Saturday, July 13, 2013

ኢህአዴግ፤ “አንድም፤ ሁለትም” ነው

ኢህአዴግ፤አንድም፤ ሁለትምነው

አንድም “አብዮታዊ ልሁን” ይላል፤ ሁለትም “ዲሞክራሲያዊ ልሁን” ይላል።
 ተቃዋሚዎችን ያስፈራራል፤ የሽብተኛ ህግ ያውጃል፤ “አንድ ለአምስት” ያደራጃል።
ዲሞክራሲያዊው ለተቃዋሚ ብር ያካፍላል፤ መሬት ለኢንቨስተር ይሰጣል፤ ማህበራት ነፃ ይሁኑ ይላል
የኢህአዴግ ነገር እንቆቅልሽ እየሆነ ለብዙዎች አስቸጋሪ የሚሆነው፤ ለካ አለምክንያት አይደለም። ግራ ስትሉት ወደ ቀኝ፤ እንደገና ቀኝ ስትሉት ግራ እየሆነ አንዳንዴ ቂም፤ ቁጣና እስር ያበዛል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ እርጋታ፤ ይቅር ባይነትና ቻይነት ይላበሳል። አንዳንዴ፤ የኢትዮጵያ ተስፋ ኢህአዴግ ብቻ ነው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዳያንሰራሩ እናደርጋቸዋለን፤ እሽሩሩ አንላቸውም ብሎ ይፎክራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ያስፈልጋል፤ ተቃዋሚዎች የገንዘብ እጥረት ካለባቸው ሊጠይቁን ይችላሉ ብሎ ይጋብዛል። ለፖለቲካው እንቆቅልሽ ፍቺ ሊሆን የሚችል መልስ ያገኘሁ ይመስለኛል። ለዚያውም ከራሱ ከኢህአዴግ ውስጥ፤ ነው ምላሹን የምናገኘው - (እከተለዋለሁ ከሚለው ”ከዲሞክራሲያዊ” አስተሳሰብ ውስጥ)።



እስቲ በየጊዜው የምትሰሟቸውን የኢህአዴግ አቋሞች አሰላስሉ። አንዳንዴ፤ የግል ቢዝነስ ዋነኛ የእድገት ሞተር ነው በማለት፤ ለኢንቨስትመንትና ለቢዝነስ ማነቆ የሆኑ የተንዛዙ የቢሮክራሲ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ዘመቻ ይጀምራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ የግል ቢዝነሶች ዋነኛ እንቅፋት ስለሆኑብኝ እቆነጥጣቸዋለሁ በማለት፤ አዳዲስ የቢሮክራሲ መሰናክሎችንና ቁጥጥሮችን በዘመቻ ይተክላል።
ኢህአዴግ፤ የውጭ አገራትን በተመለከተም እያሰለሰ ተቃራኒ አስተያየቶችን ይሰነዝራል። አንዳንዴ፤ አሜሪካንና አውሮፓን በጠላትነት እየፈረጀ፤ አምባገነኖችና ኢምፔርያሊስቶች መሆናቸውን በመግለፅ የውንጀላ መአት ያወርድባቸዋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ የዳበረና ምርጥ የዲሞክራሲ ስርአት የሰፈነባቸው እንደሆኑ በመጥቀስ ያሞግሳቸዋል። ምናለፋችሁ! ኢህአዴግ፤ በየጊዜው ከአንድ አቋም ወደ ተቃራኒው፤ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላ አቅጣጫ ይንደረደራል። ለጊዜያዊ “ጥቅም” ተብሎ የሚፈጠር የዥዋዥዌ ጨዋታ እንዳይመስላችሁ!
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: