የሃይማኖት ተቋማትን በሚመለከተው አዋጅ ላይ የሚመክር ስብሰባ በአዋሳ ተጠራ
ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም :-በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀው የእምነት አኩልነትና ተቻችሎ የመኖር የሃይማኖት እሴትን ሊያጎለብት ይችላል የተባለ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሚመለከታቸውን ወገኖች ሃሳብ ለማሰባሰብ ከነገ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ምንጮቻችን ጠቆሙ።
በዚሁ ስብሰባ ላይ በዋንኛነት የሚሳተፉት በአገሪቱ አሉ የሚባሉት 945 ያህል የእምነት ተቋማት መሆናቸውም ታውቆአል፡፡ መንግስት የሙስሊም ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ ለውይይት በተደጋጋሚ ሲያገኛቸው የነበሩትን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮምቴ አባላት በአክራሪነትና በሽብርተኝነት ወንጅሎ እስር ቤት ከከተተ ወዲህ “መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፣አንዱ በሌላው ስራ ጣልቃ አይገባም” የሚለውን ሕገመንግስታዊ ድንጋጌ በመዘንጋት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ሙሉ በሙሉ ማስገባቱን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡
መንግስት ረቂቅ ህጉ በሃይማኖት ስም ይደረጋሉ የሚላቸውን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ይስችለኛል ብሎ ያምናል። የሃማኖት ተቁዋማቱ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ ባለፈ የረቂቅ አዋጁ ኮፒ አስቀድሞ እንዲደርሳቸው እንዳልተደረገ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የሕግ ሰውነትን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ የተደነገገው በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አቋቁሞ፣ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ሕጉን ተከትሎ በሚወጣ ልዩ ደንብ እንደሚመዘገቡ መደንገጉ ይታወቃል፡፡ በደርግ ዘመንም ሃይማኖትን የተመለከተ ድንጋጌ ወጥቶ አያውቅም።
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ያወጣው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 27 ላይ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣የህሊናና የሃይማኖት ነጻነት እንዳለው በግልጽ ደነግጋል፡፡ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም መቀበል ፣ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣የመከተል፣የመተግበር፣የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ከዚህ በተጨማሪም የሃማኖት ተከታዮች ሃማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችላቸውን የሃማኖት ትምህርትና የአስተዳዳር ተቋማት ማቋቋም እንደሚችሉና ወላጆች ህጋዊ ሞግዚቶች በእምነታቸው መሰረት የሃይማኖታዊና የመልካም ስነምግባር ትምህርት በመስጠት ልጆቻቸው የማሳደግ መብት እንዳላቸው ደንግጓል።
No comments:
Post a Comment