የአፍሪቃ መሪዎች ባለፈዉ ሳምንት ባካሄዱት ጉባኤ አንድ መሪ በስልጣን ላይ እያለ ክስ እንዳይመሠረትበት መስማማታቸዉ ትችት አስከትሏል። የአፍሪቃ የፍትህና የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የተሰኘዉ መድረክ ስልጣን ላይ የሚገኙ መሪዎችና ባለስልጣናትን መክሰስ እንዳይችል የታገደ ነዉ።
የመብት ተሟጋቾች ከወዲሁ የተጣለዉ እገዳ ወንጀል ፈፃሚዎች ሳይጠየቁ በነፃ እንዲኖሩ ያደርጋል እያሉ ነዉ። የአፍሪቃ መሪዎች ይህን ዉሳኔ ያሳለፉት ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ዕለት ኢኳቶሪያል ጊኒ ላይ ባካሄዱት ጉባኤ ነዉ። አሶሲየትድ ፕረስ እንደሚለዉ የመሪዎቹ ስብሰባ ጋዜጠኞች እንዳይገቡ ተደርጎ በዝግ ነዉ የተካሄደዉ። የዝግ ስብሰባዉ ዉሳኔም ሰኞ ዕለት ማምሻዉ ላይ በመግለጫ መልክ በድርጅቱ ይፋ ሆነ። መሪዎቹ አፍሪቃዊ መሪም ሆነ የመንግስት ባለስልጣን ስልጣን ላይ እያለ ክስ ሊመሠረትበት አይገባም ማለታቸዉን 42 የአፍሪቃ እና ዓለም ዓቀፍ ሲቪል ማኅበራትና የመብት ተሟጋች ቡድኖች ተቃዉመዋል።
በሎንዶን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የህግ አማካሪ ኮላዋሊ ኦላኒያ( kolawole Olaniyan) የመብት ተሟጋቻቾች የተቃወሙበትን ምክንያት ያስረዳሉ፤
«የተደረገዉ ማሻሻያ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ያሳስበዋል፤ ምክንያቱም ለአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች፣ የመንግስት ከፍተኛ ባልስልጣናትና መራሄ መንግስታት በጅምላ ጭፍጨፋ፣ በጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ያለመከሰስን ከለላ ይሰጣል። ያለመከሰስ መብት ደግሞ እንደሚታወቀዉ ወንጀል ፈፅሞ በነፃነት መንቀሳቀስን ያስከትላል። ይህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባዎችን ይጎዳል። ለዚህ ነዉ እኛ የተቃዉምነዉ።»
እንደአምነስቲ እምነትም ስልጣን ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች የማይከሰሱ ከሆነ የመብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች ቢፈፀሙም ተጠያቂዉ በነፃነት እንዲኖር ያስችላል። አፍሪቃ ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ለማስቻል ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በዚህ ወቅትም መሪዎቿ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ መስማማታቸዉ ትርጉም እንደሚያጣ ነዉ የተገለፀዉ። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የህግ አማካሪ ኮላዋሊ ኦላኒያ እንደሚሉት የአፍሪቃ መሪዎች ይህን ማሻሻያ ያደረጉበት ወቅት አነጋጋሪ ነዉ፤
«ይህ ነገር የመጣዉ የአፍሪቃ መሪዎች ዓለም ዓቀፉን የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ላይ ከፍተኛ ተቃዉሞ ባሰሙበት ወቅት ነዉ። ፖለቲካዊ ስሌት እንዳለዉ አናዉቅም። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንዳልኩት ይህ ፍርድ ቤት የአፍሪቃ መሪዎች በስልጣን ላይ እስካሉና እስከቆዩ ድረስ ከሶ ከችሎት ማቆም አይችልም።»
የአፍሪቃ ኅብረት ICC በኬንያ ፕሬዝደንት ዑሁሩ ኬንያታና በምክትላቸዉ ላይ የመሠረተዉን ክስ እንዲያስነሳ የተመድ ላይ ያደረገዉ ግፊት ዉጤት አላመጣም። ሁለቱም በጎርጎሪዮሳዊዉ 2007ዓ,ም በሀገራቸዉ ከተካሄደዉ ምርጫ በኋላ በተፈጠረዉ ግጭት በሰብዓዊነት ላይ ከተፈፀሙ ወንጀሎች ጋ በተገናኘ ICC ክስ መስርቶባቸዋል።ሁለቱም ግን የቀረበባቸዉን ክስ ያስተባብላሉ። የአፍሪቃ መሪዎችም አፍሪቃ ላይ ብቻ ያተኩራል ያሉት ICC በመንበረ ስልጣናቸዉ ላይ የሚገኙ መሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን በአንድ ድምፅ እየተቃወሙ ነዉ። ችሎቱ ከተመሠረተበት የሮማ ዉል ፈራሚ የአፍሪቃ ሃገራት ቦትስዋና ብቻ ይህን ተቃዉማለች።ተቺዎችም እንዲሁ የICC አባል ያልሆነችዉ ዩናይትድ ስቴትስ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በፍርድ ቤቱ አሰራር እጇን እንደምትከት በማመልከት የአፍሪቃ መሪዎች በራሳቸዉ ላይ ያነጣጠረ ነዉ የሚሉትን ፍርድ ቤት አሠራር መቃወማቸዉ አይደንቅም ይላሉ። ኮላዋሊ ኦላኒያ በዚህ ላይ አስተያየታቸዉን እንዲሰጥተዋል፤
«እዉነታዉ አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግስታት ዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት የተመሠረተበት የሮም ዉል ፈራሚዎች ናቸዉ። እናም ይህን ተጠቅመዉ ለራሳቸዉ ያለመከሰስ መብት ማጎናጸም መሞከራቸዉ ስህተት ነዉ። ምክንያቱም ይህ ከመተዳደሪያ ደንባቸዉ የሚጻረር ነዉ። የኅብረቱን የመተዳደሪያ ደንቡን ብትመለከቺ የአፍሪቃ መንግስታት ወንጀል ፈጽሞ ሳይጠየቁ መኖርን ለመዋጋት ዝግጁና ፈቃደኛ ናቸዉ ይላል። ምክንያቱም ቀደም ብዬ እንዳልኩት ያለመከሰስ መብት መኖር ማለት ወንጀል ፈፅሞ በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ያጎናፅፋል። ይህ ነዉ እየኛ አቋም፣ ለዚህም ነዉ የአፍሪቃ ኅብረትና የአፍሪቃ መሪዎች በዚህ ላይ ያደረጉትን ማሻሻያ እንዲያጤኑት የምንጠይቀዉ።»
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የICC አካል ባለመሆኑ የክስ አቀራረብ ሂደትና አሠራሩን እንደማያዉቅ ያመለከቱት የድርጅቱ የሕግ አማካሪ ፍርድ ቤቱ ምንም ቢያደርግ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል የሚፈፅሙ መሪዎች ግን ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ አይከሰሱ የሚለዉን አጥብቆ እንደሚቃወም ገልጸዋል። ICC ከኬንያንያ መሪዎች በተጨማሪ በሱዳኑ ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር ላይ የቆረጠዉ የእስር ማዘዣ እስካሁን እልባት ያልተገኘለት መከራከሪያ እንደሆነ ነዉ።
ሸዋዬ ለገሠ
ተክሌ የኋላ
Source: dw
No comments:
Post a Comment