Friday, November 27, 2015

በ‹‹እነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ›› መዝገብ ሥር የሚገኙ ተከሳሾች መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ

አቶ ሀብታሙ አያሌውና ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ መከላከያ ምስክር ሆነው ቀርበዋል
ፍ/ቤቱ ቀሪ የመከላከያ ምስክሮችን ለመሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
በኢዮኤል ፍሥሐ
በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው በ‹‹እነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ›› መዝገብ ሥር የሚገኙት ተከሳሾች ከሕዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ መከላከያ ምስክሮቻቸውን ማስደመጥ ጀመሩ፡፡
ሰኞ ሕዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ችሎት ከተገኙት ተከሳሾች መሃል 10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ካስመዘገቧቸው 8 መከላከያ ምስክሮች መሃል 7ቱን አስደምጠዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ማክሰኞ ሕዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም መከላከያ ምስክሮችን ማድመጥ የቀጠለ ሲሆን፤ በዕለቱ አቶ ተስፋዬ ያላስደመጡትን ቀሪ የመከላከያ ምስክራቸውን አሰምተዋል፡፡ ከአቶ ተስፋዬ በመቀጠል 6ኛ ተከሳሽ አቶ ዮናታን ወልዴ ካስመዘገቧቸው 5 መከላከያ ምስክሮች መሃል አራቱን አሰምተዋል፡፡ የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ የሆኑት አቶ አምሃ መኮንን ለዚህ ዜና ፀሐፊ እንደገለፁት፡- ደምበኛቸው አቶ ዮናታን ወልዴ ሕዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም በተሰየመው ችሎት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 142 መሰረት የመከላከያ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በመከላከያ ቃላቸውም ክሱ አራት ፍሬ ነገሮች እንዳለው በመግለፅ፤ የቀረበባቸው ክስ የሀሰት ውንጀላ መሆኑንና ከቀረበባቸው ክስ መሃል አንዳቸውንም እንዳላደረጓቸው ለፍ/ቤቱ በሰጡት የመከላከያ ቃል መግለፃቸውን ጠበቃቸው አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮናታን ወልዴ የቀረበብኝን ክስ ለመከላከል ይረዱኛል በሚል 5 መከላከያ ምስክሮችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 4ቱን አሰምተዋል፡፡ የተከሳሹ 1ኛ መከላከያ ምስክር የሆኑት አቶ ኃይሉ፣ ከዮናታን ጋር ለ17 ዓመት የቀረበ ጓደኝነት እንዳላቸው ገልፀው፤ አቶ ዮናታን ወሰዱት የተባለው ስልጠና ማህበራዊ ድረገፆችን በተሻለ ለመጠቀም እንደሚያስችል መሆኑንና ከሽብር ድርጊት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልፀዋል፡፡ ስልጠናዎቹን በማስመልከትም ዮናታን ስለስልጠናው ገልፆላቸው እንደነበርና እሳቸውም ስልጠናዎቹን ለመሳተፍ ፍቃደኝነታቸውን በመግለፅ ስልጠናዎቹን ለመሳተፍ "ሲቪያቸውን" ለድርጅቶቹ መላካቸውንና በኋላም ባላወቁት ምክንያት ስልጠናው ሳይሳካ መቅረቱን ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪነትም 6ኛ ተከሳሽ አቶ ዮናታን ወልዴን ለ17 ዓመታት ጓደኛቸው እንደመሆኑ መጠን በደንብ እንደሚያውቋቸውና የተለየ ነገር ማድረግ ቢፈልጉ እንኳ እሳቸውን ሳያናግር ምንም ነገር እንደማያደርግ ገልፀዋል፡፡ ከአቶ ኃይሉ በመቀጠል ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ለአቶ ዮናታን ወልዴ 2ኛ መከላከያ ምስክር ሆነው በመቅረብ የምስክርነት ቃላቸው ሰጥተዋል፡፡ አቶ አስማማው፣ አቶ ዮናታን ወሰዱት በተባለው ስልጠናን በማስመልከት የተናገሩ ሲሆን፤ የስልጠናዎቹን አላማ እንዲሁም አሰልጣኞቹም እነማን እንደሆኑ፣ ስልጠናዎቹም ሕገወጥ አላማ የሌላቸው መሆኑንና ስልጠናውን የሚሰጡት ድርጅቶችም ተጠያቂነት እንዳለባቸው በዝርዝር ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ረቡዕ ሕዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም ምስክር መስማቱን የቀጠለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ችሎት የዮናታን ወልዴን ቀሪ መከላከያ ምስክሮች መስማቱን ቀጥሏል፡፡ 3ኛ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው የዓቃቤ ሕግ 3ኛ ምስክር ሆኖ የቀረቡት አቶ ኢዮብ ታደሰ የተባሉት ግለሰብ ‹‹በዮናታን ላይ ለመመስከር የተገደዱት በደረሰባቸው ጫና የተነሳ መሆኑን‹‹ እና ‹‹ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት መሆኑንና ከዮናታን ወልዴ ጋር ትውውቅ እንደሌላቸው›› በሚሉ ጭብጦች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቶ ሀብታሙ በሰጡት የምስክርነት ቃል ላይ በአቶ ዮናታን ወልዴ ላይ የአቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ የቀረቡት፤ አቶ ኢዮብ ታደሰ ‹‹በዮናታን ላይ የምትመሰክር ከሆነ ትፈታለህ›› መባሉን እንደገለፁላቸው ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ፣ አቶ ኢዮብ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ልዩ ቦታው ‹‹ሳይቤሪያ›› ተብሎ በሚጠራው ቦታ እያሉ በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ የተነሳ መራመድ ይቸገሩ እንደነበር ማስተዋላቸውን ገልፀዋል፡፡ በአቶ ዮናታን ላይ የማትመሰክር ከሆነ ከእስር ልትለቀቅ አትችልም እንደተባሉ፣ ባለቤታቸውና ልጃቸው እሳቸው በመታሰራቸው የተነሳ እንደተቸገሩ እንደገለፁላቸውና በዚህ ጫና የተነሳም በአቶ ዮናታን ወልዴ ላይ ለመመስከር እንደተገደዱ ለፍ/ቤቱ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
ከአቶ ሀብታሙ በመቀጠል 1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ለአቶ ዮናታን ወልዴ በ4ኛ መከላከያ ምስክርነት በመቅረብ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዮናታን ወልዴ እንዲወስድ የጠቆሙት ስልጠና ምን እንደነበር፣ በማን በኩል ሊሰጥ እንደነበር፣ ስልጠናዎቹ ከሽብርና ከአመፅ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው እንዲሁም ዮናታን ወልዴንና 3ኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክርን አስተዋወቋቸው ተብሎ በክሱ ላይ የተጠቀሰው ከእውነት የራቀ መሆኑን በሚገልፅ ጭብጦች ላይ አቶ ዘላለም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከአቶ ዮናታን ወልዴ 4ኛ መከላከያ ምስክር አቶ ዘላለም በማስከተል 8ኛ ተከሳሽ አቶ ሰለሞን ግርማ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ግርማ ያስመዘገቧቸውን ሶስት መከላከያ ምስክሮች አስደምጠዋል፡፡
የአቶ ዮናታን ወልዴ 5ኛ መከላከያ ምስክር የሆኑት አቶ አብርሃ ደስታ የምስክርነት ቃላቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ፍ/ቤቱ አቶ አብርሃ ደስታ ለሚገኙበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አብርሃ ደስታን እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አብርሃን ሊያቀርብ አልቻለም፡፡ ይህን በማስመልከት የዚህ ዜና ፀሐፊ ጠበቃ አቶ አምሃን አነጋግሮ ነበር፡፡ አቶ አምሃ፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳላወቁና ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በሚገኙና በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ በተመዘገቡ ተከሳሾችን በተመለከተ ፍ/ቤቱ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ሐሙስ ሕዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም በቀጠለው የችሎት ውሎ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ካስመዘገቧቸው 11 መከላከያ ምስክሮች መሃል 5ቱን አሰምተዋል፡፡ ከሰኞ ሕዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በነበረው የፍ/ቤት ውሎ 9ኛ ተከሳሽ አቶ ባሕሩ ደጉ ብቻ ምንም ምስክር ሳያሰሙ ቀርተዋል፡፡ አቶ ባሕሩ ደጉ፣ 8 መከላከያ ምስክሮችን ማዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለሕዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ዳኞች ባለመሟላታቸው የተነሳ ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሕዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
ፎቶ፡- ከግራ ወደ ቀኝ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴና ባሕሩ ደጉ
ፎቶ ፡- ከዘብርሃን ብሎግ የተወሰደ

One Party Cannot Hold the Nation Together Says US official



In an interview foreign minister Tedros Adanom had with CNN’s Christiana Amanpour, eh tried to justify the hugely embarrassing 100% election result by arguing that democracy in Ethiopia is fragile and that it took 200 years even in the US.
The US Assistant secretary of State Tom Malinowski does not agree. He stressed that one person or one party cannot hold the Nation together, but laws and institutions. Though things cannot be perfect the secretary emphasized that there need to be improvement and movement towards the right directions. In the case of Ethiopia her says that the country is heading backward rather than forward.
Below is an excerpt from the speech Secretary Malinowski gave to law school students at Addis Ababa University.
=======================
Some insist that the only way to preserve stability and progress after war or social upheaval is to keep in power, year after year, the leaders or the parties that first brought it about. "Things are still fragile," they say. “Allowing changes in leadership, letting opposition parties, journalists, and civil society groups say what they want would just reopen the divisions that tore our societies apart in the past, so why would you want us to do that?” Or, they argue that, “yes, multiparty democracy and full respect for freedom of speech and the press are good; we are working towards that; but you in America had over 200 years to build your democracy; we also need time, time to develop our economy, time to consolidate what we have already achieved. So why are you telling us to move so fast?”
The problem with these arguments, the reason why they often fail in the real world, is that dignity is not just about having physical or material security. It is about men and women being in control of their lives.
Think about the people in Nigeria who voted in their election this year; many of them live in extreme poverty; many have been terrorized by Boko Haram; yet in some places they walked and waited for hours, and even risked their lives, just for the chance to cast one vote out of millions to choose their next president. Why did they do that? A ballot cannot protect you against a bullet; free speech cannot put food on your table. But eventually, people grow tired depending on others to provide for them. Eventually, they don’t want to be treated like children; they want to make their voices heard and their choices felt, without being told what they can say or who they can choose.
If that's true even in places where there is little security and prosperity, it certainly true where people are doing better, where expectations are rising, where young people are connecting through social media and seeing how their counterparts live in other parts of the world.
The challenge for governments that truly believe in stability and progress is to keep up with these inevitable changes in their societies. It is to build institutions through which all their people can take part in the debates, decisions and responsibilities of governance, and that allow responsibility to pass normally from one generation to another. As President Obama suggested in Addis Ababa, if you think that only one person or party can hold a nation together, then that person or party has failed to truly build its nation. Only institutions and laws can hold a nation together.
……….
It is in that spirit that we have encouraged Ethiopia, as we encourage many other countries, to realize step by step the freedoms your constitution promises and to broaden year by year the political space your government says is needed. In other words, we've encouraged Ethiopia simply to keep moving forward along its chosen path, not backward.
And I think it is fair to ask whether Ethiopia is in fact doing so. After all, the political opposition once had cabinet ministers; in 2000, it won 12 percent of the seats in Parliament. But in 2010 it won only two seats; and this year none. I know political leaders and parties in many countries that are very popular, as Ethiopia’s government clearly is. But I know none that credibly can claim to represent every single citizen in their country, or honestly argue that their political opponents merit zero representation in the national legislative body. If we agree, as I hope we do, that it is healthy to have checks and balances in government, then something here has gone amiss.

Source:  Millions Voices

እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ

᎐አንዳርጋቸው ጽጌና እስክንድር ነጋ ለምስክርነት ተጠርተዋል
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት አምስት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው አሰምተዋል፡፡ በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾችም ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ባህሩ ደጉ፣ ሰለሞን ግርማ እና ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ ከሰኞ ህዳር 13/2008 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ለአራት ቀናት ምስክሮቻቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ ዘላለም ወርቃገኘሁ 11 ምስክሮች፣ ዮናታን ወልዴ 5፣ ሰለሞን ግርማ 3፣ እና ባህሩ ደጉ እና ተስፋዬ ተፈሪ እያንዳንዳቸው 8 ምስክሮችን ጠርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም በአንደኛ ተከሳሽ ለምስክርነት የተጠሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲቀርቡ አለመደረጋቸው ታውቋል፤ በተጨማሪም በእስር ቃሊቲ የሚገኙትና ለምስክርነት የተጠሩት አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽን ማረሚያ ቤቱ ለተከታታይ ቀናት ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢተላለፍለትም ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡
በዋናነት ተከሳሾች በማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ በነበሩበት ወቅት የደረሰባቸውን አስከፊ የምርመራ ሁኔታና በዚሁ ምክንያት ተገድደው ስለሰጡት ቃል የሚመሰክሩ ምስክሮችን አሰምተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ በምርመራ ወቅት አብረዋቸው ታስረው የነበሩና በኋላ ላይ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው ቀርበው የመሰከሩ ግለሰቦች እንዴት ተገድደው በሀሰት እንደመሰከሩባቸው ያስረዱልናል ያሏቸውን ምስክሮች አስደምጠዋል፡፡
ተከሳሾች የተከሳሽነት መከላከያ ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ የሰጡ ሲሆን፣ በተለይ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ህዳር 16/2008 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል፣ የቀረበበት ክስ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው (politically motivated) እንደሆነና በምርመራ ወቅትም በፖሊስና ደህንነት ከተከሰሰበት ጋር በማይገናኝ መልኩ ‹‹ምርጫ 2007ን ለማደናቀፍ ቡድን አደራጅተሃል›› በሚል ሲመረመር እንደነበር አመልክቷል፡፡
ዘላለም በሰጠው ቃል የጸረ-ሽብር ህጉ አሸባሪዎችን ለመከላከልና ለመቅጣት ሳይሆን የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ ዜጎችን እና ጋዜጠኞችን ለማጥቃት እየዋለ እንደሆነም አስረድቷል፡፡ ‹‹በእኔ እምነት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውና ግንኙነት አለህ በሚል የተከሰስኩበት ድርጅት አሸባሪ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሆኖም ግን እንደ እኔ አይነቶችን ለማጥቃት መጠቀሚያ እንዲሆን ሊፈረጅ ችሏል›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ለተከታታይ 41 ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ክፍል በማዕከላዊ እንዳሳለፈና ለአንድ ወር ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኝ እንደተደረገ የተናገረው ዘላለም፣ ‹‹ለለውጥ የሚታገሉ ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ላለማሳደር የደረሰብኝን በደል ሁሉ እዚህ መዘርዘር አልሻም›› ሲል ገልጹዋል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎችም ተከሳሾች በሰጡት ቃል በማዕከላዊ አስከፊ ምርመራ እንደተደረገባቸው አስረድተዋል፡፡
በዚህ መዝገብ የተካተቱት አቶ ባህሩ ደጉ እስካሁን ምስክሮቻቸውን አቅርበው ያላሰሙ ሲሆን፣ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ እና 6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ ደግሞ ቀሪ ምስክሮቻቸውን የሚያሰሙ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ህዳር 17/2008 ዓ.ም ‹‹ዳኞች አልተሟሉም›› በሚል ቀሪ ምስክሮችን ማሰማት ባለመቻላቸው ለህዳር 24/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚሁ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ እንዲሁም መምህር አብርሃም ሰለሞን በዚሁ ችሎት ነጻ መሆናቸው ቢበየንም በአቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው እየተከታተሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡

Source: 
ነገረ ኢትዮጵያ

Saturday, November 21, 2015

የብአዴን በዓል ለአማራ ህዝብ ምኑ ነው? ህዳሴ? ኩነኔ? ከቂሊንጦ በዘመነ ምህረት

(ዘመነ ምህረት የመኢአድ ም/ፕሬዘዳንትና የጎንደር ከተማ ተወላጅ ናቸው።፡ በሽብርተንነት ክስ ተከሰው እየተሰቃዩ ካሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው። አቶ ዘመነ የአንድኒት ምህርት ባለቤት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸው)
ይድረስ ለሀፍረተ ቢሱ ብአዴን እና ለ35ኛ በዓል አክባሪዎች
(ግልፅ ደብዳቤ ከቂሊንጦ እስር ቤት)
ፅሁፍ ዝግጅት - ዘመነ ምህረት (የቀድሞው መኢአድ ም/ፕሬዝደንት)
(አቶ አሸናፊ አካሉ አበራ ሀሳብን በማንሳት አግዞኛል)
ይህንን ፅሁፍ በአማራ ስም አማራውን ለሚያቆስለውና ለህወሓት ስሪት ለሆነው ብአዴን አመራሮችና አባላት ልፅፍ ስሰናዳ ለፅሁፉ መነሻ የሆኑት ሁለት ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነሱም፡-
1ኛ. አቶ አለምነው መኮነን (የአብአዴን የህዝብ ግንኙነት) በ01/02/08 ዓ.ም በአማራ ክልል ቴሊቪዥን ስለ 35ኛው የብአዴን በዓል አከባበር የሰጠው መግለጫ፤
2ኛ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ጭቆና፣ በደሉን የሚሰማና አለሁ ባይ ተቆርቋ ተቋምም ሆነ መሪ አለመኖሩን ለማሳወቅ ነው፡፡
የጥንታዊና የመካከለኛውን ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ባለበት ትተን ከዘመናዊው ታሪክ ብንነሳ አብዛኛው ዘመን ገዥና የገዥ መደብ ሆኖ ኖሯል ተብሎ የሚወቀሰው የአማራ ህዝብ ነው፡፡ እገሌ የሚባለው መሪ የእገሌ ብሄር ተወላጅ እንጅ የገሌ አይደለም የሚባለው ዘር ቆጠራ ውስጥ ለመግባት አይደለም አነሳሴ፡፡ በዚህ ፅሁፍ በገዥና የገዥ መደብ ስም በአማራው ላይ በደረሰውና እየደረሰ ባለው ሰቆቃ እና አማራውን ወክዬ ስታገል 35 አመት አስቆጥሬያለሁ የሚለው ብአዴን ህዝቡን እንደማይወክል ለመሞገት ነው፡፡
የአማራ ህዝብ ትናንት ‹‹አማራ›› በተባሉ ገዥዎች፣ ዛሬ ደግሞ ‹‹አማራ ጨቆነን›› ባይ ባለጊዜዎች የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆኗል፡፡ እየሆነም ይገኛል፡፡ አጤ ምኒልክ በኦሮሞና ደቡብ ፈፀሙት በተባለው ግፍ በአማራ ህዝብ ላይ ጣት ሲጠቆም፣ አጤ ዮሃንስ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላ ምላሳቸውን ስለቆረጧቸው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ትግራይን በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ አይሆንም?
ዛሬ እነ ጃዋር ሞሃመድ፣ መኩሪያ ቡልቻ፣ መሃመድ ሀሰን፣ የተባሉት ‹‹ምሁር›› ነን ባዮች በሚፈሰው የዘውግ ፖለቲካ ተንሳፍፈው በሚነፉት ድስኩር በስመ አማራ ስንቱ ከቤት ንብረቱ ተፈናቀለ፡፡ ተሰደደ፡፡ ተገደለ፡፡ ለሆነው ሁሉ ጥናት ተደርጎ የሚጠየቅ አካል ቢኖር የብአዴን አመራሮች ወክለንሃል በምትሉት ህዝብ ላይ ስለደረሰውና ስላደረሳችሁት ሁሉ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች በሆናችሁ ነበር፡፡ ከእናንተ ህሊና አልባ ህይወት የእኛ በአካል መታሰር በስንት ጣዕሙ! በእርግጥ ታሪክ ፍርዱን መስጠቱ አይቀሬ ነው፡፡
ጅብ ከሄደ....
=====
አቶ አለምነው መኮንን በቴሊቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የ35ኛ ዓመት በዓልን ማክበር ያስፈለገበትን ዓላማ ሲዘረዝሩ ለእሳቸው እኔ አፈርኩ፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
"• የኢህዴንን ወደ ብአዴን መቀየር አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ
• የአማራ ህዝብ ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ያደረገውን አስተዋፅኦ ለወጣቱ ለማሳወቅ፣
• የአማራ ህዝብ ጨቋኝ አለመሆኑን ለማስገንዘብ"
ይህን ባየሁ ጊዜ ታዲያ ‹‹እኒህ ሰውዬ ከጤናቸው ይሆኑ?›› የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ ‹‹የትምክት ለሃጩን ሳያራግፍ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ....›› ብለው በአማራው ላይ የተፉት ምራቅ ሳይደርቅ ምን የሚሉት መገልበጥ ነው ለአማራው ተቆርቋሪ መምሰል? የአማራው ህዝብ ጨቋኝ አለመሆኑን ለማስገንዘብ ስትሉስ ጨቋኝ እየተባለ ይህን ያህል ጊዜ ፍዳውን ሲያይ፣ ሲረገጥና ሲሰቃይ የት ነበራችሁ? ጨቋኝ ላለመሆኑ ጥናት እያጠናችሁ? እነ በረከት ‹‹የአማራን ትምክት እናስታግሳለን›› ሲሉ የት ነበራችሁ? የአማራ ህዝብ ለአንድነት ያደረገው ተጋድሎስ የሚጀምረው ከ35ኛ በዓላችሁ በኋላ ይሆን?በደል ለበዳዩ ምኑ ነው?
የብአዴን አባላት ሆይ!
============
ወክለንሃል እያላችሁ የምትገድሉትና የምታስገድሉት፣ የምትጨቁኑትና የምታስጠቁት፣ የአማራ ህዝብ ላይ የደረሰው ሁሉ ባይሰማችሁ አይገርምም፡፡ እናንተ የበዳዩ እንጅ የተበዳዩ፣ የጭቁኑ፣ የመከረኛው ህዝብ አካል አይደላችሁምና፡፡ በምቾትና በድሎት ችላ ብትሉትም እራሳችሁ የምታውቁትን የህዝብ በደል ላስታውሳችሁ፡፡
• ‹‹ኤርትራ/ትግራይ በገዥው የአማራ ህዝብ ቅኝ ግዛት ተይዟል›› የሚለውን የሻዕቢያንና የወያኔን ማንፌስቶዎች ተቀብላችሁ፣ አብራችሁ ለመስራት አልተስማማችሁም? ይህስ የዛሬው ፕሮፖጋንዳችሁ ጋር ሙሉ በሙሉ አይጣረስም?
• ኢህዴን ወደ ብአዴን ተቀይሮ የአማራ ህዝብ ወኪል መስሎ ሲቀርብ የትኛው የአማራ ተወላጅ ይሆን መሪ የሆነው? በረከት ስምኦን? ተፈራ ዋልዋ?..... ጀኔራል ኃይሌ ጥላሁን ጥርስ ተነክሶበት እንዲጉላላ የተደረገው በብአዴን ስብሰባ ላይ ‹‹ብአዴን ውስጥ የአማራ ተወላጅ የለም›› ብሎ በመናገሩ አልነበረም? በ1987 ዓ.ም ማርቆስ ላይ በተደረገው ስብሰባ ስንቱን የአማራ ተወላጅ ለህዝብ ይቆማል ተብሎ ከብአዴን አላባረራችሁም? ስለ ሙሉዓለም አበበ ግድያስ ምን እየተባለ ይሆን?
• ያለ ህዝብ ፈቃድ የወልቃይትና ሁመራ መሬት ከጎንደር፣ አላማጣ፣ ራያ ቆሞ፣ ኮረም፣ ከወሎ በመንጠቅ ለህወሓት ለመስጠት ሲወሰን፣ አብዛኛዎቻችሁ እሺ ብላችሁ አልተቀበላችሁም? የተላከላችሁን ውሳኔስ አላፀደቃችሁም?
• ጓንግና ጓንግ ባሻገርን፣ ኮር ሁመራን፣ ወደቁራን፣ ገላሎባን፣ ስፋዋን፣ ባህረ ሰላምን፣ መተማን፣ ቋራ ከቁጥር 1-8 እና ነብስ ገበያን ለሱዳን የሰጣችሁት ለአማራ ህዝብ ስለምትታገሉ ነው? በእናንተ ‹‹ጥረት›› ነገ ታሪክ መፅሃፍ ላይ የአጤ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታ ሱዳን ልታደርጉት ነው፡፡
• የአማራ ክልል ብቻ ተለይቶ በ1987 ዓ.ም አርሶ አደሩ በሙሉ በነፍስ ወከፍ የያዘውን መሳሪያ እንዲቀማ የተደረገው በሌሎች ክልሎች የተያዘው መሳሪያ ስለማይተኮስ ወይንስ አማራ በኢትዮጵያ ስጋት ስለሆነ ራቁቱን መቅረት አለበት ብላችሁ ስለምታምኑ?
• በ1989 ዓ.ም በአማራ ክልል በተካሄደው የመሬት ‹‹ሽግሽግ›› ቢሮክራትና ቅሬተ ፊውዳል በሚል ፍረጃ ብዙሃን መሬቱ ሲነጠቅ፣ በድህነት እንዲማቅቅም ሲደረግ፣ ያኔ ነጭ ለባሽ የነበረው የጎጃም ህዝብ ያቀረበው ቅሬታ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተቀባይነት ቢያጣ ‹‹ጎጃም አዘነ›› የሚል ቅፅል የወጣለትን ልብስ መልበስ የጀመረው በእናንተው ዘመን አይደለም? ይህ ህዝብ መሬቱ ተነጥቆ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት ደርግ ይገዛ የነበረው አማራን ብቻ ስነበር ይሆን?
• አይናችሁ እያየ ንብረቶች ወደ ትግራይ አልተጋዙም? ሌላው ይቅር፤ ጣሊያን የሰጠውና ጎንደር ላይ ሀይል እንዳይቋረጥ ያግዝ የነበረው ግዙፍ ጀኔሬተር ተነቅሎ ሲወሰድ የት ነበራችሁ? ደርግ ለቴክኒሻኖች ማስተማሪያ ይጠቀምባቸው የነበሩ በርካታ ዘመናዊ ማሽኖች፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙ የነበሩ ሜሪኩሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ወደ ትግራይ የተጓዙት እናንተ ‹‹የአማራ ወኪል ነን›› ባላችሁበት ወቅት አይደለም? አፈር ሳይቀር እንደተጫነ የማታውቁ ሆናችሁ ነው?
• የአማራ ተወላጅ ሴቶች መሃን የሚያደርግ ክትባት ሲሰጣቸው፣ ዘር ማጥፋት አንዱ አካል መሆኑን ከእናንተ የተደበቀ ነገር ኖሮ ነው?
• የምታመልኩት ህወሓት መራሽ መንግስት ነፍጥ አንጋቢዎቹ ሳንጃ፣ ጎርቢጥ ላይ የ14 ሰዎችን ደም ካፈሰሰ በኋላ ከግድያው ያመለጡ ሰዎች በምሬት የአርበኞች ግንባርን መመስረታቸው ለእናንተ ይጠፋችኋል? ምን አልባት በድሎት ከዘነጋችሁት በወቅቱ የአርማጭሆ አስተዳደርና በ2004 ዓ.ም የጎንደር ከተማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊን ጠይቁት፡፡ አስከሬናቸው ሳይቀበር ውሻ እንዲበላው ነበር የተደረገው፡፡
• በወቅቱ በምስራቅ አፍሪካ ከነበሩት ሁለት የቀዶ ጥገና ሀኪሞች አንዱ በኢህአዴግ እስር ቤት ማቅቀው የሞቱት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ አቶ አሰፋ ማሩን የመሰሉትን ምሁራን ማን ገደላቸው? ጠንካራ የነበረው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት ለምን ታሰሩ? ለምንስ እንዲሰደዱ ተደረገ ? ጭቆናን የተቃወሙ የአማራ ተወላጅ ምሁራን ሲሰደዱ፣ ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ እናንተ የት ነበራችሁ?
• በ1997 መለስ ዜናዊ ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ የአማራ ክልል የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ድሆችና መንገድ ላይ የወደቁት በሽተኞች ከባህርዳር ከተማ ተለቅመው፣ በመኪና ተጭነው የት እንደተጣሉ አታውቁም?
• ‹‹አማራ ጨፍጫፊ›› ነው በማለት ለዚሁ ቂም መፈልፈያ ይሆን ዘንድ የሲዳማ ባህል አዳራሽ፣ የአኖሌ ሀውልት ማቆም፣ በስርዓተ ትምህርት ደረጃም መቅረፅ፣ ማሰልጠኛ ማንዋል አዘጋጅቶ ጥላቻን በስልጠና መልክ መስጠት ምን የሚሉት ቢሂል ነው? በተለይ ተወካይ ነን ለምትሉት! እንደለመዳችሁት ‹‹አናውቅም!›› እንዳትሉ ደግሞ ስልጠናውን የሚሰጡት እነ አዲሱ ለገሰ፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ በረከት ስምኦንና ፣......ሌሎችም አመራሮቻችሁ ናቸው፡፡
• በአርባጉጉ፣ በቴፒ፣ በጅማ፣ በበደኖ፣ በጉራፈርዳ፣ በቤንሻንጉል እና በጋምቤላ አማራ በመሆናቸው ብቻ የተፈናቀሉት፣የተገደሉት፣ ‹‹ሀገራችሁን ግቡ›› የተባሉት፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ሀገር አገኛችሁላቸው?
• የህዝቡን አንድነት ለማዳከም አብሮ የኖረውን የቅማንት፣ የአገው... ከፋፍላችሁታል፡፡ የቅማንት ማህበረሰብም በጣና አካባቢ የራሱ ግዛት እንዲኖረው እየሰራችሁ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ሴራችሁ የአማራ ህዝብ ወኪል ስለሆናችሁ ነው?
• የተለያዩ ፖሊሲዎች ሲሞከሩ የአማራ ህዝብ እንደ አይጥ መሞከሪያ ይሆናል፡፡ ‹‹ምርጥ ዘር››ም ሆነ የትምህርት ፖሊሲ (ስምንተኛ ክፍል ድረስ በአማርኛ) የሞከራችሁት የት ነበር? አብዛኛዎቹን ፖሊሲዎች በአማራ ላይ ሞክራችሁ አይደለም ድክመታቸውን ተለካ የተባለው?
• የንግድ ተቋማት፣ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች፣ በማን እጅ እንደሆኑ እናንተ አጥታችሁት ይሆን? ይህንን ለማወቅ ጎንደርን ብቻ መጎብኘት በቂ ነው፡፡ ካፍቴሪያዎች፣ ሱቆች፣ ሆቴሎች፣ ህንጻዎች.. የሚተዳደሩት በህወሓት ደጋፊዎችና አባላት አይደለም? በአርማጭሆ፣ ቋራና መተማ ለም መሬቶች በህወሓት ቁጥጥር ስል አይደሉም? በክልሉ የጉምሩክ ቢሮ ቀዳሚዎቹ የስልጣን ቦታዎች ለማን የተተው ናቸው? ለዋቢነት ከ2004 -2005 በጎንደር ከተማ ንግድ ፅ/ቤት በመለስና በምክትሉ አባዲ መካከል ‹‹ለምን ከ500 በላይ የትግራይ ተወላጆች የያዟቸው የንግድ ተቋማት ያለ ፈቃድ ይሰራሉ?›› በሚል የተነሳውን ግጭት መለስ ብላችሁ አስታውሱ፡፡
• ሱዳናውያን ድንበር እየጣሱ የሚያቀጥሉትና የሚዘርፉትን የህዝብ ንብረት ቸል ማለታችሁ ሳይበቃ፣ በ2007 ዓ.ም ከእንፍራንዝ ወደ ሮሮታ አሳፍርሻለሁ በሚል ኩላሊቷን አውጥቶ፣ ገድሎ በመጣል፣ ሊሰወር ሲል ሀሙሲት ላይ በህዝብ ርብርብ የተያዘውን ሱዳናዊ በመቶ ሺህ ብር ክፍያ ያውም ጥቃት እንዳይደርስበት በመከላከያ ታጅቦ እንዲወጣ ያደረጋችሁት ለአማራ ህዝብ ወኪል ስለሆናችሁ ነው? ይህን ድርጊት የተቃወሙትን ወጣቶች ያሰራችሁት ለማን ስለቆማችሁ ይሆን?
‹‹አሸባሪው›› አማራ
===========
ዛሬ አማራ ማለት አሸባሪ ተብሎ ተፈርጇል፡፡ ከደህንነት ቢሮዎች እስከ ቂሊንጦ እስር ቤት፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ፣..... ድረስ ያለውን አማራ በመሆኑ ብቻ እየተሰቃየ ያለውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እኔ በምገኝበት ቂሊንጦ፣ ዞን አንድ ዘርዝሬ የማልዘልቀው (ወጣቱን ልተወውና) ለአቅመ አዳም ያልደረሱት ገብናናው ጨቅሌ፣ አብዩ ተስፋ፣ ጀጃው ኃይሌ፣ ዶክተሩ ባዬ እድሜያቸው ከ14 አመት የማይበልጡ ህፃናት ናቸው፡፡
የ‹‹የዘርህ ያንዘረዝርህ››ን ብሂል የሚከተሉት የወቅቱ ገዥዎች መሰሪያዎቻቸው ደህንነት ተብዬዎቹ ጎንደር ብልኮ አካባቢ ከሚገኘው የደህንነት ፅ/ቤት፣ ባህርዳር ኢሜግሬሽን (ደህንነት) ፅ/ቤት፣ እስከ አዲስ አበባው ማዕከላዊ የሚያደርሱት ግፍና በደል ላየው ይቅርና ለሰማው የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ አማራ መሆን ወንጀል፣ ሽብር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ‹‹የምኒልክ ዘር፣ ጥንብ አማራ፣ ወራዳ አማራ....›› እያሉ ጉድጓድ ላይ ጥለው ሽንት መሽናትና ምራቅ መትፋት፣ ራቁትን መግረፍ፣ ‹‹የትምክተኛው አማራ ዘር መጥፋት አለበት›› እያሉ ብልትን መቀጥቀጥ፣ ‹‹አማራን ሱሪውን አስወልቀነዋል፣ ሱሪህን አውልቅ›› እያሉ ማንገላታት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ተቋማት ውስጥ በአማራ ላይ የሚደርሱ የዕለት ተዕለት ግፎች ፀሃይ ወጥቶ የመግባትን ያህል ተለምደዋል፡፡ ‹‹መለስ ጀግና፣ ታማኝ በየነ እና አበበ ገላው ውሻ ናቸው በል›› እንዲሁም፣ ‹‹ትግርኛ ተናገር!›› በሚል የሚደርሰው ድብደባ፣ የሰዎቹን የውስጥ ጭንቅላት አሳይቶናል፡፡
ይህ ሁሉ ጉድ የሚደርሰው የመተማ ተወላጅ በሆነው ደርሶ አያል (ባህርዳር ላይ)፣ እና አሸናፊ (የጣቁሳ ተወላጅ) በሆኑት የብአዴን /የህወሓት ተለጣፊዎች እንዲሁም በትግርኛ ተናጋሪ ደህንነቶች ነው፡፡ ባህርዳር ላይ በብአዴንና በህወሓት ደህንነቶች አማራ በግፍ ሲረገጥ እዛው ቁጭ ብሎ የአማራ ተወካይ ነኝ ማለት በጣም ያሳዝናል፡፡ ስላቅም ነው፡፡
ብአዴን፡- ሰው በላው ድርጅት
===============
ይህንን ፅሁፍ ሳዘጋጅ ሞኝነት ቢጤ እንደተሰማኝ አልክድም፡፡ ለራሱ አባል ያልሆነው ብአዴን እንዴት የህዝብን ጥቅም ሊያስከብር ይችላልና የሚል መጠይቅ ውስጥ በመግባቴ፡፡ እስኪ ሰው በላው ድርጅት የበላቸውን አባላት ላስታውሳችሁ፡-
• መላኩ ፈንታ፡- የቀድሞ ጉምሩክ ዳይሬክተር የህወሓት የበላይነት ላይ ጥያቄ በማንሳቱ ዛሬ መገኛው ቃሊቲ እስር ቤት ሆኗል
• ብ. ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ ብ. ጀኔራል አለማየሁ፣ ኮሌኔል አሳምነው ፅጌ፣ በ2001 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ልትፈፅሙ አሲራችኋል በሚል እስር ቤት ይገኛሉ
• ሙሉ ዓለም አበበ፡- በ1987ቱ የማርቆስ የብአዴን ስብሰባን ተከትሎ አይደለም የተገደለው?
• ብርሃኑ፡- የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበረውና በአማራው ላይ የሚደርሰውን በደል ዘግይቶ በመንቃቱ በፖሊስ አባላት ‹‹የት ነበርክ›› የሚል የቅፅል ስም የተሰጠው፣ የአልማ ፅ/ቤት የተቃጠለበትን ሁኔታን ሲያጣራ ግልፅ ባልሆነ መንገድ መገደሉን ዘነጋችሁት? በዚህ ጉዳይ እነ አቶ ህላዊ የሆነ ነገር ማለት ይገባቸዋል፡፡ ጠይቋቸው!
• ጀኔራል አበባው ታደሰ፡- አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ሳይታወቅ፣ በከተማ የቁም እስር ተገሎ እንደሚኖር አታውቁም ይሆን?
• ነባር የተባሉት ‹‹የብሄር ተዋፅኦ›› በሚል፣ ለምሳሌ ያህል በ2005-2006 ከሻንበል በላይ ያሉት የሰራዊት አባላት መመንጠራቸው ለእናንተ ድብቅ ሆኖ ነው?
• በቅርቡ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አጃቢ የነበረው ኢንስፔክተር አበበ የኋላ ሶስት ራሱን አሸባሪ ተብሎ ቂሊንጦ ተቀላቅሏል፡፡ የታሰረበት ምክንያት አቶ ገዱም ሆነ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ዘውዱ ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ የክልሉ መንግስት አጣርቶ ‹‹ችግር የለበትም›› ብሎ ሲፈታው በፌደራል ደህንነቶች ጫና ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ታስሯል፡፡ በወልቃይትና ጠገዴ፣ በትግራይና አማራ ክልል መካከል በታህሳስ 2007 ዓ.ም ተነስቶ በነበረው ግጭት ተሳትፏል በሚል በህወሓት ጥርስ ውስጥ መግባቱን ብዙዎቻችሁ ታውቃላችሁ፡፡
ብአዴን እንደ ጉፈላ ላም
=============
ታዲያ ብአዴን ማን ነው? ማንንስ ወክሎ ነው? ብዬ ሳስብ የጉፈላ ላም ትዝ ትለኛለች፡፡ አንዲት ላም ወልዳ ጥጃዋ ከሞተባት ገበሬው የጥጃዋን ቆዳ ይገፍና ቆዳው ላይ ሳር ሰግስጎ ጥጃ አስመስሎ ይሰፋዋል፡፡ ሰው ሰራሽ ጥጃዋ ላይ አሞሌ ይቀመጥና እናቷ ጨውን እየላሰች፣ በሰው ሰራሽ ጥጅ እየተታለለች ወተቷ ይታለባል፡፡ ለእኔም ገበሬው ህወሓት፣ ሰው ሰራሽ ጥጃው ደግሞ ብአዴን ነው፡፡ በሰው ሰራሽ ጥጃ ወተቱ የሚታለበው ደግሞ የአማራ ህዝብ ነው፡፡ አሁን ላሚቱ በሰው ሰራሽ ጥጃ መታለሏን አቁማ አዲስ ጥጃ ልትወልድ፣ የታሰረችበትን ገመድ በጥሳ የራሷን ልጅ ልታጠባ የግድ ነው፡፡ ሰዓቱም ነው፡፡
በተለይ ወጣቱ ጥጃ ሆነህ እንደ እናት ያቀፈህን ህዝብ ወክለህ የምትቆምበት፣ የተጠመደብህን ቀንበር ሰብረህ የምትጥልበት ወቅት ነው፡፡ የህወሓት ስሪት የሆነው ብአዴንን ‹‹አትወክለኝም፡፡ ነቅቼብሃለሁ›› የምትልበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ግፍ፣ በደልና ጭቆና ይበቃል፡፡ አሁን የአማራ ህዝብ ጉዳይ የዴሞክራሲ ሳይሆን የመኖር ያለመኖር ጉዳይም ጭምር ሆኗል፡፡
በ1997 ዓ.ም ኢህአዴግ ‹‹ኢንተርሃምዌይ›› የሚለውን ክፉ ቃል ሲጠቀም ከራርሞ፣ ሰሞኑን ደግሞ እነ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተጠቅሞበታል፡፡ አሁንም ‹‹እገሌ ሲጨቁንህ ነበር›› እያሉ ነው፡፡ እናም ብአዴንን ሆይ! በጉፈላ ላም ስመስልህ ከገዳዮች ጋር አብረህ በመሆን የገደልከው፣ ያስጨረስከው፣ ታሪክና ማንነቱን ያዋረድከውን ህዝብ ከ35 አመት በኋላ አዳኝ፣ ወኪሉ መስለህ መቅረብህ ባይዋጥልኝ ነው፡፡ እንደ ቅዱስ መፅሃፍ አርዕዮስ ሁለት ምላስ ሆናችሁ ትናንት ሌላ፣ ዛሬ ሌላ ትዘባርቃላችሁ፡፡ መዘባረቃችሁ ከውስጥ አለመሆኑንም እሩቅ ሳንሄድ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ‹‹ለሃጩን እያዝረከረከ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ ትምክት የሚተፋ›› ብሎ የተሳደበውን አቶ አለምነው መኮንን በአመራር ደረጃ ያውም የብአዴን የህዝብ ግንኙነት አድርጎ ማስቀመጡ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፡፡ ጉዳዩ ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ›› ነው፡፡
በዓሉ የህወሓት ወይንስ የብአዴን
=================
35ኛ በዓላችሁን ልታከብሩ ሸር ጉድ እያላችሁ መሆኑን እስር ቤት ሆኘም በቴሊቪዥን እየተከታተልኩ ነው፡፡ በዓሉ ከብአዴን ምስረታ ጀምሮ ተቆጥሮ መሆኑ ደግሞ ግርምትን ይጭራል፡፡ ለመሆኑ የኢህዴን/ብአዴን አላማና ተልኳቸው ለየቅል አይደለም? ኢህዴን ተቀጥቅጦ ብአዴን የተባለው መአህድ መመስረቱን ተከትሎ አልነበረም? እንደ እኔ በዓሉን ማክበር ያስፈለገው፡-
• የስልጣን እድሜን ለማራዘም
• ጭቆናው ያንገፈገፈውን ህዝብ ግፊት ለማቀዝቀዝ
• የኢትዮጵያ አንድነትን ወደኋላ ለመጎተት
• ከህወሓት ጋር ቁመት በመለካካት፣ እኩል እንደሆኑ ለማስመሰል ነው
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ ‹‹ኢህዴን/ብአዴን የማንም ውራጅ አይደለም፡፡›› ቢሉም አሁንም ግን ብአዴን የህወሓት ውራጅ ነው፡፡ በመሆኑም ብአዴን የአማራነትን ጭምብል አጥልቆ የቆመ በመሆኑ በዓሉ የህወሓት በዓል ነው፡፡ የህወሓትና የብአዴን ልደት በ11 የሚከበር በመሆኑም በአንድ ላይ ቢያከብሩትም ባልከፋ፡፡
ማን ይናገር......
የአማራ ህዝብ ይህን ያህል ገፈት ሲቀምስ ቆምኩለት የሚለው ብአዴን ዛሬ በአዲስ ስልት ‹‹ጨቋኝ አይደለህም›› ‹‹ለዴሞክራሲና አንድነት ትተጋለህ››....በሚል አዲሱን ወይን በአሮጌው አቅማዳ ይዞ፣ ከፊት ለፊት ቆሞ ሲያርድና ሲያሳርድ የነበረው ህዝብ በአዲስ ስልት ከጀርባ ቆሞ ሊያርደውና ሊያሳርደው መዘጋጀቱን የሚያሳይ ነው፡፡
ዛሬ በየሄደበት ‹‹ጡት ቆራጭና ጨቋኝ›› እየተባለ የሚሳደደውና የሚሰቃየው ህዝብ በአማራነቱ፣ በኢትዮጵያዊነቱ፣ ወኪል ቢኖረው ኖሮ ብአዴን ፅ/ቤት ላይ ተሰብስቦ ሲያለቅስ ምላሽ ባገኘ ነበር፡፡ እነ መላኩ ፈንታ ‹‹ምላሽ ይሰጣቸው›› በማለታቸው ወደ ዘብጥያ ተወርውረዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አማራ በመሆናቸው ብቻ በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው (አማራ ማለት ሽብር ሆኗልና) ጥቂት የቂሊንጦ ነዋሪዎችን ስም ዝርዝር ላካፍላችሁ፡-
1. በእነ አለላቸው አታለለ የክስ መዝገብ 5 ሰዎች
2. በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
3. በእነ ዘመነ ምህረት የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
4. በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ 16 ሰዎች
5. በእነ አበበ ካሴ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
6. በእነ አስማረው አሰፋ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
7. በእነ ታደሰ ፈረደ የክስ መዝገብ 5 ሰዎች
8. በእነ ገ/ሚካኤል ገ/ስላሴ የክስ መዝገብ 9 ሰዎች
9. በእነ ነገደ ሸዋቀና የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
10. በእነ አጥናፉ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
11. በእነ አበበ ተመስገን የክስ መዝገብ 12 ሰዎች
12. በእነ መብራቴ ይርጋ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
13. በእነ ሁሴን አሊ የክስ መዝገብ 4 ሰዎች
14. በእነ አበበ የኋላ የክስ መዝገብ 4 ሰዎች
15. በእነ አዳሙ ታዬ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
16. በእነ ፀጋው አለሙ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
17. በእነ ቸሬ ተክሉ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
18. በእነ ሰጠኝ ሙሉ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
19. በእነ ማስረሻ ሰጠኝ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
20. በእነ አንተነህ የክስ መዝገብ 2 ሰዎች
21. በእነ አቤል ከበደ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
22. በእነ አብርሃም ሞገስ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
23. በእነ ማስረሻ ታፈረ የክስ መዝገብ 9 ሰዎች
24. በእነ ሊጋባው ግርማ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
25. በእነ ፋንታሁን የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
26. በእነ ተፈራ በላይ የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
27. በእነ አስቻለው የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
28. .........እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡
ከዚህ በታች የምዘረዝራቸው ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ የሚገኙ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ናቸው፡፡
1. አለማቸው ማሞ የ60 አመት አዛውንት
2. ፀጋው ካሳ የ78 አመት አዛውንት
3. ቢሆነኝ አለነ የ60 አመት አዛውንት
4. አዋጁ አቡሃይ የ75 አመት አዛውንት
5. የሻለቃ ሰጠኝ ሙሉ የ75 አመት አዛውንት
6. ወርቁ አያሌው የ67 አመት አዛውንት
7. ይርጋ አሳምረው የ68 አመት አዛውንት
8. በላይ ብሩ የ68 አመት አዛውንት ናቸው፡፡
ከላይ በስም ከጠቀስኳቸው ውስጥ ማስረሻ ሰጠኝ፣ አንተነህና አቤል ከበደ የአየር ኃይል አብራሪዎች ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር ከሌሎች ጋር የተከሰሱት የአማራ ተወላጆች፣ ከቂሊንጦ ውጭ የሚገኙት (በማዕከላዊ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ፣ አማራ ክልልና ውጡ እየተባሉ በሚባረሩባቸው አካባቢዎች) በስቃይ ላይ የሚገኙትን አይጨምርም፡፡ ይህን ፅሁፍ በማዘጋጅበት ወቅት እንኳን አማራ ወደሚሰቃይበት ማዕከላዊ እስር ቤት ከ100 በላይ የሚሆኑ አዲስ ‹‹ሽብርተኛ›› ወጣቶች ከጎንደርና ጎጃም ተለቅመው እንደገቡ መረጃ ደርሶኛል፡፡ እና የ35ኛው የብአዴን በዓል ለአማራ ህዝብ ምኑ ነው? ህዳሴ? ኩነኔ?
አበቃሁ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ዛሬ ብአዴን የሚያደረገው ፌሽታ ብሄራዊ ዉርድት ነው - የሚሊዮኖች ድምጽ


"የብአዴን የምስረታ በአል በፌሽታ ሳይሆን ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ይከበራል"
ይሄን የተናገሩት አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። የብአዴን ሊቀመንበር።
ነገ ብአዴን 35ኛ በዓሉን በባህር ዳር ያከብራል። ለዚህ በዓል ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገ በስፋት እየተዘገበ ነው።
በአዴን ሲቋቋም ኢሕዴን(የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በሚል ከኢሕአፓ በወጡ ጥቂት ግለሰቦች ፣ በሕወሃት አዝማችነት የተመሰረተ ሲሆን ፣ ህወሃት ስልጣን ሲጨብጥ "ኢትዮጵያ" የሚል ስም ያለበት ደርጅት ማየት የማይፈልጉት እነ መለስ ዜናዊ በሰጡት ትእዛዝ "ኢሕዴን" ወደ "ብአዴን"(ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ተለወጠ። ድርጅቱን የሕወሃት አሽከር ሆኖ፣ ኤርትራዉያን የሆኑ እነ በረከት ስምኦንን መሪው አድርጎ፣ የአማራዉን ብሄረሰብ እወክላለሁ አለ። ለምለም የሰሜን ጎንደር መሬቶች ወደ ትግራይ ተደባለቁ። በደቡብ ጎንደር ምእራብ ጎጃም ቤነሻንጉል የሚል ክልል ተመሰረተ። በዚያ ከሕወሃት ጋር ግንኝነት ያላቸው፣ ገበሬዉ እየተፈናቀለ፣ ሰፋፊ የ እርሻ መሬቶች ተሰጣቸው። ብአዴን እንወክላለን ላሉት ህዝብ መቆም ሳይሆን፣ እንወክላለን ባሉት ህዝብ ላይ ተነሱበት። የሕወሃት ዱላ ሆነው ህዝቡን ገደሉት። አሰሩት፣ አሸበሩት፣ አሰቃዩት።
ብአዴን፣ እወክለዋለሁ ያለው ማህበረሰብ፣ በተለያዩ የአገሪቷ ግዛቶች "አገርህ አይደለም" እየተባለ ሲገደል፣ ሲፈናቀል ዝምታን መርጧል። ከሌሎች ክልሎች መፈናቀልና መገደል ፣ በቅርቡ ተገድለው፣ በጆንያ ተጠቅልለው ተቀበረው እንደተገቡት ወደ አሥራ ሁለት የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን፣ እድል ፈንታ እየሆነ ነው።
ብአዴን፣ እወክለዋለሁ ያለው ማህበረሰብ፣በተከይም በአሁኑ ሰዓት፣ በወሎና በሰሜን ምስራቅ ጎንደር ለክፍተኛ ረሃብና አደጋ ተጋልጧል። ሕጻናት እየሞቱ ነው። ገበሬዎች ተፈናቅለው ወደ ከተማ እየጎረፉ ነው።
ሕዝቡ በዚህ ችግር ላይ ሆኖ እያለ ግን፣ ብአዴኖች በአል ለማክበር፣ ዉስኪ ለመርጨት፣ ዳንኪራ ለመምታት፣ ወደ ሶስት መቶ ሚሊዮን ብር እያቃጠሉ ነው።
በርግጥ ይህ ፣ ብአዴንም ሆነው ጌታው ሕወሃት፣ ለሕዝብ ደንታ እንደሌላችዉ ያረጋገጡበት አንዱና ትልቁ ማሳያ ነው።
ያ ብቻ አይደለም። ነገ ብአዴን የሚያደርገው ፌሽታ በኢትዪጵያ ታሪክ ዉስጥ ትልቅ ጥቁር ነጥብ የሚጥል፣ ብሄራዊ ዉርድት ነው !!!! ዉርደት !!!! ዉርደት !!!! ዉርደት !!!!

‹‹ብ.አ.ዴ.ን.›› የማን ወኪል ነው?

ጌታቸው ሺፈራው
በአገራችን በስፋት ከሚተረክላቸው ፓርቲዎች መካከል ኢህአፓ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይሁንና ‹‹ያ ትውልድ›› ተብሎ የሚነገርለትን ያህል ሳያበረክት በአጭሩ ተቀጭቷል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ከሚነሱት ምክንያቶች መካከል አንዱ በፓርቲው ውስጥ የተነሳው ‹‹አንጀኝነት›› ነው፡፡ በፓርቲው ‹‹የአንጃ›› ታሪክ በነ ብርሃነ መስቀል ረዳና ጌታቸው ማሩ የሚመራው ቡድን የመጀመሪያው ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ አሲምባ ላይ ‹‹በዳግማዊ አንጃነት›› የተረሸኑት ይገኙበታል፡፡ ብ.አ.ዴ.ን. ቀደም የነበሩትን ‹‹አንጀኞች›› በማድነቅ ራሱን ‹‹ሳልሳዊ አንጀኛ›› አድርጎ ይቆጥራል፡፡
ምንም እንኳ ብአዴን የኢህአፓን ታሪክ በታሪክነት ቢወስድም ከኢህአፓ ከወጣ በኋላ በተሸከማቸው አብዛኛዎቹ አቋሞቹ ግን አብሮት የነበረ አይመስልም፡፡ አባል የነበረበትን ኢህአፓን የሚያወግዘው ብአዴን/ኢህዴን በተቃራኒው የኢህአፓ ተቀናቃኝ የነበሩትን ህወሓትና ሻዕቢያ ላይ ምንም አይነት ትችት አያነሳም፡፡ እንዲያውም ህወሓትና ሻዕቢያ የተከተሉት መንገድ ‹‹ዴሞክራሲያዊና ትክክለኛ መንገድ ነው›› ብሎ በአድንቆት ተቀብሏቸዋል፡፡ ይህም ኢህዴን/ብአዴንን የኢህአፓ አንድ አካል ሳይሆን ለሌላ ተልዕኮ አብሮ የቆየ እንደሆነ ጥርጣሬ ያጭራል፡፡
ብአዴንና ኢህአፓ
ብአዴን ኢህአፓ ውስጥ የተፈጠረውን ‹‹አንጃ›› አድንቆ ‹‹ሳልሳዊ›› መሆኑን ቢገልጽም አንጃ ከሚባሉትም ጋር ተመሳሳይ መርህ ሲከተል አይስተዋል፡፡ ኢህአፓ ውስጥ ‹‹በአንጃዎቹ›› ከተነሱት አምስት የሀሳብ ልዩነቶች መካከል ሁለቱን ብቻ ብናይ እንኳ ኢህዴን የሚያምንባቸው አይደሉም፡፡ ‹‹አንጀኖቹ›› ካነሱት ሀሳም መካከል አንደኛው ከደርግ ጋር ጸረ ኢድሃና ጸረ ሶማሊያ ግንባር መፍጠር አለብን የሚል ነው፡፡ ሆኖም ኢህዴንን ያቋቋመው ህወሓት ሶማሊያን እስከ ድሬዳዋ በመምራት ቀዳሚው ድርጅት ነው፡፡ ይህን የህወሓት ድርጊት ኢህዴን አንድም ቀን ተችቶ አያውቅም፡፡ በመሆኑም ኢህዴን ከኢህአፓ ነበረኝ የሚለውን ልዩነትና ከህወሓት ጋር ያለውን ግንኙነት ምክንያታዊ ለማድረግ እንጅ ‹‹አንጃዎች›› ያነሱት ‹‹የጸረ ሶማሊያ ግንባር›› ሀሳብ እንደማይስማማ ለመገመት አያዳግትም፡፡
ሌላኛው ‹‹የአንጀኞች›› ሀሳብ ‹‹በ3ኛው ዓለም ፋሽዝም ሊነሳ አይችልም የደርግ ተፈጥሮም ፋሽዝም አይደለም›› የሚል ነበር፡፡ ምንም እንኳ ብአዴን ‹‹ከአንጀኖቹ›› አንድ አካል መሆኑን ቢገልጽም የኢህዴንን ታሪክ የተረከባት ‹‹ፅናት›› መጽሃፉ አብዛኛው ክፍሏ የደርግን ‹‹ፋሽስትነት›› ነው የምታወራው፡፡ የመጽሃፏ ርዕስ እንኳ ‹‹ከፋሽስታዊ ጭፍጨፋና አፈና ያልተነበረከከው …የተጋድሎ ታሪክ›› የሚል ነው፡፡ ብአዴን በመጽሃፉ ‹‹የኢህአፓ አመራር ግን እነዚህን አብይ ጥያቄዎች ተገቢውን ውይይት ተደርጎባቸው አባላቱ እንዲረኩ የድርጅቱ ዴሞክራሲያዊነትም እንዲረጋገጥ ለማድረግ ፍላጎት አልነበረውም፡፡››(22) ቢልም እሱ ከ‹‹አንጃውም›› ሆነ ከዋናው ኢህአፓ ጋር ይህ ነው የሚባል ተመሳሳይ አቋም እንዳልነበረው ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
ከኢህአፓም ይሁን ‹‹አንጀኖቹ›› ይልቅ ብአዴኖች ቀድሞውንም ለህወሓት ልባዊ ፍቅር እንደነበራቸው ራሳቸው ያሰፈሩት ታሪክ ይናገራል፡፡ የብአዴን መስራቾች ከኢህአፓ ጋር በይፋ የተለያዩት ህወሓት ላይ ምላጭ አንስብም ብለው ነው፡፡ ሆድ ያባውን እንዲሉ ውስጥ ለውስጥ የነበራቸውን ፍቅር ኢህአፓ ከህወሓት ጋር ውጊያ በገጠመበት ወቅት በህወሓት ላይ ምላጭ መሳብ የሚችል ‹‹ጨካኝ›› ልብ እንደሌላቸው አስመስክረዋል፡፡ ‹‹በ1972 ዓ/ም ወደ ወልቃይት ተጠርተው ሄደው የነበሩት ሁለት የበለሳ ሀይሎች ወልቃይት ላይ በተደረገው የኢህአፓና የህወሓት ጦርነት ላይ እንዲሳተፉ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው እንዷ ሀይል አሻፈረኝ ብላ ወደ በለሳ ስትመለስ ሌላዋ ሀይል በጉዳዩ ላይ ባደረገችው ውይይት በመሃሏ ልዩነት ስለተነሳ ከሁለት ተከፍላ ከነበራት 55 አባላት 22ቱ ከሀይሏ ተገንጥለው ወደ በለሳ ተመልሰዋል፡፡ ይህች ጋንታ በበለሳ ዴሞክታሲያዊ ንቅናቄ ታሪክ ውስጥ ጋናታ 22 ተብላ ትጠራለች››(85)፡፡ የብአዴን መስራቾች የኢህአፓ አካል የነበሩት ሁለቱም ‹‹አንጃዎች›› ሲመቱ ምንም ሳይሉ ህወሓት ጋር ጦርነት ሲጀመር ልዩነታቸውን መፈንዳቱ የቆየ ልባዊ ግንኙነት አሊያም ተልዕኮ ካልሆነ በስተቀር አጋጣሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚያ በፊትም በበለሳ፣ ወልቃይትና የትግራይ ከተሞች በርካታ አመራሩ እንጅ ተዋጊው የማያምንባቸው ውጊያዎች ቢካሄዱም የብአዴን መስራቾች ግን ያንገበገባቸው ከህወሓት ጋር የነበረው ጦርነት ነው፡፡
ከጦርነት ባሻገር ኢህአፓ ውስጥ የነበራቸውን አቋም በአንዴ አሽቀንጥረው ከህወሓት አቋም ጋር መላመድ ያልከበዳቸው መሆኑ ደግሞ ኢህአፓ ውስጥ የነበሩ ‹‹ህወሓቶች›› ስለመሆናቸው ጥርጣሬን ያጭራል፡፡ በኢህዴኗ መጽሃፍ ‹‹ከህወሓት ጋር የነበረውን ግንኙነት ጠቅሶ ከህወሓት ጋር ግንባር መፍጠር ይቻል እንደነበር አስምሮበታል፡፡ በአጠቃላይ የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ ያለውን ቦታ ሲመለከትም ህወሓት አንግባው የተነሳችው ጥያቄ ዴሞክራሲ ጥያቄ መሆኑን አስተውሏል፡፡›› ሲሉ ከኢህአፓ ይልቅ ድሮም ለህወሓት ቅርብ እንደነበሩ ያስረግጥልናል፡፡ ኢህአፓና ህወሓት ሲቃቃሩ የብአዴን መስራቾች ‹‹ከኢህአፓ ተገንጥለው ሳይውሉ ሳያድሩ ከሚያዚያ ጀምሮ በወሎ ክፍለ ሀገር በዋግ አውራጃ ውስጥ ህዝባዊ ሰራዊቱን አስገብተው ትጥቅ ትግሉን በአዲስ መሰረት ላይ ጣሉ›› (ፅናት፣ 117)፡፡ ከኢህአፓ ከወጡ በኋላ አዲሱ ተግባራቸውን በትዕዛዝ የጀመሩት ይህኔ መሆኑ ይነገራል፡፡ ኢህአፓ ከሚታወስባቸው ጉዳዮች መካከል ብአዴኖች ‹‹ፅናት›› ባሏት መጽሃፍ መግቢያ ላይ
‹‹ፍጹም ነው እምነቴ
የትግሉ ነው ህይወቴ
ልጓዝ በድል ጎዳና
በተሰውት ጀግኖች ፋና›› በሚል ያስቀመጡት መዝሙር ተጠቃሽ ነው፡፡
ኢህአፓ ‹‹ጽኑ ነው እምነቴ›› ሲል ህወሓት ለተነሳለት የከፋፍለህ ግዛ ስርዓት ሳይሆን ለህብረ ብሄርተኝነት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁንና ብአዴን መዝሙሩን እየዘመረም ቢሆን ጽናት እንደሌለው የህወሓትን ፖሊሲዎች ትክክለኛ እንደሆኑ ይገልጽልናል፡፡ ‹‹በኢህአፓ ምክንያት በጭቁን ህዝቦችና በታጋይ ድርጅቶች መካከል ሊኖር የሚገባውን ህብረት ለመፍጠርም ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ ኢህአፓ ወላዋይና ትምክተኛ ድርጅት ስለነበረ ያደናቀፈውን የጭቁኖች አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳለ ለመገንባት ከህወሓት ጋር በጋራ ባደረገው ትግልም አኩሪ ድሎችን አስመዝግቧል››(139)፡፡ ብሎ ህወሓት ከእነ ምናምኑ ይቀበለዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የብአዴን መስራቾች ከኢህአፓ ለመውጣት ያነሷቸው ከነበሩት መከራከሪያዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በወቅቱ ኢህአፓን ‹‹ትምክተኛ፣ ግትር፣…›› እያሉ የሚወቅሱትም ሆነ ህወሓትን የሚያወድሱበት ‹‹ጽኑ ነው እምነቴ›› ከሚለው ኢህአፓ ይልቅ የህወሓትን ቋንቋ ተውሰው ነው፡፡
ብአዴንና ህወሓት
ከኢህአፓ ይልቅ ለህወሓት መልካም አመለካከት የነበረው ‹‹ንቅናቄው›› ከኢህአፓ ተነጥሎ የህወሓትን ድጋፍ ለማግኘት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ‹‹ህወሓት ለመደራጀት በምናደርገው ጥረት ልትተባበረን ትችል ይሆናል፣ ይህ ካልሆነም በመስዋትነት የተገኘው ንብረታችንን ለደርግ ከመስጠት ለህወሓት መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡›› የሚል ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በአሁኑ ወቅት ብአዴን ስልጣንም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች አሳልፎ መስጠትና ህወሓት ያለውን ማስፈጸም በግልጽ የጀመረው በዚህ ወቅት ይመስላል፡፡ በስንክሳራቸው ስላልገለጹትና ህወሓትም ከእሱ ጋር ከሚሆኑ ይልቅ አዲስ መሸጋገሪያ ድርጅት ቢፈጥሩ ይበልጥ እንደሚጠቀም ስላሰበ ይሆናል እንጅ እንደዚህ ፍቅራቸው የህወሓት አንድ አካል ለመሆን ጥያቄ አንስተው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
ሰኔ 20 1972 ንቅናቄው ከህወሓት ጋር ግንኙነት ካደረገ በኋላ (ከዛ በፊት መሰረታዊ ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠረጥሩበት በርካቶች ናቸው) በህወሓት የሀሳብ መሪነት አዲሱ የድርጅት ጉዞውን ቀጠለ፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የህወሓት መሪዎች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በአሁ ወቅት ህወሓት/ኢህአዴግ በአጋር ፓርቲዎች አማካሪም ሆነ እሱ ብቻ የመከረበትን ሀሳብ የሚጭንበት ታሪክም የጀመረው በዚሁ የኢህአፓው ተገንጣይ ቡድን ላይ ነው፡፡ ህዳር 11 1972 ዓ/ም ትግራይ ውስጥ በተምቤን አውራጃ አምባራ ወረዳ ሽልምዕምኒ ቀበሌ ተክራርዋ በተባለ መንደር መስራች ጉባኤው ተቋቋመ፡፡ በዚህ ወቅትም መግባባት የተደረሰበት የድርጅቱ ዋነኛ መስመር ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› እንዲሆን ነው፡፡ ‹‹ከሰኔ 20 ቀን 1972 እስከ ህዳር 7 1973 ለ5 ወራት የተካሄደው ዝግጅት መካከል አንዱ የኢህአፓን የተሳሳተ መስመር በመሻር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቋሞችን የመውሰድ ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡›› (ፅናት፤ 99)፡፡ እንግዲህ የብአዴን መስራቾች ለበርካታ ጊዜ አብረውት ኖረው ‹‹የተሳሳተ›› ከሚሉት የኢህአፓ መንገድ ይልቅ አሁን አርሶ አደሩን ጭምር የሚያደርቁበት የህወሓት ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› እንዲሁ የተቀበሉት በተንበኗ ትንሽ መንደር በተገናኙባት ጥቂት ቀናት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡
ህዳር 11 1972 ተከራዋ ከተባለችው መንደር ውስጥ ኢህዴን ተመሰረተ፡፡ ብአዴን በዚች መንደር የተመሰረተበትን 35ተኛ አመቱን አክብሯል፡፡ የአሁኑ ብአዴን ራሱን ኢህዴን ብሎ ይቆይ እንጅ የህወሓትን መስመር ሳያንገራግር የተቀበለው የምስረታው ጊዜ ነው፡፡ ተከራዋ በተባለችው መንደር ኢህዴን ከህወሓት የተቀበለው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቁንስ ኢህአፓ የሚቃወመውን የኤርትራን የመገንጠል መብትም ተቀብሎ ተመለሰ፡፡ ይሁንና ወደ ወሎና በለሳ ተመልሶ በዚህ ፖሊሲው ከህዝብ ጋር መግባባት እንደማይችል በመታወቁ መለስተኛ ለውጥ እንዲደረግበት ተወሰነ፡፡ በመሆኑም ‹‹የኤርትራ ህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል መብት ያከብራል›› የሚለውን መጀመሪያ ላይ ሳያንገራግር የተቀበለውን መርህ ‹‹የኤርትራ ህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ ነጻነት ያውቃል›› በሚል ግራ አጋቢና ጊዜያዊ አቋም ተክቶ ወደ ስራ ገባ፡፡ በእርግጠኝነት ይህኛውንም ቢሆን ህወሓትን ፈቃድ ውጭ ሊቀየር የሚችል አልነበረም፡፡ ይህን አቋም ስልጣን ሊይዙ በተቃረቡበት ወቅት እንደገና እንዲቀይር ተደርጓል፡፡ ህብረ ብሄራዊነት፣ ከዛም ‹‹አማራን›› የወከለ የሚያስመስለው ስምም ህወሓት አባይን ለመሻገር በሚጠቅም መልኩ የቀረጸው እንደነበር የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ብአዴንና አማራ
ኢህዴን ከተመሰረተ በኋላ አብዛኛዎቹ መስራቾች ከህወሓት ጋር ያለውን ግንኙነትም ሆነ አዲሱን ፖሊሲውን ተቃውሞው ጥለው ወጥተዋል፡፡ ለአብነት ያህል በመስራች ጉባኤው ከተመረጡት 9 አባላት መካከል የቀሩት አምስቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ከህወሓት ጋር ባለው ግንኙነትም ሆነ በአዲሱ አቋም ባለማመናቸው ከትግሉ ወጥተዋል፡፡ ያም ሆኖ ኢህአዴን በህብረ ብሄርነት ስም ለ9 አመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ስልጣን ለመያዝ በተቃረበበት ወቅት ግን ‹‹አማራን›› የወከለ የሚያስመስል ስም ለጥፎ ወደ መሃል አገር ህወሓትን መምራቱን ተያያዘው፡፡
ኢህዴን (ብአዴን) ከህወሓት በሚደረግለት ድጋፍና ትዕዛዝ ዋነኛ መንቀሳቀሻው ወሎና ጎንደርን አድርጎል፡፡ በዚህ ወቅት በእነዚህ አካባቢዎች ህዝቡ በርካታ ችግሮች ተጋፍጦ ከጎኑ ተሰልፎ ተዋግቷል፡፡ ሆኖም ብአዴን ህወሓትን ቤተ መንግስት ካደረሰ በኋላ አብሮት የተዋደቀውን ህዝብ ተመልሶ አላየውም፡፡ ሌላው ይቅርና ከህወሓት ጋር አንዋጋም ብለው ከኢህአፓ ከወጡት ውጭ ህዝብ ላይ የደረሰውን በደል ተነግሮ አያውቅም፡፡ ለአብነት ያህል የሀሙሲትን ጭፍጨፋ ማንሳት ይቻላል፡፡ ኢህዴን/ብአዴን ይንቀሳቀስባቸው ከነበሩት ከተሞች አንዷ የሆነችው ሀሙሲት ከሀውዜን ባልተናነሰ በደርግ አውሮፕላኖች የወደመች ከተማ ነች፡፡ በገበያ ቀን በተደረገው ድብደባ ሰውም ሆነ እንሰሳ አልተመለሱም፡፡ ሆኖም ስለዚች ከተማ ሲወራላት ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የብአዴንና የህወሓት ታጋዮች ህዝቡ በደርግ ላይ እምነት እንዲያጣ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ እንደ ትምህርት ቤት ያሉ የህዝብ መገልገያዎች ላይ በመጠለል አሊያም እንደተጠለሉ በማስወራት በርካታ ተቋማት በደርግ እንዲወድሙ አድርገዋል፡፡ ይህ በሆነበት ግን ህወሓት በአካባቢው የነበሩትን ሀብቶች ማጓጓዙን ተከትሎ ጥያቄ ሲያነሳ ከብአዴኖች የሚሰጠው መልስ ‹‹እናንተ ምን ደረሰባችሁ?›› የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከአስር አመት በፊት ጎንደር ተማሪዎች ከተማው ውስጥ የነበረን አንድ ዘመናዊ ጀኔሬተር በህወሓት መወሰዱን ተከትሎ ባነሱት ጥያቄ ከብአዴን የተሰጠው መልስ ‹‹የተደበደቡት፣ የቆሰሉት፣ የተዋጉት፣ የተጨፈጨፉት›› እነሱው ናቸው የሚል ነው፡፡ ብአዴን እንዱ ህዝብ ለሌላኛው የጦርነት ካሳ መክፈል እንዳለበት ለማሳመን የሚያደርገው ጥረት ህዝብ ከህዝብ ጋር ለማናቆር ሆን ተብሎ የተዘየደ ስልት ነው፡፡ በምሳሌነት የምትነሳው ደግሞ ሀውዜን ነች፡፡ የሀውዜን መደብደብ ዋነኛው ተዋናኝ ህወሓት እንደነበር የቡድኑ ታጋዮች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የሀሙሲት ጉዳይም አንድ ቀን ታሪክ የሚያወጣው ይሆናል፡፡
የወሎና የጎንደር ህዝብ ከጎኑ ሆኖ እንደታገለ ብአዴን ራሱ አይክድም፡፡ ይሁንና ከስም ያለፈ ተግባራዊ ውክል ኖሮት አያውቅም፡፡ ከኢህአዴግ ጎን ተሰልፈው የተዋጉ አርርሶ አደሮች የሚገባውን እንዳላገኘ በምሬት ሲገልጹ ኢቲቪና ኢህአዴግ አቶ መለስን ‹‹የህዝብ ልጅ›› ለማስመሰል ባቀረበው ዶክመንተሪ ላይ ታይቷል፡፡ ይህ ጸሃፊ በተገኘበት አንድ መድረክ ከኢህዴን ጎን ቆመው የታገሉ አርሶ አደሮች አዲሱ ለገሰን ከድተኸናል በሚል በዚህ ጽሁፍ ሊገለጽ የማይችልን ስድብ ሲያወርዱበት ታዝቧል፡፡ ስድብና ወቀሳ የበዛበት አዲሱ ለገሰ በሌላ ወቅት የአርሶ አደሮቹን ቁጣ ያበርዳል የተባለ መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ለማስመረቅ ወደ አካባቢው በሄደበት ጊዜ ህዝቡ መንገዱን ዘግቶ አላሳልፍም በማለቱ ሄሊኮፍተር ከባህርዳር መጥቶለት ሲመለስ ምስራቅ መኮነን አዲሱ ወደ ባህርዳር መመለሱን በመግለጽ ህዝቡን ‹‹አረጋግታ›› እንድትመልስ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ህዝብ ለብአዴን ያለው አመለካከት ጭራሹን የወረደ ነው፡፡
በእርግጥ ብአዴን በአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን አብረውት ወደ ቤተ መንግስት ለገቡት ተዋጊዎችም እንዳልሆነ ተስፋዬ ገብረ አብ አስነብቦናል፡፡ ተስፋዬ ‹‹የጋዜጠኛው ማስታወሻ›› በተሰኘው መጽሃፉ ተፈራ ዋልዋ ‹‹እኛ ኢህዴኖች ውጊያ ላይ ወደ ኋላ በማፈግፈግ መሳሪያ ሲከፋፈል ደግሞ በመንጫጫት እንታወቃለን፡፡ በውጊያ ወቅት ‹‹ህወሓት ይዋጋ እንደ ጦጣ በቆንጥርና በተራራ መሮጥ የለመዱት እነሱ ናቸው ትሉ አልነበርም? ህወሓት ተሰውቶ የያዘውንና የማረከውን መሳሪያ ደግሞ ካልተካፈልን እያላችሁ ታጉረመርሙ አልነበረም? ስለ ስልጣን ከማውራታችሁ በፊት እስኪ ስንቶቻችሁ ናችሁ የተሰጣችሁን ስራ አድምታችሁ የሰራችሁ!?›› በሚል ዳግመኛ ለህወሓት ቆሟል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ብአዴን ያኔ ኢህአፓ ከተገነጠለበት ጊዜ ጀምሮ ከህወሓት የተዋሰውን ቋንቋ ስልጣን ይዞም በስፋት እየተገበረው መሆኑን ነው፡፡ ለህወሓቶች ቆሞ የነበረው ተፈራ ዋልዋ እነ ስብሃት ነጋ ፖለቲካውን በሚያሾሩበት ወቅት አድራጊ ፈጣሪው ህወሓት ‹‹መተካካት›› ብሎ ባመጣው ፖሊሲ ከመድረኩ አርቆታል፡፡
ሻምበል አስረስ የተባለ የብአዴን ካድሬ ‹‹የደራሲው ማስታወሻ›› በተሰኘ መጽሃፉ ደግሞ ህወሓትና ሻዕቢያ ብአዴን ወክየዋለሁ የሚለውን ህዝብ በማን አለብኝነት ሲጨፈጭፉ ምንም ማድረግ አለመቻሉን ይነግረናል፡፡ ካድሬው በ1987 ዓ/ም ለስራ ወደ አዘዞ በሄደበት ወቅት ምሽት ላይ ከፍተኛ ጮኸት ይሰማና ከአንድ ሌላ የህወሓት አባል ጋር ጩኸት ወደተሰማበት ቦታ ያቀናሉ፡፡ በቦታው በደረሱበት ወቅት ያዩት ጉዳይ ግን ለማመን የሚከብድ ነበር፡፡ ‹‹አዘዞ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ፈንጠር ብለው (ለድብደባ) የተሰሩ ቤቶች የታጠቁ የደህንነት ሀይሎች እጃቸው የታሰሩ ሰዎችን መሬት ላይ አጋድመው በአጣና ጉማጅ አናት አናታቸውን ልክ እንደ እባብ ይቀጠቅጧቸዋል፡፡ ግማሾቹ በደም ተነክረው ተዘርረው ያቃስታሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሰቅጣጭ ጩኸት ያሰማሉ፡፡ ሌሎቹ ስቃይ የበዛባቸው ትንፋሻቸው እንኪቆራረጥ በከፍተኛ ድምጽ የድረሱልኝ ጮኸታቸውን ይለቁታል›› (178፣ 179)፡፡ ሻምበሉ አጣርቼ አገኘሁት እንደሚለው በአሰቃቂ ሁኔታ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸውም በጎንደር ከተማና አካባቢው ህወሓትና ሻቢያ ‹‹ነፍጠኛ›› ብለው የፈረጇቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ሰዎችን እንዲህ በአጠና በአሰቃቂ ሁኔታ የሚደበድቡት የህወሓት አባላት ብቻ አለመሆናቸው ነው፡፡ ኢህዴን አንድ ግዜ ‹‹የመገንጠል መብታቸውን እናውቃለን፣ ሌላ ጊዜ እናውቀላን፣ እናደንቃለን›› ይልላቸው የነበሩት የሻዕቢያ ካድሬዎች ጭምር እንጅ፡፡
የብአዴን ካድሬ የነበረው ሻምበል አስረስ ህወሓት በፈለገው ጊዜ ብአዴን አስተዳድረዋለሁ ከሚለው አካባቢ የሚወስዳቸውን አካባቢዎች እንደፈለገ መከለል የጀመረው ከ23 አመት በፊት መሆኑንም ያስረዳል፡፡ ሻምበሉ ሱዳን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኢህአዴግ ስለሚመሰርተው ‹‹የድሮው አስተዳደር በወንዝና በተራራን መሰረት አድርጎ የተከለለና ፍትሃዊ ያልበረ በመሆኑ አዲሱ የህዝብ ለህዝብ አንድነትን ለማምጣት የሚያስችል እንደሆነ እንዲቀሰቅሱ መመሪያ ይሰጣቸውና ቅስቀሳ ይጀምራሉ፡፡ ይሁንና የካድሬ (ክፍለ ህዝብ) መሪ የነበረው የህወሓት ካድሬ አንድ ቦታ ላይ ‹‹(ህወሓት) በፊውዳሉ በተለይም በአጼ ኃ/ስላሴ ዘመን መንግስት የትግራይ ህዝብ የተቀማውን መሬት ማለትም አላማጣን፣ ኮረምን፣ ሁመራንና ወልቃይትንና የመሳሰሉ መሬቶችን አስመልሷል፡፡ ወደፊትም እየተጠና የምናስመልሰው ይኖረናል›› በሚል ህዝብን ለመያዝ በመመሪያ የተሰጣቸውን ሳይሆን የህወሓትን ዋነኛ አላማን ለህዝብ ያቀርባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ህዝብ ግራ ለመጋባትም አልፎ ቁጣ ይቀሰቀሳል፡፡ በካድሬዎቹ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮም እርስ በእርሳቸው ተደባድበዋል፡፡ ሆኖም ከ‹‹መርህ›› ውጭ የቀሰቀሰው የህወሓት ካድሬ እርምጃ ይወሰድበታል ሲባል የብአዴኑ ሻምበል አስረስ ስራ እንዲያቆም ተደርጓል፡፡ ያ የህወሓት ካድሬ ‹‹ወደፊትም እየተጠና የምናስመልሰው ይኖረናል›› ያለው አሁንም እውን እየሆነ ይመስላል፡፡ በቅርቡ ከጎንደር አካባቢ የተከለሉ ሁለት ወረዳዎች እንዳሉ መገለጹ ይታወቃል፡፡ (ብአዴን አስተዳድረዋለሁ የሚለው መሬት ለሱዳንም ይሁን ለህወሓት ካድሬዎች እንዲከፋፈል በደስታ ፈርመው እያስረከቡ ነው የሚባሉት ም/ጠ ሚኒስተር ደመቀ መኮነንንና፣ የክልሉ ምክትል አስተዳደር ገዱ አንዳርጋቸውን የመሳሰሉት በርካታ የብአዴን አመራሮች ‹‹እናስተዳድረዋለን›› በሚሉት ህዝብ ዘንድ የተጠሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡) እንግዲህ ፌደራል ስርዓቱ ከተመሰረተ ከ23 አመት በኋላ እንደገና ክለላ፣ እንደገና የመሬት ወረራ ‹‹ብአዴን›› የህወሓት አካልና አገልጋይ እንጅ አንድ ራሱን የቻለ ፓርቲ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ብአዴን ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ህወሓት ያለውን ተቀብሎ ቀጥሏል፡፡ በ1993ቱ ክፍፍል ደግሞ ከህወሓት የወጡትን ለመተካት በሚመስል መልኩ ለአቶ መለስና ህወሓት ተገን ሆኖ አገልግሏል፡፡ አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ የተሰጠውን አስፈጻሚነት ሲቀማም ቢሆን ህወሓትን በማክበር ልምዱ ያለ ማንገራገር ተቀብሎታል፡፡
በ1997 ምርጫ ደግሞ የብአዴን አባላት ‹‹እንወክለዋለን በሉ!›› የተባሉትን ህዝብ በህወሓት ቋንቋ በጅምላ በነፍጠኝነት የከሰሱበት ወቅት ነበር፡፡ ኢህዴን/ብአዴን ‹‹ትግሉ የአማራ ገዥ መደቦች በጭቁን ብሄሮችና በአማራው ህዝብ መካከል ፈጥረውት የነበረውን የእርስ በእስር መጠራጠርና አለመተማመን አስወግዷል›› (ፅናት፣ 139)፡፡ ቢልም ቀድሞውንም ቢሆን በገዥ መደብ መካከል እንጅ በህዝብ መካከል ይህ ነው የሚባል አለመተማመን ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የድሮው ኢህአዴን ወክየዋለሁ የሚለው አማርኛ ተናጋሪ ከህዝብ ሳይሆን ከበርካታ ክልሎች በገዥዎች የማፈናቀል ሰለባ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ ከህወሓት ጋር በመሆን ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማስማማት ተነሳሁ የሚለው ብአዴን ጭራሹን በህዝብ መካከል መቃቃርን ፈጥሯል፡፡ ብአዴን አስተዳድረዋለሁ ከሚለው አካባቢ በህወሓት የሚወሰዱ ንብረቶች፣ የሚከለሉ መሬቶችና መቀስቀሻዎቹ ሆን ተብሎ በህዝብ መካከል ያለውን ድልድይ በመስበርና አለመተማመን እንዳይኖር ማድረግ ህወሓት ለብአዴን በአስፈጻሚነት የሰጠው ዋነኛው ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› መርህ ይመስላል፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት ህዝብ በርሃብ እያለቀ ‹‹የአማራ ወኪል›› ነኝ የሚለው ብአዴን እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ‹‹የትምክት ልሃጩን ያላራገፈ …..›› እያሉ በሚሰድቡት እነ አለምነው መኮነን አሳላፊነት 35ኛ አመቱን በፌሽታ ሲያከብር ከርሞ፣ በርካታ ገንዘብ የፈሰሰበት ሀውልት ማስመረቁን ስናይም ከህዝብ ይልቅ ለራሱና አላማውን እንዲያስፈፅምለት ላቆመው ወኪል መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ ለህወሓት!

Friday, November 20, 2015

ፖለቲካ በደም አይጋባም

def-thumbህዝባዊ ተቀባይነቱን ያጣው ወያኔ በሽፍትነት ዘመኑ ትግራይ ውስጥ ሲያደርግ እንደረነበረው ሁሉ፣ መንግስታዊ ስልጣኑን ከያዘም በሁዋላ መሰልጠን አቅቶትና እንደመንግስት ማሰብ ተስኖት፣ አገዛዜን ይቃወማሉ ብሎ የሚጠረጥራቸውን ዜጎች የቅርብ ቤተሰቦችና የሩቅ ዘመዶች ሳይቀር ማሰቃየት መጀመሩን ከአራቱም የአገራችን ማዕዘናት በየቀኑ የሚደርሱን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
በቅርቡ በአርባ ምንጭ ከተማ ለአገራቸው ነጻነት በገዛ ፈቃዳቸው ተነሳስተው ታሪካዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በሞከሩ ወጣቶች ላይ የስርዓቱ ታማኝ ጥቂት የደህንነት ሃይሎች የወሰዱት እርምጃ ዘግናኝና ልብ የሚያቆስል ነው። ይህም አልበቃ ብሎ የተፈላጊ ወጣቶች መኖሪያ ቤቶች በታጠቁ የደህንነት ሃይሎች ተወረው ፍተሻ ተካሂዶባቸዋል:: እናቶች ህጻናት ልጆቻቸው ፊት “የተደበቁ ልጆቻችሁን አምጡ ” ተብለው መሳሪያ ተደቅኖባቸው፣ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል። በአገዛዙ ዘረኛና የተጨማለቀ ፖሊሲ ተማረው ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ እርምጃ መውሰድ የጀመሩ የቴፒ ወጣቶችን ለማደን የተደረገው ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ የፈደራል ፖሊስና መከላኪያ ሠራዊት በወላጆች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። ወጣት ሴቶች እና እናቶች ርህራሄ በጎደላቸው የስርዓቱ ታማኝ ወታደሮች ተደብድበዋል፣ ተደፍረዋል፣ ታስረዋል። በሰሜን ጎንደርም እንዲሁ መብታችን ይከበር ብለው በተነሱ ወጣት ቤተሰቦች ላይ የገዢው ሃይል ታማኞች ፣ ግድያና አስገድዶ መድፈር ፈጽመዋል። እህትማማች ሴቶች መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ተገድለዋል። በወታደሮች የተደፈሩ ሴቶች ቅስማቸው ተሰብሮ ወደ አደባባይ ለመውጣት እንኳ የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። በመርአዊ ከተማ መኳንንት ጸጋዬ የተባሉ በሰላማዊ ትግል ስርዓቱን የሚቃወሙ ግለሰብ፣ በልጆቻቸውና በባለቤታቸው ፊት አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ተደብድበዋል፤ የልጆችን ስነልቦና በሚነካ መልኩም ሰዋዊ ክብራቸው እንዲዋረድ ተደርጓል።
በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ ድንበር የለውም፤ የወያኔን የበቀል ዱላ ያልቀመሰ፣ ማንነቱና ክብሩ ያልተዋረደ ህዝብ ማግኘት አይቻልም። በገዳዩ ስርዓት እየደረሰ ያለው ግፍ አንድ ጊዜ በሰሜን፣ ሌላ ጊዜ በደቡብ፣ ሌላ ጊዜ በምስራቅ እያለ ቀጥሎአል። የዚህ ፍጹማዊ የአፈና አገዛዝ ህልውና እንዲቀጥል እስከተፈቀደለት ድረስ ጭቆናው፣ መዋረዱ፣ መታሰሩና መሞቱ አይቆምም። የአገዛዙ ባህሪ እነዚህን ሰይጣናዊ ድርጊቶች ለመፈጸም እንጅ መልካም ነገር ለመፈጸም አያስችለውም።
ለነጻነት የሚደረገው ትግል በመሬት ላይ አድማሱን እያሰፋ በመጣ ቁጥር የጥቃቱ አይነትና መጠንም እየጨመረ እንደሚመጣ ስናስብ፣ ይህን ጥቃት የምናስቆምበት ወይም የምንቀንስበትን መንገድም መሻት ተገቢ ነው። ወያኔ በነጻነት ታጋይ ቤተሰቦች ላይ ጥቃቱን ሲፈጽም ከሚጠቅሳቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ “ልጅህ ወይም ወንድምህ መንግሥታችንን ለመናድ ሌት ተቀን እየሰራ አንተ በሠላም ልትኖር አትችልም” የሚል ነው። ይህ ሁዋላ ቀር አስተሳሰብ ወያኔን ከሚመሩ ሰዎች የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ፖለቲካ ወይም የነጻነት ጉዳይ በደም የሚወረስ ሳይሆን ከግለሰቦች ማንነት ጋር ተያያዞ የሚመጣ መሆኑን፣ ቀድም ብለው በሁለት ጎራ ለይተው ሲፋለሙ የነበሩ ወጣቶችን ታሪክ ማስታወስ በቂ ነው። ከአንድ ማህጸን የወጡ የአንድ እናት ልጆች የተለያዬ የፖለቲካ አመለካከት እንደሚይዙ ታሪካችን ብቻ ሳይሆን፣ የወያኔ ታሪክ ራሱ ምስክር ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ በጅምላ በቤተሰብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት፣ ከሁዋላ ቀርነትና ከግንዛቤ ማነስ የመጣ ነው ተብሎ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን፣ ድርጊቱን ከሚፈጽሙት ሰዎች ስነልቦና ቀውስና የሁዋላ ታሪክ ጋር የሚያያዝ ነው። በንጹህ ዜጎች ላይ ጭካኔና ግፍ የሚፈጽሙ ሰዎች፣ የሰው ማንነት የሌላቸው፣ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ የተበላሹና ማህበረሰቡ “አይመጥኑም” ብሎ የተፋቸው ናቸው። አሁን በስልጣን ላይ ያሉና በህዝባችን ላይ የጭካኔ ዱላቸውን የሚያሳርፉ ገዢዎች የሁዋላ ታሪክ ቢጠና ከዚህ የተለየ እውነታ አይኖረውም።
ሌላው የወያኔ ስልት ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭ የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ታጋዮችን ቤተሰቦችና ዘመዶች እየተከታተሉ ” እባካችሁ ዘመዶቻችሁ ከፖለቲካው እንዲርቁ አድርጉ፣ እንዲህ ካደረጋችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናድርግላችሁዋለን፣ ለእነሱም የፈለጉትን ነገር እናደርግላችሁዋለን” በማለት ለመደለል መሞከራቸው ነው።
ለወያኔ ነጻነት ማለት ገንዘብ ነው፤ ቤት ነው፤ ሆድ ነው፤ ነጻነት የህሊናና የማንነት ጉዳይ መሆኑን ገና አላወቀም። ሁሉም ሰዎች ነጻነታቸውን በገንዘብ፣ በቤት፣ በሆድ ወይም በብልጭልጭ ምድራዊ ነገር ይሸጣሉ ብሎ ያስባል፤ በርግጥ በእነዚህ አላፊና ጠፊ ነገሮች ተታለው ነጻነታቸውን የሸጡ ቢኖሩም፣ ሁሉም ሰው ግን እንደዛ አይደለም። የወያኔን የግፍ አገዛዝ ተቃውመው ለነጻነት የሚታገሉ ሃይሎች ሁሉ፣ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ትተው፣ ህሊናዊና ማንነታዊ ፍላጎትን ለራሳቸውም ለህዝባቸውም ለማምጣት የሚታገሉ ናቸው። በወያኔና በእነዚህ ታጋዮች መካከል ያለው ልዩነትም ይህ ነው፤ ወያኔ ለአላፊ ጠፊው ምድራዊ ህይወት ሲጨነቅ፣ እነዚህ ተጋዮች፣ ዘላለማዊ ለሆነው ለነጻነትና ለማንነት ክብር ይጨነቃሉ። ስለዚህ ወያኔ ለህሊናቸውና ለማንነታቸው የሚታገሉ ሃይሎችን በቁሳዊ ፍላጎት ለመደለል የሚያደርገው ጥረት መቼውንም ፍሬ አያፈራምና ቤተሰቦችን እየጠራ ባያንገላታቸው ይመረጣል።
የአገዛዝ ዕድሜን ለማራዘም ሲባል በነጻነት ታጋይ ቤተሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለው ጥቃት ከዚህ ቀደም በነበሩ ሁለት መንግሥታት ዘመን እንኳ ታይቶ የማይታወቅ ለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም:: መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት በተለየበት ሰሞን የአገዛዙ ጋዜጠኞች አደዋ የሚገኘውን የወላጆቹን መኖርያ ቤት በቴለቪዥን ለህዝብ ዕይታ አቅርበው ፣ መለስ ዜናዊ ከጫካ እየሾለከ መጥቶ ያርፍ እንደነበር በገዛ ወንድሙ አፍ እንዲነገር አድርገዋል::
በአጭሩ ፓለቲካ በደም አይተላለፍም፤ ደምን ቆጥሮ በፖለቲካ ታጋይ ቤተሰቦች ላይ የሚደርስ ጥቃትም፣ ቂምና በቀልን ከመውለድ ውጭ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ህዝባዊ የነጻነትን ትግልን፣ የታጋዮችን ቤተሰቦች በማሰቃየት ወይም በመደለል ማስቆም አይቻልም። አፈናና ሰቆቃ ባለበት ቦታ ሁሉ፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ አመጽ የማይቀር ማህበራዊ ክስተት ነው :: በተለይ “የህዝብ ብሶት ወለደኝ” በማለት መሣሪያ አንስቶ 17 አመት ታገልኩ ለሚለው ወያኔ ይህ ግልጽ እውነታ ምርምር የሚጠይቅ ውስብስብ ፍልስፋና ሊሆንበት ባልቻለ ነበር :: ዳሩ ከተጣመመ አፈጣጠሩ፣ ከመሪዎቹ ምንነትና ማንነት እንዲሁም ስልጣን ከተያዘም በሁዋላ በዘረፋ የተሰበሰበው ሃብት የፈጠረው የኑሮ ምቾትና የተከማቸው የጦር መሳሪያ ያቀዳጀው እብሪት አይነ ልቦናውን ጋርዶታልና ለወያኔ ይህ ሃቅ ሊገባው አይችልም።
አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ የአፈና ክንዶች ሺ ጊዜ ቢፈረጥሙም ፤ በተቃዋሚዎችና የነጻነት ታጋዮች ቤተሰብ ላይ የሚወሰደው እርምጃ የህይወት መስዋትነት እያስከፈለ ቢመጣም እንኳ ለነጻነት የሚያደረገው ትግል ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ ለአፍታም ቢሆን አይዘናጋም። የታጋይ ቤተሰቦችና ዘመዶችም፣ አሁን በወያኔ የሚደርስባችሁ ግፍና በደል፣ ለመላው አገራችን ነጻነት ሲባል የሚከፈል ዋጋ በመሆኑ ልትኮሩ እንጅ ልለትሸማቀቁ አይገባም ። በህዝብ ፊት የነጠሉዋችሁና ከማህበራዊ ህይወታችሁ እንድትገለሉ ያደረጉዋችሁ ቢመስላችሁ፣ እውነታው ተቃራኒው ነው፤ ከህዝብ የተገለሉት እነሱ ናቸው፤ የሚዋረዱትና የሚያፍሩት እነሱ ናቸው።
በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ሥር የሚማቅቅ እያንዳንዱ ዜጋ አርበኞች ግንቦት 7 የለኮሰውን የነጻነት ትግል ችቦ አንግቦ በወያኔ ከርሰ መቃብር ላይ የታፈረች የተከበረችና የዜጎቿን መብት በእኩልነት የምታስከብር አገር ለመገንባት በሚደረገው ትግል እንዲቀላቀል አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪውን ያቀርባል:: የወያኔ የጥቃት እጆች የሚያጥሩትና ዜጎች በአገራቸው ተከብረው የሚኖሩት ወያኔ ሲወገድ ብቻ ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
Source: patriotg7.org