Sunday, July 21, 2013

ከአገር በወጡት የመሬት ባለሥልጣን ምክንያት ውዝግቡ ቀጥሏል

ከአገር በወጡት የመሬት ባለሥልጣን ምክንያት ውዝግቡ ቀጥሏል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቃሲም ፊጤ፣ ከአገር የወጡበት ሁኔታና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን በማንሳትና ባለማንሳት ሒደት ከተፈጠረው ልዩነት ጀምሮ ውዝግቡ ቀጥሏል፡፡
አቶ ቃሲም ከመሬት ጋር በተያያዘ በሙስና ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ለተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ የቀረበው ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ በደኅንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ባለሥልጣን ሥር ለሚገኘው ለኢሚግሬሽንና የዜግነት ዋና መምሪያ ከአገር እንዳይወጡ እንዲተባበር በደብዳቤ የተጠየቀው ሐምሌ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. መሆኑን ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡

ነገር ግን የአቶ ቃሲም ያለመከሰስ መብት ለአንድ ዓመት ያህል የተንከባለለበት ምክንያትና ከአገር እንዳይወጡ በደብዳቤ ከተጠየቀ ከዓመት በኋላ ከአገር የወጡበት ሁኔታ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ ፓርላማው የአቶ ቃሲም ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የቀረበለትን ሰነድና የውሳኔ ሐሳብ ከመረመረ በኋላ፣ የተለያዩ የአሠራር ሒደቶችን በማንሳት ተገቢውን ድጋፍ ሊሰጠው አልቻለም፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአቶ ቃሲምን ያለመከሰስ መብት በማንሳትና ባለማንሳት ሒደት ተቃውሞና ድጋፍ ተሰምቷል፡፡ በዋናነት የአቶ ቃሲም ያለመከሰስ መብት ሰኔ 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ሳይነሳ የቀረው፣ በፓርላማው ሥነ ሥርዓት ሕግ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከሳሽ በመሆኑ ለምክር ቤቱ ጥያቄ መቅረብ ያለበት በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል መሆን አለበት በመባሉ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ግን ኢሕአዴግ ለሚመራው መንግሥት የሚዋጥ ሀቅ አልሆነም፡፡ ከኢሕአዴግ አካባቢ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ መንግሥት ሙስናን እዋጋለሁ ብሎ በተነሳበት ወቅት ፓርላማው አሠራሮችን እየጠቀሰ ሒደቱን ማጓተት የለበትም የሚል ነው፡፡

በዚህ መሠረት ኢሕአዴግን የመሠረቱት አራቱ ፓርቲዎች ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን የፓርላማ አባላቶቻቸውን ጠርተው ጠንከር ያለ ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ ስብሰባው ረዥም ጊዜ ወስዶ የተካሄደ ሲሆን አባላቱ በአብዛኛው በመንግሥት አቅጣጫ ላይ መግባባት ላይ እንደደረሱ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት የአቶ ቃሲም አለመከሰስ የሕግ ከለላ እንዲነሳ ጥያቄው ለሦስተኛ ጊዜ ቀርቦ የምክር ቤቱን ሙሉ ድጋፍ በማግኘት ያለመከሰስ መብታቸው በማግስቱ ሰኔ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ተነስቷል፡፡  

ነገር ግን የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ ቃሲምን በቁጥጥር ሥር ማዋል ሳይችል ቀርቷል፡፡ የአቶ ቃሲም ያለ መከሰስ መብት ዓርብ ተነስቶ አቶ ቃሲም ከአራት ቀናት በኋላ ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ ወደ ቻይና ማቅናታቸው ተገልጿል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የአቶ ቃሲም ያለመከሰስ መብት መነሳቱን ያወቀው እንደማንኛውም ዜጋ በሬዲዮ ዜና መሆኑን እየገለጸ ይገኛል፡፡ ክትትል እያደረገ አቶ ቃሲም ቢሮ መኖራቸውን እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ማረጋገጡንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

አቶ ቃሲም ለሥራ መሆኑን ለባለቤታቸው ከመንገራቸው ውጪ ለማንም ሳያሳውቁ ሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ሌሊቱን ከአገር መውጣታቸውን ተከትሎ የመንግሥት አካላትና የተለያዩ ሰዎች ያነሱትን ተቃውሞ ለመከላከል በሚመስል ሁኔታ፣ ኮሚሽኑ ፓርላማው ሊያሳውቀው ይገባ እንደነበር እየገለጸ ይገኛል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም ብርሃኑ፣ አንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ሲነሳ ለጠያቂው አካል እንዲያውቅ ስለሚደረግበት ሁኔታ እንዲያስረዱ ተጠይቀው፣ ለሚመለከተው አካል በተነሳበት ዕለት እንዲያውቅ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ አቶ ቃሲምን በሚመለከት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳበትን ውሳኔ ሰኔ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ፈርሞ መውሰዱን አረጋግጠዋል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ ቃሲም ተጠርጥረውበታል ባላቸው ከ500 ካሬ ሜትር ቦታ ጋር የተያያዘ ሙስና ጉዳይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቁጥር 426/መመ/-መ10/7690 ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳለት መጠየቁ ታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ያቀረበውን ያለመከሰስ መብት ይነሳልኝ ጥያቄ ተከትሎ፣ ሐምሌ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. በደኅንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ባለሥልጣን የኤሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምርያ፣ ግለሰቡ ከአገር ሲወጡ በመውጫ ኬላዎች ክትትል ተደርጐ ሪፖርት እንዲደረግለት የትብብር ደብዳቤ በኮሚሽኑ የምርመራ ዓቃቢያነ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መጻፉ ታውቋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የሚገልጹት፣ ኮሚሽኑ ችላ ያለው ምናልባት ከዓመት በፊት ለኢሚግሬሽን የጻፈውን ደብዳቤ ተማምኖ ሳይሆን እንደማይቀር ነው፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶ ጥፋቱን የሚገልጽ አካል ባይኖርም፣ ለቀጣይ ግን ማስተማሪያ ሆኖ ማለፉን አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ሲፈጸም ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ስለድርጊቱ ግልጽነት በተሞላው የኃላፊነት ስሜት ጉዳዩን ለሚመለከተው አካልም ሆነ ለሕዝቡ ማስረዳት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ለሙስና በእጅጉ የተጋለጠ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡ 

No comments: