Thursday, March 31, 2016

የነጻነት ዋጋ - አቤል ዋልባ (ከዞን ዘጠኝ አንዱ)

ይህ የአእምሮ ጨዋታ አርነት የወጣች ነፍስ ላላቸው ወይም ነፍሳቸው አርነት እንድትወጣ በመፈለግ በታላቅ ፍርሃት እና መራድ ውስጥ ለሚገኙ እና በህይወታቸው ምክንያታዊ ውሳኔን ማሳለፍ ጥረት ለሚያደርጉ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ይህንን ትግል የሚያደርጉ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት አሊያም በማኀበረሰባዊ ተጽዕኖ ምክንያት ሂሳባዊ ስሌት ይሰራሉ፡፡ ይህ የማደርገው ነገር የሚያመጣብኝ ችግር መከራውን ተቀብዬ ከማገኘው ጥቅም አንጻር ሲመዘን ያዋጣኛል? ብዙዎች እንደሚያደርጉት ራሴን በተፈቀደለኝ መጠን ማኖር፣ ማዝናናት አይሻለኝምን? ይህን የነጻነት ድርጊት/ዐሳብ፣ ብፈጽም/ ባስብ በዚህ ምክንያት የምቀበለው እንክርት እና እንግልት ተገቢ ነውን? ትንሽ ራስን ከማሰቃየት የሚገኝ ደስታን ፈላጊ(ሳዲስት) አልሆንኩም? የመሳሰሉት ጥያቄዎች በሰልፍ ወደ አእምሮ ይመጣሉ፡፡ Selfless እንዳልሆንን ስለምናውቀው የእነዚህ ጥያቄዎች አግባብነት ጮክ ብሎ ይሰማናል፡፡ ወላጆቻችን ያወረሱን “የሚያልፍ ዝናብ አይመታህ” የሚለው ምርቃት ያቃጭልብናል፡፡ ይሄ ነጻነት የሚሉት ነገር አዋጭ ነው ወይ?
ይህ መልሱ ቀላል እና አጭር ነው፡፡ ብዙዎችን በሩቅም በቅርብም ሆነው ይህንን ስሌት በማደረግ እንደነጋዴ ሲመትሩ የሚደረስባቸውን ችግር ለማሳነስ ነጻነትን በማድረግ እና ባለማደረግ መሀል ሲዋልሉ ተመልክቻለው፡፡ ይህ ፍርሃታቸውን አሸንፈው የከፈሉትን መስዋዕትነት እንኳን በዜሮ የሚያባዛ ነው፡፡ ‘ሞኝ አትሁን’ የሚል የወዳጅ የዘመድ ምክር የሚጠይቅም አይደለም፡፡ነጻነትን ማከናወን ብዙ ጊዜ የሚጠናቀቀው በኪሳራ ነው ፡፡ ነገር ግን ነጻነትን መከወን ምርጫ ነው፡፡ ነጻነትን ማድረግ ገቢ የሌለው ክፍያ ነው፡፡ ለቀጣይ ትውልዶች እየተባሉ ነገሮች በኃላፊነት መደረጋቸውን ብድግፍም የእኔ ትውልድ ፍትሓዊ ጥቅም የማያገኝበት ነገ ስሜት ስለማይሰጠኝ ስምን ከመቃብር በላይ የማኖር አስፈላጊነትን መረዳት ይከብደኛል፡፡
ስለዚህ ነጻነትን የምናደርገው እና የምንኖረው ስለሚያዋጣን ሳይሆን ልክ ስለሆነ ነው፡፡ ነጻነት ትክክለኛ ነው ስለዚህ እንኖረዋለን፤ እናደርገዋለን፡፡ የሰው ልጆች ታሪክም የሚነገረን ይህነን ነው፡፡ ልክ የሆነውን ነጻነት በማድረጋቸው ብቻ ተነግሮ የማያልቅ ግፍን የተቀበሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ የነጻነት ዋጋው ለሚያምኑበት ነገር መከራን መቀበል ነው፡፡ ይህ የምድሪቱ በረከት ነው፡፡ የሀገሬ ሰው ‘ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል’ እንደሚለው ሳይሆን ሰው ለሚያምንበት ልክ ነገር ዋጋ ይከፍላል፡፡

No comments: