቸው የድሮ ሞገሷን የተገፈፈች ኣድርገው እንደሚያስቡ ገመትኩ። ርግጥ ነው ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ባህልን ማጣት እንደ ሃገርም እንደ ዜጋም ይከነክናል ይጎዳልም።ሌሎች የኢኮኖሚ ህይወታቸው እያደር እየደቀቀ የመጣ ሰዎችም እንዲሁ የድሮውን ጊዜ ሲናፍቁ ብዙ ጊዜ እሰማለሁ። ጥያቄያቸው ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ባህላቸውንም እንደናፈቁ መረዳት ይቻላል።
ለዚህ ነው ኣዲሲቱ ኢትዮጵያ የተደባለቀውን ፖለቲካዊ ማንነትና ባህላዊ ማንነት በመለየትና በተለያየ ቤት እንዲያድሩ በማድረግ የተሻለ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋታል የሚያስብለን ። የተባበረችውን ኢትዮጵያን የምንመሰርተውም እንዲህ በጠነከረ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት ላይ መሆን ኣለበት። ለዴሞክራሲ፣ ለለውጥ የምናደርገው ትግል ሁሉ Je Suis ኢትዮጵያ መርሃችን ኣድርገን የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገንባ። ኢትዮጵያውያን የተባበረችውን ኢትዮጵያን ገንብተን ትኩረታችንን ሁሉ በምግብ ዋስትና ላይ ልናደርግ ይገባናል። ተመልከቱ እስቲ። ኢትዮጵያ ባለፉት ኣስር ኣመታት ያለማቋረጥ በጥንድ ቁጥር እያደገች ነው ተባለ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ በምግብ በብሄራዊ ደረጃ ራሷን ቻለች ኣሉ።
እነሆ በማግስቱ ዛሬ በጥቂት ወራት ውስጥ ለ4.5 ሚሊዮን ህዝብ ኣስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋል ተባለ። የተባበሩት ህዝቦች ድርጅት የሰባዊ መብት ኣጋር ድርጅትና መንግስት ይህን ገልጸዋል። በእኔ እምነት ይህም ይፋ የሆነው በተባበሩት ህዝቦች ድርጅት ቅስቀሳ እንጂ መንግስት ይህ ነገር ወደ ኣደባባይ ሳይወጣ የሆነው ቢሆን የሚመርጥ ነው የሚመስለኝ። የሚገርመው ዛሬ በብሄራዊ ደረጃ ራሳችንን በምግብ ቻልን ያሉን ጠቅላይ ሚንስትር ለተራቡ ሰዎች ቀለብ ለመግዛት ከሚያስፈልገው ተጨማሪ $230 ሚሊዮን ውስጥ $33 ሚሊዮን የሚሆነውን ብቻ ነው መንግስት መሸፈን የሚችለው። ቀሪውን 200 ሚሊዮን ገደማ ዶላር ባስቸኳይ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ርዳታ እንዲያደርግ ልመና ጀምረናል። ይህ ማለት ደግሞ በምግብ በብሄራዊ ደረጃ ራሳችንን ኣልቻልንም ነበር ማለት ነው። ለብዙ ዓመታት በጥንድ ቁጥር ኣድጊያለሁ ዓለም ያጨብጭብልኝ ስትል የነበረች ኣገር ዛሬ ለጥቂት ወራት እንኳን ዜጎቿን መታደግ ኣልቻለችም። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብስ ምነው ዛሬ ጠዋት በምግብ ራሳችንን ቻልን ብልችሁ የለም እንዴ? ቢለን ……ያሳፍራል። ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች በውነት ኣጃንዳቸው ሁሉ ይህ ነው ሊሆን የሚገባው። ይህቺን ኣገር በምግብ ራስዋን የማስቻል ስራ ነው መቅደም ያለበት። ሰው በሚራብበት ኣገር የብሄር ፖለቲካ ቅብጥርሴ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። ለውጥና ሪፎርሜሽን ይመግበናል፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ይፈታልና ለለውጥ ታጥቀን እንነሳ።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
Source: goolgule

አዲሱ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት በይፋ ስራውን ጀመረ

አዲሱ የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት ዛሬ ጱግሜ 1/2007 ዓ.ም በይፋ ስራውን ጀምሯል፡፡ በዛሬው የአዲሱ ምክር ቤት ስብሰባ ነሃሴ 16ና 17/2007 ዓ.ም በተደረገው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አስመራጭ የነበረው ኮሚቴ የብሔራዊ ምክር ቤትን፣ የኢዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላትን ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በጠቅላላ ጉባኤው ምርጫ ከ1ኛ-50ኛ የተመረጡ አባላት እንደ ውጤታቸው 37ቱ ቋሚ እንዲሁም 13 ተለዋጭ አባላት ይፋ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም 5 የኦዲትና ምርመራ አባላትንም ይፋ አድርጓል፡፡
በተመሳሳይ አዲስ የተመረጠው የኦዲትና ምርመራ የአዲሱን ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አስመርጧል፡፡ ለሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢነት አቶ ይድነቃቸው ከበደ፣ አቶ አበበ አካሉና አቶ እስክንድር ጥላሁን የተወዳደሩ ሲሆን አቶ ይድነቃቸው ከበደ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆኖ ተመርጧል፡፡ በእስር ላይ የሚገኘው አቶ የሸዋስ አሰፋ ምክትል ሰብሳቢ ሆኖ ተመርጧል፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ መስከረም 9/2008 ዓ.ም በሚያደርገው ሁለተኛ ስብሰባው የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት አዲሱን ካቢኔያቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው ያፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

Friday, September 4, 2015

የኢህአዴግ ካድሬዎች መረጋጋት ተስኖአቸዋል

ነኅሴ ፳፰ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት የመስተዳድሩን ካድሬዎች ገምግሞ ለአብዛኞቹ ዝቅተኛ ነጥብ መስጠቱን ተከትሎ እና ከ4 ሺ በላይ ሰራተኞች በወንጀል እንደሚጠየቁ መነገሩን ተከትሎ፣ የመስተዳደሩ የኢህአዴግ አባላት ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ ገብተዋል። በዚህም የተነሳ መስተዳድሩ አገልግሎቶችን መስጠት አቁሟል በሚባልበት ደረጃ መድረሱን ምንቾች ገልጸዋል። "ምንም ስራ እየተሰራ አይደለም፣ ካደሬው በሙሉ ድንጋጤ ላይ ነው፣ ሹመትና ሽረቱን እየጠበቀነ ነው፣ በዚህም የተነሳ ስራ ቆሟል ብሎ መናገር ይቻላል" ሲል የመስተዳድሩ ሰራተኛ ተናግሯል። በርካታ ባለጉዳዮች እሮሮ እያሰሙ ቢሆንም፣ መፍትሄ የሚሰጥ አመራር በመጥፋቱ ፣ አዲስ ሹመት እስከሚሰጥ ድረስ ችግሩ ተባብሶ እንደሚቀጠል ምንጫችን ጠቅሷል። ኢህአዴግ አላማውን ደግፈው የሚታገሉ አባሎችን ለማግኘት እየተሳነው መምጣቱን በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ ገልጿል። አብዛኛው አባሎቹ አርሶ አደሮች መሆናቸውን የሚገልጸው ግንባሩ፣ ከአርሶ አደሩ ውጭ ያለው ደጋፊው አብዛኛው ለጥቅም ብሎ የቀረበው በመሆኑ፣ የድርጅቱን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል። ግንባሩ ከመሞቱ በፊት የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ መዘጋጀቱን ገልጿል። ምንም እንኳ ታች ያሉ በርካታ አባላት ሊባረሩ ወይም ወደ ተለያዩ ስራዎች ሊመደቡ ቢችልም፣ ቁልፍ ችግሩ ያለው ከዋና አመራሩና ከስርአቱ በመሆኑ ፣ ኢህአዴግ አሁን በሚወስደው እርምጃ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አይመጣም ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።

የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ

Understanding Dictators
የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ
ጂን ሻርፕ የአረቡ አለም አብዮት የሚባለውን እንዲቀጣጠል ነዳጅ ጨምሯል የተባለለትን ‹‹ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ››የተሰኘ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ መጽሐፍ ውስጥ አብዛኛዎቹ አስረጂ ምሳሌዎች አምባገነኖች መሰረታቸው ሕዝብ መሆኑን ነው የሚነግሩን፡፡ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በተደጋጋሚ ‹‹ጭቆና የሚሸከመው ትከሻ ይፈልጋል›› የሚሉን ይህንን ነው፡፡ አምባገነኖች ሕዝብ ጭቆና ለመሸከም ትከሻውን እንዲሰጣቸው ብዙ መንገዶቸን ይጠቀማሉ፡፡ የ‹ሠላማዊ ትግል 101› ጸሐፊ ግርማ ሞገስ ሶስት ነገሮችን የጠቅሳሉ፡- እነዚህም ፈቃደኝነት፣ ፍራቻ ወይም ግዴለሽነት ናቸው፡፡ የሚኪያቬሊ ፍልስፍናም (The Prince ላይ እንደተገለጠ) ‹‹ነገሥታት በመወደድ ብቻ ሳይሆን በመፈራትም ነው የሚኖሩት፡፡›› ከተቻለ ወዶ እና ፈቅዶ የሚተባበር፣ የሚታዘዝና ለምዶበት የሚታመንላቸውን፤ ይህ ሲከብድ ትልቅ ሠራዊት በመገንባት ወይም የደህንነት መረባቸው ትልቅ፣ ብልህ እና አስተማማኝ እንደሆነ በማስወራት ሕዝባቸውን እያስፈራሩ ትከሻው ላይ ይወጣሉ፡፡ ይህ ብቻውን ስላማያቆማቸው ያገኙትን ሞኝ ለማታለል ተቀባይነት የሚያስገኝላቸውን ዘዴም መዘየዳቸው አይቀርም፡፡
መንግሥታት ሥልጣን ላይ የሚቆዩት የተወሰነ ቅቡልነት (Legitimacy) እስካላቸው ድረስ ነው፡፡ የቀድሞ ነገሥታቶቻችን ራሳቸውን ‹‹ስዩመ እግዚአብሄር ›› በማለት ቅቡልነትን ለማግኘት ይጥሩ ነበር፡፡ ጳጳሳቱም (ሲሦ ቀላዳቸውን ለማግኘት) ይህንኑ ለሕዝቡ ይሰብኩ ነበር፡፡ ለአሁኖቹ መሪዎች ይህ አያዋጣም፡፡ ሕዋሓት የዘውግ ብሄርተኝነትን (ዕኩልነትን አስጠብቃለሁ በሚል ስም) ቅቡልነትን ሊገዛበት ሞክሮ ነበር፡፡ ብዙም አላስኬደውም፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ልማታዊነት›› የተባለውን ጨብጧል፡፡ ድሃ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች እንደሚያዘናጉት በመረዳት ‹‹መጀመሪያ ዳቦ›› እያለ እስከዚያው የመጨቆኛ ካርድ ለማግኘት ይጥራል፡፡ በዚህ አካሄድ ዊኒ ማንዴላ ተናግረውታል እንደሚባለው ‹‹ወፍራም ባሪያ›› መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡  

አባገነኖች፣ ልዩ ፍጡሮች?
አምባገነንነት የሚፈጠረው ሰዎች ያልተገደበ ስልጣን ሲገጥማቸው ራሳቸውን መግዛት ስለሚከብዳቸው ነው፡፡ ብዙዎች የዓለማችን አምባገነኖች መጀመሪያ ምስኪን ነፃ አውጪዎች ነበሩ፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን እንኳን ብንወስድ ዐፄነት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የድሀ አባት ነበሩ፤ ያውም ከበዝባዥ ፊውዳል ባለሀብቶች እየዘረፉ ለድሀ የሚያከፋፍሉ፡፡ ኋላ በትረ ሥልጣኑን ሲይዙ ግን በገዳይነት የሚወዳደራቸው አጡ፡፡  ‹‹የአገሬ ሕዝብ ስራት ያዝ ብለው እምቢ አለኝ›› እያሉ በስርዓት ማስያዝ ስም ሕዝቡን ፈጁት፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን ውስጣቸው የነበረው ቅንነት እየወቀሳቸው ‹‹አቤቱ አምላኬ፣ እባክህን ግደለኝ እና ሕዝብህን ነፃ አውጣ›› እስከማለት ደርሰው እንደነበር እንግሊዛዊ እስረኞቻቸው ጽፈዋል፡፡ሰዎች ሰላማዊነትን መምረጥ የሚኖርባቸው ከራሳቸው ድብቅ አውዳሚነት ራሳቸውን መጠበቅ ስለሚከብዳቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ- አምባገነንነት ባሕል ነው ማለት ይቻላል፡፡ አምባገነኖቻችን በቁልምጫ ነው የሚታወሱት፡፡ ‹‹መንጌ››ን መጥቀስ ይቻላል! አባወራዎች በቤተሰቡ ላይ ፍፁማዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ መምህራን በክፍል ተማሪዎቻቸው ላይ ፍፁም የበላይ ተደርገው ይሾማሉ፡፡ አለቆችም በምንዝሮቻቸው ላይ እንዲያው ናቸው፡፡ ሁሉም አቅሙ በፈቀደው ላይ ፍፁማዊ ኃይልን እና የበላይነትን መጠቀምን ባሕላችን ያበረታታል፡፡ ዘበኛው በደጅ ጠኚው ላይ፣ አሠሪው በሠራተኛዋ ላይ ኃያል ነው፡፡ ዕድሩ ስብሳቢው አይለወጥም፤ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ እስኪሞት አይሻርም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲው ሊቀመንበር አይቀየርም በዚህ ባሕል ውስጥ እየኖርን የአገር መሪ ብንቀያየርም ‹‹ተረኛ ጨቋኝ›› እንጂ ዴሞክራሲን አናመጣም፡፡

የአምባገነኖች አንድነት
አምባገነን አገር ወይም ብሔር የለውም፡፡ ቋንቋ የለውም፡፡ ሁሉም ያልሠለጠኑ ሕዝቦች ውስጥ ያለ ዕዳ ነው፡፡ አማር ቦንጎ ጋቦንን ለ42 ዓመታት ገዝቷል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎችን ለቤተዘመዱ አከፋፍሏል፡፡ ልጁ እሱ ሲሞት ሥልጣኑን ወርሷል፡፡ ሴት ልጁ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ነበረች፡፡ ባሏ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፡፡ በስሙ ያልተሰየመ ነገር የለም፤ ቦንጎ ዩኒቨርስቲ፣ ቦንጎ አየር ማረፊያ፣ ቦንጎ ሆስፒታል.... ሌላው ቀርቶ የትውልድ ከተማው ቦንጎቪል ተብላለች፡፡ እኛም አገር ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እስከ መለስ ዜናዊ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡
የኮትዲቯሩ ሆፎኤት-ቦይኚ 6 ጊዜ የፕሬዚዳንት ምርጫን አሸንፏል፡፡ ያውም 99.7 በመቶ አማካኝ ድምፅ አግኝቶ! የአንዱን አምባገንነት ታሪክ መስማት፣ የሌላኛውን እንደመስማት ነው፡፡
አምባገነኖች ሥራቸውን ልባቸው ስለሚያውቀው ይፈራሉ፡፡ የደህንነት ሠራተኞችም ፍርሐታቸውን ለማረጋጋት የውሸት መረጃ ይሰጧቸዋል፡፡ የዩጋንዳው ኢዲ አሚን ዳዳ ለምሳሌ ‹‹ሕዝቡ በፕሬዚዳንቱ ፍቅር አብዷል›› የሚል የደኅንነት ሪፖርት ደርሶት እንደነበር ተነግሯል፡፡  አሁን፣ አሁን የአገራችን ባለሥልጣኖችም በጋዜጣ መግለጫዎቻቸው የሚያሳዩት ባሕሪ እንዲህ ዓይነት ሪፖርት የደረሳቸው በሚመስል መልኩ ነው፡፡
የራሺያው የቦልሼቪኮች ፓርቲ (እ.ኤ.አ በ1917 ጀምሮ እስከ 1940 ብቻ) በ23 ዓመታት ውስጥ ከ24 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ የቀረው አንድ ጆሴፍ ስታሊን ብቻ ነበር፡፡ 8ቱ ተገደሉ፣ 7ቱ ‹‹በተፈጥሮ አጋጣሚ ሞቱ›› ተባለ፣ 7ቱ ‹‹የደረሱበት ጠፋ›› ተባለ፣ አንዱ ታሰረ፡፡ ቀሪው አንድ አምባገነን ብዙ ሚሊዮኖችን ፈጀ፡፡ ይህንን ስታሊኒስታዊ አመራር (ተቀናቃኞችን ማጥፋት) ከልባቸው ያሳደሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንደስታሊን ማዕከላዊ ኮሚቴውን ባዶ ከማድረግ ይልቅ ፣ ታዛዥ አላዋቂዎች እንዲሰበሰቡበት አደረጉ፡፡ ልዩነቱ ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን ሞት ቀደማቸው፡፡ የቀሩት አባላት የሚያደርጉት ጠፋቸው፡፡ ስለዚህ የሟቹን ሌጋሲ (‹‹ትሩፋት››) እናስቀጥላለን በማለት በመለስ የተሾሙለትን ዓላማ እያስፈፀሙ ነው፡፡

ምርጫ በአምባገነኖች አገር
በአምባገነኖች አገር ምርጫ ማለት አሸናፊውን (ገዢውን) አጅቦ ለድል ማብቃት ማለት ነው፡፡ ወይም አምባገነኖቹ የሚፈልጉት እንደዚያ እንዲሆን ነው፡፡ The Dictator የተሰኘው ፊልም ነገሩን ግልጽ አድርጎታል፡፡ ሳላዲን የተባለው የዋዲያ መሪ የራሱን ኦሎምፒክ አዘጋጅቶ፣ ራሱ ተወዳድሮ ያሽንፋል፡፡ ውድድሩን ተኩሶ የሚያስጀምረው ራሱ ነው፡፡ የሚቀድሙትን ተወዳዳሪዎች እየተኮሰ ይጥላቸዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ራሱ ያሸንፋል፡፡ ምርጫ ለአምባገነኖች እንዲህ ቀላል ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ አሸንፌ ድሌ ይከበርልኛል፡፡ ብለው ከሚያስቡ የሳላዲንን ሽጉጥ የጨበጠ እጅ ቢይዙ የተሻለ ያዋጣቸው ነበር፡፡ የአምባገነን መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአምባገነንነት መንግሥት እጅ መያዝ አለባቸው፡፡
አገዛዙ ወይም የአገዛዙ ልሒቃን በምን ጥገኛ እንደሆኑ መለየት እና ያንን መንፈግን እንደትግል መሣሪያ (መደራደሪያነት) መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የእኛ አምባገነኖች ተፎካካሪዎቻቸውን የሚጥሉት በየትኛው እጃቸው ነው? የኃይል ምንጫቸው ምንድን ነው? ሠላማዊ ትግሉ ሊሠራው የሚጠብቀው የቤት ሥራ ነው፡፡…ይቀጥላል፡፡



ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
የቀደሙት ጽሁፎች ‹‹ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? ፣ ሠላማዊ ትግል ስንል? እና   ‹‹ከሕወሓት መማር››  ማስፈንጠሪያዎቻቸውን በመጫን ማንበብ ይችላሉ፡፡

Source: Zone9

Thursday, September 3, 2015

በእስር ላይ የሚገኙ ሦስት የሰማያዊ አባላት በዓለም ላይ ከተመረጡ 20 የፖለቲካ እስረኞች መካከል ተካተቱ



በአሜሪካ መንግስት ኦፊሳላዊ ድረ ገጽ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አስተባባሪነት በዓለም ላይ ለተመረጡ 20 ሴት የፖለቲካ እስረኞች ለአንድ ወር የሚቆይ ዘመቻና ማስታወሻ ሊደረግላቸው ነው፡፡ ከ20ዎቹ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ሁሉም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡
ከዛሬ 20 አመት በፊት ሴቶችን ለማብቃት፣ የጾታ እኩልነትን ለማስፈን እና የልጃ ገረዶችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ የቤጂንግ መርሃ ጉዞ ተቀምጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእነዚህ 20 አመታት ልክ ከዓለም ሀገራት በፖለቲካ እስረኝነታቸው የተመረጡ 20 ሴት እስረኞችን ለማሰብ የሚደረገው ዘመቻ መነሻው ይህ መርሃ ጉዞ ነው፡፡
በዚህ መሰረት ከኢትዮጵያ ብሌን መስፍን፣ ንግስት ወንዲፍራው እና ሜሮን አለማየሁ የተካተቱ ሲሆን ከቻይና እንዲሁ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች ተመርጠው ይታወሳሉ፡፡ ከብዙ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል እነዚህ ጥቂቶች መሆናቸውን የጠቀሰው ድረ ገጹ በመስከረም ወር ‹‹ሴቶችን አብቋቸው፣ አትሰሯቸው!›› በሚል መርህ ዘመቻው ይደረጋል፡፡ በዚህም መንግስታት ሴቶችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ማሰር አቁመው ማብቃት ላይ እንዲያተኩሩ መልዕክት ይተላለፍበታል፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ ዘመቻው ለታሳሪ ቤተሰቦችና ለራሳቸው ለታሳሪዎች ብቻቸውን እንዳልሆኑና እንዳልተዘነጉ ለማሳየት ታስቦ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ በኢትዮጵያ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች በዚህ ደረጃ መጠቀሳቸው በሀገራችን ያለውን ስርዓት ዓለም እንደተረዳውና ኢትዮጵያ በመጥፎ እንድትነሳ እያደረጋት መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ 
ዘመቻው እንዲደረግላቸው ከተመረጡት መካከል ከኢትዮጵያና ቻይና ሶስት ሶስት፣ ከቬትናም፣ አዘርባጃንና በርማ ሁለት ሁለት እንዲሁም ከኢራን፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ቬንዞዌላ፣ ሶሪያ፣ ሩሲያ/ዩክሬንና ሰሜን ኮሪያ አንድ አንድ ሴት የህሊና እስረኞች ናቸው፡፡ 

ዘመቻው #FreeThe20 በሚል መለያ (ሀሽታግ) ይደረጋል፡፡

http://www.humanrights.gov/freethe20/

ከሕወሓት መማር

What to Learn From TPLF
እስከዚያው ከሕወሓት መማር
የሚቀናቀኑትን አካል በቅጡ መረዳት ግማሹን መንገድ መምጣት ነው፡፡ የሕወሓትን ታሪክ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ወዘተርፈ መለየት ለሠላማዊ ትግላችን ሰፊ አስተዋፆ ይኖረዋል፡፡
ትምህርት አንድ
ሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት በአውራ ፓርቲ ሥም፣ አሀዳዊ ፓርቲ ስርዓት እየዘረጋ ነው፡፡ መላ አገሪቱ ከቀበሌ እስከ ፓርላማ በአንድ አይነት አስተሳሰብ የተቃኙ፣ የአንድ ፓርቲ ሰዎች እንዲሞሉት አድርጓል፡፡ ይህ አመል ኢሕአዴግ የመንግስት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ የመጣ ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ሕወሓት ከቀድሞ ወዳጁ ሻዕቢያ የተማረው ‹‹በአንድ ሜዳ ሁለት ኃይል አይኖርም›› የሚል አባባል አለው፡፡ በዚህ ፍልስፍና ሻዕቢያ ጀብሃን አጠፋ፡፡ ሕወሓት ደግሞ ሕግሐኤ፣ ኢዴኃ (EDU)፣ ኢሕአሠን በኃይል ደምስሷል፡፡ ሕዋሓት ደርግን ከመደምሰሱ በፊት አምባገነኑን ደርግን እንወጋለን ብለው ግን ደግሞ ከሱ በጥቂቱ የተለየ የፖለቲካ ፍልስፍና ይዘው ከጎኑ የተሰለፉ ኃይሎችን አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህ የጫካ አመሉ ያደገበት ሕወሓት (ኢሕአዴግን ለብሶ) ከተማ ሲገባ የቱንም ያክል ‹‹ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው›› እያለ ቢፎክርም፣ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን መታገስ አልቻለም፡፡
ሕወሓት/ኢሕአዴግ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን ቀርቶ በውስጡ የሚከሰቱ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን እንኳን መታገስ አይችልም፡፡ ትግል ላይ በነበሩት ጊዜ የተነሳው የመጀመሪያው ሕንፍሽፍሽ (ቀውስ) ‹የአሽዓ (አክሱም፣ ሽረ እና አደዋ) ሰዎች የሥልጣን የበላይነት (ልክ አሁን የትግራይ ልሒቃን የሥልጣን የበላይነት በፌደራል መንግስቱ ውስጥ በዛ እንደምንለው) ፓርቲያችን ላይ እየታየ ነው› የሚል አቤቱታ ያቀረቡ አባላቱን በማስወገድ ነው የተጠናቀቀው፡፡ በ1993 በተፈጠረው ቀውስ ደግሞ የሉአላዊነት ጥያቄ ያነገቡ አባላቱን የውስጥ ሕገ-ደንቡን (ሕወሓትን በማዳን ስም) ሽሮ፣ ምርጫ ቦርድ ባለበት አገር በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ማሕተም የተፃፈ ደብዳቤ ነበር ያሰናበታቸው፡፡ ይሕ ባሕል ከጫካ ተከትሏቸው የመጣ ባሕል ነው፡፡ የውብማር አስፋው ‹ፊኒክሷ ሞታም ትነሳለች› ባለችው መጽሐፏ እንዲህ ትለናለች፡-
‹‹ሕወሓት ደንብ መሠረት አንጃ መፍጠር እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ያስከትል ስለነበር፣ የሕወሓት ፖሊት ቢሮ ይህንን ሲያስቀምጥ በማኅበሩ አመራር ውስጥ የማይፈልጋቸውና የሚጠላቸው የአመራር አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመለክት ነበር፡፡ . . . ›› (ገጽ 112፣ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ እንዳጣቀሰው)
እነዚህ ችግሮች ስር ሰደው ነው የአሁኑን አማራጭ ሐሳብ የማይቋቋም ኢሕአዴግ የፈጠሩት፡፡ ይህንን የ1993ቱ የሕወሓት ቀውስ ወቅት ከፓርቲው ከወጡት ታጋዮች መካከል አረጋሽ አዳነ ለጥሕሎ መጽሔት በሰጠችው ቃለምልልስ ከስር ከስሩ ባለመታረሙ የመጣ ጣጣ ነው በማለት ከታሪክ እንድንማር ትመክረናለች፡-
‹‹እነዚህ ሁሉ [ጥያቄዎችን በኃይል የመጨፍለቅ] ችግሮች ገና ድሮ ከመፈጠራቸው፣ [ስ]ር ከመስደዳቸው በፊት ቀደም ብለን ለዚህ ሁሉ መሰረት የሆኑትን ችግሮች . . . አስተውለን ከስር ከስር ወይም ደረጃ በደረጃ እየታገልናቸው ያለመምጣታችን አሉታዊ ፍፃሜ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡››
(ገጽ 77፣ ዮናስ በላይ፣ የትግራይ ሕዝብ፣ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ)
የቀድሞ የሕወሓት ታጋዮች ፀፀትም ሆነ የአሁን ታሪኩ የሚያስተምረን ዴሞክራሲ መንገድ እንጂ መዳረሻ አለመሆኑን ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያልመጣ ኃይል ዴሞክራሲን ሊያመጣ አይችልም፡፡

ትምህርት ሁለት
ሕወሓት ደርግን ወግቶ ለድል እንዲበቃ በተለይ ሁለት ዘዴዎች ረድተውታል፡፡ ሠላማዊ ታጋዮች እነዚህን ዘዴዎች በራሳቸው መንገድ ተርጉመው ሊጠቀሙበት የችላሉ፡፡ የመጀመሪያው ደርግን እራሱን መጠቀሚያ ማድረግ ነው፡፡  ሕወሓት የደርግን ክፋት ለራሱ ተቀባይነት መግዣ በማድረግ ተጠቅሟል፡፡ ለምሳሌ በትግል ወቅት የማረካቸው ወታደሮች ‹ተሃድሶ› ካሰለጠናቸው በኋላ ሁለት አማራጭ ይሰጣቸው ነበር፡፡ አንድ ከጎን ተሰልፈው ደርግን እንዲወጉ አልያም ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፡፡ የትኛውንም ቢመርጡ ሕዋሓት ያተርፋል፡፡ ተመላሾቹ የገጠማቸውን ለቀሪው ወታደር ስለሚናገሩ ወታደሩ በወኔ ለመዋጋት ይለግማል እነርሱም ተመልሰው ሕወሓትን አይወጉም፡፡ የደርግ አባል የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ደበላ ደንሳ ተመላሽ ‹‹ምርኮኞችን መልሶ ማዝመት›› ደርግን እንዲሸነፍ ያደረጉት ካሏቸው 13 ነጥቦች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ሠላማዊ ታጋዮች ተቀናቃኜ የሚሉትን አካል ከጎናቸው ማሰለፍ የሚችሉበትን ስልት መንደፍ አለባቸው፡፡ በሐሳብ በመብለጥ! የሕወሓት ወገን የነበሩ በመሆናቸው ብቻ በለውጡ እንደማይቀጡ ዋስትና ይፈልጋሉ፣ ሁለተኛ በለውጡ ሐሳብ መማረክ አለባቸው፡፡
ሁለተኛው የሕዋሓት ብልሐት ደርግን የሚዋጋበትን መሣሪያ ከራሱ ከደርግ ማግኘት መቻሉ ነው፡፡ የአሁን ሰላማዊ ታጋዮች ሕዋሓት (ኢሕአዴግን ለማሸነፍ ወይም በዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ስርዓት ለመተካት የራሱን መሳሪያዎች መጠቀም መቻል አለባቸው፡፡) ሕገ-መንግሥቱን፣ የመንግሥት መዋቅሮችን፣ የመንግሠት ሠራተኞችን፣ ወዘተርፈ ለሠላማዊው ትግል የሚፈይዱበትን ዘዴ መቀየስ ይበጃል፡፡

ትምህርት ሦስት
ሕወሓት ትግሉ ሕዝቡ ውስጥ ስር እንዲሰድ ከረዱት መንገዶች መካከል ሳይጠቀስ የማይታለፈው ኪነትን መጠቀም መቻሉ ነው፡፡ በተለይ በዘፈን ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በወኔ የሚቀሰቅሱ፣ ሕልም እንዲያልሙ የሚረዱ እና የራሳቸውን የዘመን ወግ (Folklore) መፍጠር የቻሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ‹ንገሪን እንደ ሐለፋይ . . . › የሚለው (በትርጉሙ ‹‹ንገሪኝ እስቲ እናቴ፣ ወዴት ነው የሄደው አባቴ?›› የሚል) የማሚት እና ብርሃነ (ሐለፋይ) የቅብብሎሽ (duet) ዘፈን፣ አሳዛኝ እና የተከፈለው መስዋዕትነት ለሚመጥነው ዋጋ መሆኑን የሚዘክር ዘፈን ነው፡፡ ይህንን ዘፈን ትግሪኛ ተናጋሪ ጓደኞቼን ‹‹ንገሪኝ እስኪ እናቴ፣ ለዚህ ነበር ወይ የሞተው አባቴ?› በሚል ምፀት እንዲቀይሩት ጠይቄያቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ . . . ጥበብ (ኪነ ጥበብ ይሁን ሥነ ጥበብ) በጥቅሉ ከአመፃዊ ይልቅ ለሠላማዊ ትግል መሣሪያ መሆን የችላል፡፡ በዚህ ረገድ በዓለማችን ብዙ ትምህርት የሚሆኑ ሥራዎችን አይተናል፡፡ የማርያ ማኬባ ፀረ-አፓርታይድ ዜማዎች፣ የቦብ ማርሌይ የነፃነት ሬጌምቶች፣ . . . እና በአገራችንም የቴዲ አፍሮ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ከነዚሁ ተርታ ይመደባል፡፡ የቀድሞዎቹን የጦር ሽለላዎችና ቀረርቶዎች በመጠቀም ያውም ለዚህ ትውልድ ጆሮ በሚስብ መልኩ በሂፕሆፕ (ራፕ) መልኩ፣ የለውጥ ሰባኪ ግጥሞች ተጽፈውለት መሥራት ይቻላል፡፡ ኬናን የተባለ ካናዳ-ሶማሊያዊ ራፐር ይህንን አሳይቷል፡፡
በጥበብ ረገድ የሚደረጉ ሠላማዊ ተጋድሎዎች በዘፈን ብቻ ሊገደቡ አይገባም፡፡ በሥዕል፣ በሥነፅሁፍ፣ በቲያትር፣ ፊልም፣ ካርቱኖች እና ሌሎችም አማራጮች ቀርበው ሁሉንም እንደየፍላጎቱ ሊደርሱት ይገባል፡፡

…ይቀጥላል፡፡

ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

Tuesday, September 1, 2015

የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ከጠቅላላ ጉባኤው ሲመለሱ ተደበደቡ

‹‹የደበደበኝና የዘረፈኝ ሰው ተለቆ እኔ ታስሬያለሁ›› አቶ ጌትነት በሱፍቃድ
በወላይታ ዞን ቦሎቶሶሬ ወረዳ አረካ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ጌትነት በሱፍቃድ ተደብድበው ንብረቶቻቸውን መዘረፋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በምርጫው ወቅት ቅስቀሳ ላይ እያሉም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ተመሳሳይ ወንጀል ተፈፅሞባቸው እንደነበር የገለፁት አቶ ጌትነት ‹‹በምርጫው ወቅት ቅስቀሳ ላይ እያለሁ በካድሬዎች ተደብድቤ ንብረቴን ተቀምቻለሁ፡፡ ሌሎች የትግል ጓደኞቼም ተመሳሳይ ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ሆኖም ከፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ እስከ ከንቲባው ፅ/ቤት ድረስ በመሄድ አቤቱታ ብናቀርብም የሚሰማን አላገኘንም፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በቦሎቶሶሬ ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጌትነት በሱፍቃድ ከሰማያዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፈው ከተመለሱ በኋላ ነሃሴ 20/2007 ዓ.ም በአረካ ከተማ ተመሳሳይ ወንጀል እንደተፈፀመባቸው ገልጸዋል፡፡ ደብድቦ ስልካቸውንና የአንገት ሀብላቸውን የቀማቸው ሰው እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ ስልካቸው በፖሊስ እንደተመለሰላቸው የገለፁት አቶ ጌትነት እሳቸው ታስረው እስከ ሌሊቱ 5 ሰዓት ሲቆዩ ወንጀሉን የፈፀመው ሰው ወዲያውኑ መለቀቁን ገልጸዋል፡፡
‹‹የደበደበኝና የዘረፈኝ ሰው ተለቆ እኔ ታስሬያለሁ፡፡ የደበደበኝ ሰው ካድሬ ነው፡፡ ጭራሹን ለፖሊስ ለመክሰስ በሄድኩበት ወቅት ‹እሱም ሊከስህ ስለሆነ አንተም መክሰስ የለብህም፡፡ እንዳትካሰሱ ብለን መዝገቡን ዘግተነዋል› ብለው መልሰውኛል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ በሆነው አረካ ከተማ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚፈፀም በተደጋጋሚ የሚገለፅ ሲሆን አቶ ጌትነትም ‹‹የሚደርሰው በደል ከፍተኛ ነው፡፡ ባለፈውም ለተፈፀመብን አሁንም ለተፈፀመብኝ ወንጀል መፍትሄ አልተሰጠኝም፡፡ ለአንድ ሰው ካድሬዎች በመንጋ መጥተው ነው የሚያጠቁህ፡፡ አቤት የምትልበት አካል የለም›› ሲሉ ገልጸውልናል፡፡