Saturday, July 13, 2013

የተክለሀይማኖት አስተዳደርና ምዕመናን እየተወዛገቡ ነው

የተክለሀይማኖት አስተዳደርና ምዕመናን እየተወዛገቡ ነው


የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ጊዜያዊ የልማት ግንባታ፤ በአስተዳደሩ፣ በምዕመናኑና በሠንበት ት/ቤቱ መካከል ውዝግብ አስነሳ፡፡ ቤተክርስቲያኑ በዋናው አስፋልት መንገድ በኩል ከ12-20 የሚደርስ ህንፃ ሰርቶ እንዲጠቀም ቢፈቀድለትም ዋናውን ግንባታ ለመጀመር አቅሙ ስለማይፈቅድ ጊዜያዊ ገቢ ማስገኛ ሱቆች ተሠርተው ቤተክርስቲያኑ እንዲጠቀም የተወሠነው ውሳኔ ለውዝግቡ መነሻ እንደሆነ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ጊዜያዊ ልማቱን ቤተክርስቲያኑ ባለው በጀት ሠርቶ መጠቀም እየቻለ፣ በደብሩ አስተዳደርና ዋና ፀሀፊ የውስጥ ለውስጥ ድርድር ለአንድ ባለሃብት መሠጠቱን በመቃወማችን ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰብን ነው ብለዋል - ምዕመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች፡፡ “የደብሩ አስተዳደርና ዋና ፀሀፊው ከባለ ሀብቱ ጋር በመደራደር አንድ ትልቅ መጋዘንና 10 ሱቆችን ለራሱ፣ ሌሎች 10 ሱቆችን ለቤተክርስቲያኑ ሠርቶ ሊያስረክብ እንዲሁም ለራሱ የሠራውን ለ10 ዓመታት በነፃ ሊጠቀም መዋዋላቸው አግባብ አይደለም” ሲሉ ምዕመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡
ጊዜያዊ ልማቱን ግለሠብ ይስራው ከተባለም ጨረታ ወጥቶና በግልፅ ተፎካክሮ እንጂ ቤተክርስቲያኑ የሚመራበት ሠበካ ጉባኤ ሳይወስን በግለሠቦች ድርድር ሊሆን እንደማይገባ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡ አሁን ከስራቸው በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁት የሠበካ ጉባኤው አባላት፤ በመጀመሪያ ጉዳዩ ተድበስብሶ ስለቀረበላቸው አምነውበት እንደነበር፣ ነገር ግን የተቃዋሚው ምዕመናንና የሠንበት ት/ቤቱ ተወካዮች ቁጥር እየበዛ በመሄዱ ጉዳዩን እንደገና በመመርመር አካሄዱ ችግር እንዳለው በተደጋጋሚ ለደብሩ አስተዳደር ማስረዳታቸውን በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው አስፍረዋል፡፡የደብሩ ዋና ፀሀፊ ሊቀ ህሩያን ሲሳይ ገ/ማሪያም በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ውስጥ ለውስጥ የተካሄደ ነው መባሉ ሀሰት መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩን ተስማምተው ከፈረሙት ዘጠኝ የቤተክርስቲያኒቱ የሠንበት ት/ቤት ተወካዮች፣ ምዕመናንና የአስተዳደር አካላት ውስጥ አሁን ስራ የለቀቁት የሠበካ ጉባኤ አባላት ፊርማ ያለበትን ቃለ ጉባኤ በማቅረብ ጉዳዩ ታምኖበትና ሥምምነት ላይ ተደርሶ የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡
ዋና ፀሀፊው አክለውም፤ ቃለ ጉባኤው ሲፈረም ከማህበረ ካህናት አራት ሠዎች፣ ከምዕመናን ሶስት፣ የደብሩ አስተዳዳሪና ዋና ፀሀፊው በድምሩ ዘጠኝ ሠዎች የተስማሙበት እንደሆነ ተናግረዋል። ቤተክርስቲያኑ ባለው ገንዘብ ጊዜያዊ ልማቱን ማሠራት ይችላል መባሉንና ያለ ጨረታ ለምን ለግለሠብ ግንባታው እንደተሠጠ ጠይቀናቸው ዋና ፀሀፊው ሲመልሱ፤ “በግል ጥቅም ምክንያት ለግለሠብ ሠጡ የተባለውን እቃወማለሁ፤ ጨረታን በተመለከተም ባዶ መሬት ላይ መጥታችሁ እንዲህ አድርጉ ይህን ስሩ ማለት አንችልም። ምክንያቱም መሬት የመንግስት ነው” ብለዋል፡፡ በመሆኑም ጉባኤው በተሠጠው ስልጣን መሠረት የተፈቀደውን ህንፃ እስክንጀምር ድረስ ጊዜያዊ ሱቆች ለማሰራት ተወስኗል ብለዋል፡፡ ዋና ፀሀፊው ይህን ይበሉ እንጂ ቅሬታ አቅራቢዎች ጉዳዩ አስጊ ሁኔታ ላይ በመሆኑ ጉዳዩን ለምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፅህፈት ቤት ያቀረቡት ሲሆን ፅ/ቤቱም ለደብረ አሚን ተክለሀይማኖት ቤ/ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ፣ የልማት ስራው እስኪጣራ ድረስ ሁሉም እንቅስቃሴ እንዲቆምና ከስራ የለቀቁት የሰበካ ጉባኤው አባላት ወደ ስራ እንዲመለሱ አዟል፡፡
በቤ/ክርስቲያኑ ውስጥ ሙስና እንደሚፈፀም የገለፁት ምዕመናኑ፤ “ለክ/ከተማ እና ለማዘጋጃ ቤት ማግባቢያ የሚውል 50ሺህ ብር ያለ ደረሠኝ እንዲወጣ ትዕዛዝ የተላለፈበት ደብዳቤ እንዳለ ጠቅሰው ይሄም በደብሩ የተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አሠራር ያሳያል” ብለዋል፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ ኤርሚያስ ወ/ኢየሱስን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባይሳካም የደብሩ ዋና ፀሐፊ ሊቀህሩያን ሲሳይ፤ ገንዘቡ የወጣበት ደብዳቤ በደብሩ አስተዳዳሪ ያልተፃፈና በሰዎች ተጭበርብረው የፈረሙት መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ በፖሊስ ምርመራ እየደረገበት እንደሆነ ገልፀዋል። ምዕመናኑ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ለምዕራብ አዱ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ቀርቦና ተረጋግጦ የሀገረ ስብከት ፅ/ቤቱ ገንዘቡ የወጣው ከህግና ደንብ ውጭ በመሆኑ፣ በአስቸኳይ ወደ ባንክ እንዲገባ ለደብሩ አስተዳደር በደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment