Friday, April 3, 2015

EPRDF's human rights abuse against the main oppostion, Blue Party

EPRDF's human rights abuse against the main oppostion, Blue Party increases as the 2015 elections gets closer. 
Mr. Solomon Tadesse, a talented young Blue Party election candidate from Debretabor was severely arbitrary beaten up by the government forces.



በደ/ታቦር ከተማ አሁንም አፈናዉ እንደቀጠለ ነዉ።በነመቶ አለቃ ፈንቲ ትእዛዝ ከምሽቱ ሶስት ሰአት ቁጥራቸዉ አስር የሚሆኑ ፖሊሶችና ቁጥራቸዉ ያልታወቀ ሚሊሻዎች የደ/ጎ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ፀሀፊና የፋርጣ ሁለት የተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ ሰለሞን ታደሰ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፀመ። ሰለሞን ታደሰ ሰማያዊ ፓርቲ ካፈራቸዉ ምርጥ ወጣቶች አንዱ ሲሆን ለወያኔ የእግር እሳት በመሆን በአደባባይና በህዝባዊ ስብሰባዎች የገዥዉን አፈና ያለ ምንም መሸማቀቅ ያጋለጠና በወጣቱ ዘንድ ድጋፍና አድናቆት ያለዉ ወጣት ነዉ።ይህ ወጣት ከአንድነት ጀምሮ በተለያዩ ወረዳዎችና እንዲሁም በእግሩ በመጉዋዝ በየ ቀበሌዉ ወጣቱን ሲያደራጅ የቆየ ነዉ።ሰሞኑን ሰማያዊ ፓርቲ ባደረገዉ ሰልፍ ከፍተኛ አስተዋፆ አበርክቷል።ይህን የቁርጥ ቀን ጀግና ወጣት ሆድ አደር ባለ ድርሻ አካላት መገደል እንዳለበት የወሰኑ መሆኑን ምንጮች የገለፁ ሲሆን ወጣቱ ባሰማዉ የድረሱልኝ ጥሪ ህዝቡ ሲወጣባቸዉ አንገለዉም ህግ አቅርቡ ብሎን ነዉ በማለት እስር ቤት ወሰዱት።ሌሊቱን በሙሉ ሲደበድቡት አድረዉ በአካሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ እስኪ ሰማያዊ ያድንህ በማለት ሲሳለቁበት እንዳደሩ ከወጣቱ አንደበት እና ከታሰሩ ሰዎች ለማወቅ ተችሏል። አሁን በመቶ አለቃ ፈንቲ አማካኝነት ከጧቱ አራት ሰአት ምንም አይነት ዋስና ክስ ሳይከሰስ እንዲፈታ ተደርጉዋል። ሸር በማድረግ ለሁሉም ይድረስ

ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የንግድ ድርጅቶች ጀርባ እየተፈጸመ ያለው ሙስና -ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የት እንደገባ አይታወቅም።

ከድርጅቶቹ ጀርባ እነማን አሉ?
መጋቢት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ከታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጠው በቦሌ አየር ማረፊያ በሚስጢር ስም የተመዘገቡና ባለቤታቸው ተለይቶ ያልተመዘገቡ ድርጅቶች ካለፉት 10 አመታት ጀምሮ የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያድሱ እና የቤት ኪራይ ክፍያቸውን ለመንግስት ገቢ ሳያደርጉ በመነገድ ላይ ናቸው።
በእነዚህ ድርጅቶች ጀርባ የከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ እንዳለበትም ምንጮች ጠቁመዋል።
የኤርፖርቶች ድርጅት ፣ተከራዮችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚል ምክንያት በየካቲት 1999 ዓም ላይ ኤሮኔቲካል ያልሆኑ የገቢ ምንጮችን ለማስተዳደር የሚል መመሪያ ያወጣ ሲሆን፣ በመመሪያው መሰረት ተከራዮቹ በየአምስት አመቱ በግልጽ ጨረታ እንደገና መወዳደር ይጠበቅባቸው ነበር።
ይሁን እንጅ ከእነዚህ መካከል፣8ት ባለቤታቸው የማይታወቅ በኮድ ስም የተመዘገቡ ድርጅቶችን ጨምሮ 15 የንግድ ድርጅቶች የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያድሱ ፣ የሚከፍሉት ወርሃዊ ክፍያ የት እንደገባ ሳይታወቅ ገንዘቡ በባለስልጣናት መበላቱን ምንጮች ጠቁመዋል።
ድርጅቶቹ በ1995 ዓም የኮንትራት ውል የፈረሙ ቢሆንም ፣ በ1999 ዓም በወጣው መመሪያ መሰረት እንደገና አለመመዝገባቸውን፣ ድርጅቶቹን ደፍሮ እንዲመዘገቡ የሚያደርግ አካል መጥፋቱን ምንጮች አክለዋል።
-በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 02 የተመዘገበው ድርጅት፣ የህትመት ውጤቶችን ለመሸጥ በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ተመን 54 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ክፍል ተከራይቶ የሚገኝ ሲሆን፣ በአመት 437 ሺ 400 ብር የኪራይ መጠን- የአስር አመት ጠቅላላ ክፍያ 4 ሚሊዮን 374 ሺ ብር የት እንደገባ አይታወቅም።
-በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 07”Cultural Cuisine” በሚል የይዞታ አይነት የተመዘገበው ድርጅት በአመት በካሬ ሜትር 5 ሺ 220 ብር ተመን 54 ካሬ ሜትር ቦታ ቢወስድም፤ የ10 አመታት የኪራይ ክፍያ 2 ሚሊዮን 818 ሺ 800 ብር የት እንደገባ አይታወቅም።
-በተርሚናል ቁጥር 2 ለሻንጣ ማሸጊያ በሚል በኮድ ቁጥር AACS 22 የተመዘገበ ድርጅት ለ12 ካሬ ሜትር በአመት በካሬ ሜትር 4 ሺ 100 ሂሳብ - በአስር አመት 492 ሺ ብር ለመክፈል ቢዋዋልም፤ ክፍያው የት እንደገባ አልታወቀም።
-በተርሚናል 2 በኮድ ቁጥር AARS 12 ለካውንተር ሰርቪስ አገልግሎት ተመዝግቦ የሚገኘው ድርጅት በካሬ ሜትር በአመት 4 ፣ 100 ብር ለመክፈል ተስማምቶ 141.31 ካሬ ሜትር ቦታ ቢወስድም፤የ10 አመታት በአጠቃላይ ክፍያ 5 ሚሊዮን 793 ሺ 710 ብር የት እንደገባ አይታወቅም።
-ተርሚናል በኮድ ቁጥር AACS 09 የተመዘገበው የወርቅና ጌጣጌጦች ሱቅ ፤ለያዘው 31.10 ካሬ ሜትር ቦታ በአመት በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ሂሳብ -አጠቃላይ የአስር አመት 2 ሚሊዮን 519 ሺ 100 ብር ክፍያ የት እንደገባ አልታወቀም።
-በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 21 ለአበባ መሸጫነት የተከራየው በ25.9 ካሬ ሜትር የሰፈረው ቦታ በአመት በካሬ ሜትር 4 ሺ 100 ብር የሚከፈልበት ቢሆንም፤ የ10 አመታት አመታዊ ክፍያው 1 ሚሊዮን 61 ሺ 900 ብር የት እንደገባ አይታወቅም።
-በተርሚናል ቁጥር AACS 06 የይዞታዉ መጠን 31.10 ካሬ ሜትር ለብር ጌጣጌጥ/Silver Shop/ የሚውለው መደብር በአመት በካሬሜትር 8 ሺ 100.00 ብር የተከራዬ ቢሆንም፤ የአስር አመታት ኪራይ 2 ሚሊዮን 519 ሺ 100 ብር ክፍያ የት እንደገባ አይታወቅም።
-በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 16 ለሱፐር ማርኬት የተከራየውና በ 33.4 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሰፈረው መደብር በአመት 8 ሺ 100 ብር የሚከፈልበት ቢሆንም፤ የ አስር ዓመት ክፍያው 2 ሚሊዮን 700 ሺ ብር ከ40 ሳንቲም እንዲሁ የት እንደገባ አይታወቅም።
እነዚህን ድርጅቶች በባለቤትነት የሚያስተዳድሩዋቸው ሰዎች በግልጽ ባይታወቁም፦ የዜንስው ምንጮች፦ ” በህግ የማይጠየቁ የተወሰኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘመዶችና ቤተሰቦች ናቸው” ይላሉ።
በስማቸው ተመዝገበው የሚገኙት የንግድ ድርጅቶችም በአዲሱ መመሪያ መሰረት ውል ሳይገቡ በመነገድ ላይ ሲሆኑ፤ የሚከፍሉት ክፍያ ከወቅቱ ጋር የማይመጣጠንና ተቆጣጣሪ የሌለባቸው መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በአዲሱ ውል መሰረት ውል ሳይዋዋሉ ለ5 አመታት ያክል በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በመነገድ ላይ ካሉት ድርጅቶች መካከል፦
- ለንደን ካፌና ሳተላይት ሬስቶራንት- 109.9 ካሬ ቦታ በአመት ብር 138 ሺ 474
- አልፋራጅ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፣ የይዞታ መጠን 631 ካሬ ሜትር፣ አመታዊ ክፍያ በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር
- ላሊበላ ወርቅ ቤት፣ 31.10 ካሬ ሜትር፣ አመታዊ የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር
-ሲቲ ቢዝነስ ኮምፒዩተር ፣ 104 ካሬ ሜትር -አመታዊ የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር
-ድሬ ኢንዱስትሪ ሃ/የተወሰነ የግል ማህበር 54 ካሬ ሜትር አመታዊ የክፍያ መጠን በሄክታር 8 ሺ 100
- ህይወት ለማ ትሬዲንግ 31.10 ካሬ ሜትር የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር
ሲማት ትሬዲንግ 31.10 ካሬ ሜትር የክፍያ መጠኑ ባከሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ይገኙበታል።
በአጠቃላይ አዲስ በወጣው መመሪያ መሰረት ህጋዊ ውል ሳይፈርሙ በመስራት ላይ የሚገኙት ድርጅቶች የ10 አመታት የኪራይ ዋጋ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ኤርፖርቶች ድርጅት እስካሁን እርምጃ ለመውሰድ አለመድፈሩን ምንጮች ገልጸዋል።
ጉዳዩ በተደጋጋሚ ለድርጅቱ ቢቀርብም ምላሽ መጥፋቱን ምንጮች አክለው ይገልጻሉ። በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ኤርፖርት ኢንተርፕራይዝን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ኢሜግሬሽን በኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጉዳይ ላይ መልስ መስጠት አልቻለም



• ‹‹ይህ ሁሉ ከአቅመ ቢስነታቸው የመነጨ ነው›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጉዳይ ላይ መልስ መስጠት አለመቻሉንና ይህም ሆን ተብሎ ጉዟቸውን ለማጓተትና እንቅስቃሴያቸው ለመግታት የተደረገ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ በትናንትናው ዕለት ቀጠሮ ሰጥቷቸው የነበር ቢሆንም ምንም አይነት ምክንያትና መፍትሄ ሳይሰጥ ለዛሬም ሌላ ቀጠሮ ተሰቷቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በዛሬው ዕለትም የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ሲሄዱ ‹‹ፓስፖርቱ እኛ ጋር አልደረሰም፡፡ ቆይተው ደውለው ይጠይቁ›› ብለው ስልክ እንደሰጧቸው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆን ተብሎ ጉዞውን ለማጓተት የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ይህን ሁሉ የሚያደርጉት አገር የማስተዳደር ብቃት ስለሌላቸው፣ የፖለቲከኛን እንቅስቃሴ በማጓተትና በማገድ የተፈጠረባቸው ስጋት የሚቀርፉ ስለሚመስላቸው ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ከአቅመ ቢስነታቸው የመነጨ ነው›› ብለዋል፡፡ በምርጫ ክርክር ወቅት ኢህአዴግ ሰማያዊ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጋር ያለውን ግንኙነት አሉታዊ አድርጎ እንዳቀረበ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የኢህአዴግ ሚዲያዎችም ይህን አቋም እየተደጋገመ እንደሆነ የገለጹት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያለው ተቀባይነት፣ እነዚን ኢትዮጵያውያን እያንቀሳቀሰ መሆኑና አቅማቸውን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑ በጣም አስፈርቶታል ብለዋል፡፡

በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በ19ኛው ወንጀል ችሎት እየታየ ያለው የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የክስ ጉዳይ



በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በ19ኛው ወንጀል ችሎት እየታየ ያለው የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የክስ ጉዳይ ለሁለተኛ ቀን ምስክሮችን አሰምቶ በአወዛጋቢ መልኩ ለሚቀጥለው መጋቢት 30 ቀጠሮ ይዞ ተጠናቋል፡፡
ከእለቱ ዋዜማ ቃለ መሃላ ፈጽመው ሳይሰሙ የቀሩት ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን ቃለ መሃላ በቀደመው ቀን በመግባታቸው ቀጥታ ወደ ምስክርነት ቃላቸው ተገብቷል፡፡ በሃያ ስድስተኛው የፍርድ ቤት ውሎ ተሰሙት ምስክሮች
7ተኛ ምስክር -ተስፋዬ መንግስቴ የመሰከሩት አቤል ዋበላ ላይ ሲሆን ከመንገድ ላይ ፓሊስ ሲፈትሹ አንዲታዘቡ ጠይቋቸው ቤቱ እና መስሪያ ቤቱ የተገኘው ሲዲ መጽሄቶች እና መጸሃፍት ላይ ሲገኙ አይቼ ፈርሜያለው አቤልም ፈርሟል ብለዋል፡፡
8ተኛ ምስክር- አቶ በረከት ጌታቸው በተመሳሳይ መንገድ ላይ ፓሊስ ታዘቡልኝ ብሎ የበፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ መታዘባቸውን በፍቃዱ የፈረመባቸው ነገሮች ላይም መፈረማቸውን ተናግረዋል፡፡ ጽሁፎቹ አማርኛ እና አንግሊዘኛ ከመሆናቸው ውጪ የሚያስታውሱት ይዘት አንደሌለ ተናግረዋል፡፡
9ኛ ምስክር - አቶ አንድነት ስሜ ይባለሉ አጥናፍ ብርሃኔ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ቤቱ የተገኙ ወረቀቶች ላይ እሱም ፈርሟል አኔም ፈርሜያለው ብለዋል፡፡ የተገኙት ወረቀቶች አማርኛ እና እንግሊዘኛ ሲሆኑ ሴኩሪቲ ኢን ኤቦክስ የሚል መጽሃፍ አለበት ብለዋል፡፡ በይዘቱ ላይ አቃቤ ህግ አንዲመሰክሩ ቢጠይቅም ጠበቆች በይዘቱ ላይ ለመመስከር ስላልተመዘገቡ አንዳይመሰክሩ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲመሰክሩ ቢፈቅድም ምስክሩ ምንም ይዘት አንደማያስታውሱ ተናግረዋል፡፡
10ኛ ምስክር -አቶ ታምራት ዓለሙ የሚባሉ ሲሆን አቤል ዋበላ ቤት ሲፈተሽ እንደነበሩ በመግለጽ ምስክርነታቸውን አሰምተዋል፡፡ አቤል የፈረመባቸው ነገሮች ላይ ፈርመናል ያሉ ሲሆን የነጻነት ጎህ ሲቀድ መጽሃፍ እስልምና በኢትዬጲያ የሚል መጽሃፍ አዲስ ጉዳይ መጽኄቶች አና እምነት እና ተስፋ በኢትዬጲያ የሚሊ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡ ሲዲም ተገኝቷል ብለዋል፡፡ የፍተሻውን ቀን ሚያዝያ 11 ነው ብለዋል፡፡ ( ጦማሪ አቤል የታሰረው ሚያዝያ 17 አንደሆነ ይታወቃል)
11ኛ ምስክር አቶ ፋሲል ግርማ ሲሆኑ በፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤት ውስጥ ተገኙት እቃዎች እና ሰነዶች ላይ ተከሳሹ ሲፈርም እኛም ፈርመናል ብለዋል፡፡ የተገኙትን ሰነዶች ብዛትና ይዘት እንደማያሰታውሱም ተናግረዋል፡፡
12ኛ ምስክር አቶ ደረጀ አበበ የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ ባልደረባ ሲሆኑ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ቢሮ ሲፈተሽ ፓሊስ ታዘቡ ብሏቸው አንደነበሩ እና ተገኙት ወረቀቶች ላይ ፈርመው ቢሮውን ዘግተው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የፈረሙበትን ወረቀት ይዘት የማያስታውሱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
13ኛ ምስክር አቶ አክሊሉ ሃይለማርያም ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ስሙን ብቻ ነው የማስታውሰው በማለት ያዬትን ተናግረዋል፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዬን አካባቢ ያለው ቤቱ ሲፈተሽ የተገኙ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ጽሁፎች የግል ማስታወሻዎች ሲም ካርድ እና መጽሃፍት የተገኙ ሲሆን ሁሉም ላይ በፍቃዱም ሲፈርም እኔም ፈርሜያለሁ ብለዋል፡፡
በ14ኛ ምስክርነት አቶ የማነ ብርሃኔ የተባሉ ግለሰብ ቀርበው የነበር ቢሆንም አቃቤ ህግ ‹የተለየ ነገር አያስረዱልኝም› በሚል ምስክሩ ሳይደመጡ እንዲመለሱ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ምስክርነታቸው ሳይሰማ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ አጠቃላይ 41 ምስክሮችን እንዳስመዘገበ በመጥቀስ ትናንት ካስመዘገባቸው 17 ምስክሮች ውጭ ሌሎቹን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳጣቸው በመግለጽ ማቅረብ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን 8ኛ፣ 9ኛ እና 27ኛ ላይ አቃቤ ህግ ያስመዘገባቸው ምስክሮች መጥሪያ ደብዳቤ ደርሷቸው እንዳልተገኙለት ገልጹዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠበቆችን (የተከሳሾችን) አስተያየት ጠይቆ ነበር፡፡ በዚህም ጠበቆቹ አሉ የተባሉትን ምስክሮች ፌደራል ፖሊስ ሌሎችን በአድራሻቸው ፈልጎ ማቅረብ ይገባው እንደነበር፣ እግዚቢት ላይ የተመሰከሩት ቃሎችን ፍ/ቤቱ እንዳይመዘግባቸው ማመልከት፣ እንዲሁም ያልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ምስክር መስማቱ ተገቢ እንዳልሆነ በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም አቃቤ ህግ ቀሪ ምስክሮችን ማሰማት ካለበትም ምስክሮቹን በተሰጠው ቀን ( የማስረጃ መስማት ለሶሰት ተከታታይ ቀናት አንደተቀጠረ ይታወሳል) እንዲያቀርብ በማሳሰብ የደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት በፍርድ ቤቱና በአቃቤ ህግ በኩል እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ባልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ይህን ያህል ጊዜ መውሰዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ጦማሪ ናትናኤል በበኩሉ ‹‹አቃቤ ህግ ያቀረበውን ሰምተናል፤ እኛ ብቻችንን አይደለም የታሰርነው፤ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችንም አብረውን ታስረዋል፡፡ በህሊና እና በኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰብን ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሁሉ ‹ውሳኔው ላይ አብሮ እንዲታይልን እናመለክታለን ብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠዋት ምስክር መስማቱን ሂደት አጠናቆ ለከሰአት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ ከሰአት በኋላ ሁለት ጉዳዬች ብይን ሰጥቷል፡፡ የመጀመሪያው የምስክሮች ቃል ከመዝገቡ ጋር አንዲያያዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀሩ የተባሉት ሶስት ምስክሮች ታስረው ለመጋቢት 30 አንዲቀርቡ እና አቃቤ ህግ ተጨማሪ ምስክሮች አሉኝ ካለም አንዲያቀርብ ነው፡፡በዚህም መሰረት ለሶስት ቀን የታቀደው ምስክሮችን መስማት በአንድ ቀን ከግማሽ ተጠናቋል፡፡ ጠበቆች አቃቤ ህግ ቀድሞ በተወሰነው ቀን ምስክሮችን ሊያቀርብ ሲገባ ሌላ ቀነ ቀጠሮ መሰጠት የለበትም በማለት ያቀረቡትን ተቃውሞ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክሮቹን በፌደራል ፓሊስ እያስፈለኩ ስለሆነ ተከሳሾ ማረሚያ ቤት እንዳሉ ለፍለጋው ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ነበር ፡፡
ጠበቆቹ አቃቤ ህግ የእግዚቢት ሰነዶችን በተመለከተ የመዝገብ ቁጥሩን ገልጾ እንዲቀርብ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ በትዕዛዙ መሰረት አቃቤ ህግ ዛሬ የመዝገብ ቁጥሩን ይዞ መቅረብ የነበረበት ቢሆንም፣ ጠበቆቹ ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት ሲጠይቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልሰጠንም በሚል ክዷል፡፡
የዞን9 ማስታወሻ
አቃቤ ህግ የሌሉትን ምስክሮች ፍለጋ በማለት ለሚያባክነው ጊዜ ፍርድ ቤቱ አንደተለመደው ተባባሪ መሆኑ የፍትህ ስርአቱን በአጠቃላይ እና ይህንን መዝገብ ሂደት ይበልጥ አሳፋሪ አድርጎታል፡፡ አሁንም ቢሆን የተከሳሾች አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ተጠብቆ ሁሉም ተከሳሾች ነጻ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ አጥብቀን እንጠይቃለን ፡፡ ያልተሰራ ወንጀል ምስክር አይገኝለትም ፡፡
ዞን9

ወቅቱ የተግባራዊ ትግል ነው!

pg7-logoለገዛ ራሱ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያ ቅን የሚመኝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ህወሓትን ለማስወገድ ተግባራዊ ትግል ውስጥ መሳተፍ የሚኖርበት ወቅት ላይ እንገኛለን። በዚህ ወሳኝ ወቅት ከዳር ሆኖ መታዘብ ዘረኛውን፣ አምባገነኑን፣ ፋሽስቱን ህወሓት እንደመደገፍ ይቆጠራል።
ዛሬ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህሊናውና አቅሙ በሚፈቅድለት የትግል ዘርፍ የመሰማራት ሰፊ እድል ተፈጥሮለታል። በዚህም መሠረት የህወሓትን አፈና በጠነከረ ክንድ ለመመከት የቆረጡ ኢትዮጵያዊያን ወደ በረሃዎችና ተራራዎች አቅንተዋል። ብዙዎች በመንገዱ ላይ ያሉ ጋሬጣዎችን ተቋቁመው እየተቀላቀሏቸው ነው። በደል የመረራቸው ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በቡድን ለነፃነታቸው ዘብ ቆመው በህወሓትና አገልጋዮቹ ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል። ይህ የሚበረታታ እና ተቀናጅቶ ሊጠናከር የሚገባው ጉዳይ ነው።
አሁን ያለንበት ጊዜ ልዩ የትግል ወቅት ነው። ትናንት በከተሞች ይካሄድ የነበረው ፀረ ወያኔ ትግል ዓይነተኛ መታወቂያው ሕዝባዊ ተቃውሞ ነበር። ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። በተለይ በአገዛዙ ፈቃድ የሚደረጉ ተቃውሞዎች ፋይዳ ቢስ ሆነዋል። በአገዛዙ ፈቃድ በሚደረጉ ተቃውሞዎች ለውጥ እንደማይመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያሻማ ሁኔታ ተረድቷል። ስለሆነም ትግሉ ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት አድጓል።
ዛሬ ከዚህ በፊት ያልተሞከሩ የትግል ስልቶች ተግባራዊ እየሆኑ ነው። በዚህ ረገድ የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን የተቀናጁ ርምጃዎች በአርዓያነት የሚጠቀሱና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ የሚሹ ናቸው። እነዚህ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ተግባራት የእምነት አጥር ሳይለያየን ፍትህ የተጠማን ዜጎች ሁሉ ልንተገብራቸው የሚገቡ ናቸው።
ለምሳሌ፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በተወሰኑ ቀናት መዝጋት በተቀናጀ ሁኔታ ከተደረገ ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ የሚችል፤ በሙስሊም ወገኖቻችን ግንባር ቀደም መሪነትና አስተባባሪነት ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል መሆኑ የታየ አንድ የትግል ስልት ነው።
በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው ሣንቲሞችን የመሰብሰብ ዘመቻም ሌላ ከዚህ በፊት ያልተሞከረ፤ በተጨማሪ እርምጃዎች ከታገዘ ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን ገንዘብ መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ ላይ ሊያደርስ የሚችል ጉልበት ያለው ስልት ነው። ውሳኔው ሣንቲሞችን ብቻ ሳይሆን የወረቀት ኖቶችንም ሲያካትት በዝውውር ላይ የሚኖረውን ገንዘብ ብዛት የሚቆጣጠረው ህወሓት ሳይሆን በደል ያንገሸገሸው ሕዝብ ይሆናል። በባንኮች ያለ ተቀማጭ ገንዘብ በማውጣትም የህወሓት የፋይናንስ ተቋማትን ማሽመድመድ ሌላ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ስልት ነው። በእነዚህ እርምጃዎች የተለማመደ ሕዝብም ወደ ግዢ እቀባ፤ ለተወሰኑ ቀናት ከቤት አለመውጣት ብሎም “ግብር አልከፍልም” ወደማለት ሊሸጋገር ይችላል።
እንዲህ ዓይነቱ ስልቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ግን የመላው ሕዝብ ተሳትፎ እና የተቀናጀ አሠራርን ይፈልጋል። ለምሳሌ፣ ሰብስቡ ሲባል መሰብሰብን፤ በትኑ ሲባል መበተን ይጠይቃል። እንዲህ ዓይነት የተቀናጁ የጋራ እርምጃዎች በአምባገኑ የህወሓት አገዛዝ ላይ ከሚያደርሱት ጥቃት በተጨማሪ በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለውን መግባባት ያጠናክራሉ። እንዲህ ዓይነት የተቀናጁ የጋራ እርምጃዎች በማኅበረሰብ ቡድኖች መካከል አዎንታዊ መስተጋብር ለመፍጠር የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
አሁን አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ በጥሞና ሲጤን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይነጋገር መግባባት፣ እርስ በርሱ መናበብ የሚችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑ መረዳት ይቻላል። ይህ ስነልቦናዊ ዝግጅት ደረጃ በደረጃ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያዘጋጀናል።
በማናቸውም የጋራ እርምጃዎች ለግል ጥቅሞቻቸው ቅድሚያ የሚሰጡ፤ ራሳቸው “ብልጥ” አድርገው በማየት በተፈጠረው ሁኔታ መጠቀም የሚፈልጉ፤ በሌላው ድካም ለማትረፍ የሚሯሯጡ ሰዎች መኖራቸው የማይቀር ነው። ህወሓት ለሃያ አራት ዓመታት ኮትኩቶ ያሳደገው የአድርባይነት ባህልም ሌላው እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ድህነት ደግሞ በገዢዎች ላይ ጨክነን የመነሳት አቅማችንን እንደሚያዳክም የታወቀ ነው። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፊቱ የቀረበለት ምርጫ “ባርነት ወይስ ነፃነት” መሆኑን የተገነዘበበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
በዚህም ምክንያት ለህወሓት ባርነት ከመገዛት ነፃነትን የሚመርጥ ዜጋ ሁሉ ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርበታል። ለሁላችንም የሚሆን የትግል ዘርፍ መኖሩ የሕዝቡን ተሳትፎ ከፍ ያደርገዋል። የሁለገብ ትግል ስትራቴጂ ጥቅሙም እዚህ ላይ ነው። ማንም የማንም ነፃ አውጭ አይደለም። ሁላችንም ተባብረን ሁላችንንም ነፃ እናወጣለን።
አርበኖች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ትግላችን ዘርፈ ብዙ ነው፤ ተግባራዊ ትግል የሚደረገውን በሁሉም ቦታዎች ነው፤ እርጃዎቻችን እናቀናጅ፤ ወቅቱ የተግባራዊ ትግል ነው” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Wednesday, April 1, 2015

ሰበር ዜና ኢንጂንየር ይልቃል ጌትነት ከሃገር እንዳይወጡ ታገዱ



ኢንጂንየር ይልቃል ጌትነት እንዳይወጡ ታገዱ
በኢትዮጵያ ዋነኛ የሚባለው ተቃዋሚ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂንየር ይልቃል ጌትነት በአሜሪካ የሚኖሩ የፓርቲውን ደጋፊዎች ለማግኘት እንዳይጓዙ ዛሬ ምሽት በድጋሚ ከቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ታገዱ። 
በእልህና በቁጭት በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰማያዊ ፓርቲን ለመደገፍ የሚያደጉት አስተዋጽዎ ከመቸም በላይ እንደሚሆን አገዛዙ ተገንዝቧል። ትግሉ ይቀጥላል !!!

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በተከሰሱት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ላይ ምስክሮች መሰማት ጀመሩ

zone 9 bloggers
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የሽብርተኝነት ክስ በመሠረተባቸው ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ላይ ምስክሮቹን ከመጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ማሰማት ጀመረ፡፡
ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ባስያዘው ጭብጥ፣ በዕለቱ ያቀረባቸው ምስክሮች የደረጃ ወይም ታዛቢ ምስክሮች መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ የሚመሰክሩትም ፖሊስ በተከሳሾቹ ቤት፣ በቢሮአቸውና በማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ፣ ከተከሳሾቹ ላይ የተገኙ ማስረጃዎች የእነሱ መሆናቸውን አምነው ሲፈርሙ ማየታቸውንና እነሱም መፈረማቸውን መሆኑን ገልጿል፡፡
ታዛቢ ምስክሮቹ አንዳንዶቹ ለግል ጉዳያቸው በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ሄደው ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑለት ሲጠይቃቸው፣ በፈቃደኝነት የታዘቡ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ከራሳቸው ላፕቶፕ ላይ (አንዳንዶቹ) የአማርኛና እንግሊዝኛ ጽሑፎችን ማየታቸውንና ርዕስ ርዕሱን ማንበባቸውን ገልጸዋል፡፡ አቤል ዋበላ የተባለው ጦማሪ በራሱ የይለፍ ቃል (Pass Word) ላፕቶፑ ተከፍቶ የታተመ ‹‹አፍሪካን ሪቪው›› የሚል በእንግሊዝኛ የተጻፈ ነገር ማየታቸውን መስክረዋል፡፡ ‹‹ወያኔ ወይኔ ጉዱ›› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ደግሞ የበፈቃዱ ኃይሉ ላፕቶፕ ተከፍቶ ሲታተም ማየታቸውን መስክረዋል፡፡
አንድ ታዛቢ የታዘቡትና ምስክር የፈረሙት በጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ ላይ መሆኑን ቢገልጹም፣ አስማማውን ከስም በስተቀር በአካል መለየት አቅቷቸዋል፡፡
ቀረብ ብለው እንዲለዩት ቢደረግም ጦማሪ አቤል ዋበላን ‹‹እሱ ነው›› ብለው ደጋግመው ከመናገር ያለፈ አስማማውን መለየት ባለመቻላቸው የችሎት ታዳሚውን አስፈግገዋል፡፡ ሌሎቹም ምስክሮች ተመሳሳይ ምስክርነት በመስጠት ተከሳሾቹ ከፈረሙ በኋላ እነሱም በሰነዱ ላይ መፈረማቸውን ገልጸዋል፡፡
ስድስት ምስክሮችን መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ያሳማው ዓቃቤ ሕግ፣ መጋቢት 22 ደግሞ ስምንት ምስክሮችን አቅርቦ ሰባቱን አሰምቷል፡፡ ሁሉም ተመሳሳይነት ያለው ቃል መስክረዋል፡፡ ቀሪዎቹ ምስክሮች መጥሪያ ደርሷቸው ባለመቅረባቸው ታስረው እንዲቀርቡለት፣ ሌሎች ምስክሮችን ፖሊስ ፈልጎ ሊያገኛቸው ባለመቻሉ፣ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶት አፈላልጎ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡ ፖሊስ አፈላልጎ ስለማጣቱ ዓቃቤ ሕግ ምንም ማስረጃ ባላቀረበበት፣ ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡትም ቢሆኑ በአዳር እንዲቀርቡ እንዲታዘዝላቸው ጠይቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የሰነድን ማስረጃ በሚመለከት ስላልካዱ እነሱን በእስር አቆይቶ እንዲንገላቱ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ ስለሌለው፣ ዓቃቤ ሕግ ተመሳሳይነት ያላቸው ምስክሮቹን ማሰማቱን አቋርጦ ወደ ቀጣይ ማስረጃ መስማት እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ምስክሮቹን ከማሰማቱ በፊት አቤቱታ እንዳለው አመልክቶ ፍርድ ቤቱ ሲቀበለው፣ በምስክሮች ጥበቃ አዋጅና በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652 2001 አንቀጽ 32 መሠረት ‹‹ምስክሮቼ ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ምስክርነቱ በዝግ ይታይልኝ፤›› ብሎ አመልክቷል፡፡
ዳኞቹ ተመካክረው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 መሠረት በዝግ የሚታዩ ጉዳዮች ተዘርዝረው ከመቀመጣቸው አንፃር፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው አቤቱታ አሳማኝ አለመሆኑን በመንገር አቤቱታውን ወድቅ አድርገውበታል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ መጋቢት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ ፖሊስ ያላገኛቸውን ምስክሮች ፈልጎ እንዲያቀርብና መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡት ምስክሮች ታስረው ለመጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጥሯል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter