Thursday, January 22, 2015

“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም”

journalism


የሰብዓዊ መብት ጠባቂ የሆነው ድርጅት (ሂዩማን ራይትስ ዎች) “ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” በሚል ርዕስ ያወጣል ተብሎ የተጠበቀውን ዘገባ ማምሻው ላይ ይፋ አድርጓል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ያለ ነጻ ሚዲያ – ምርጫ ወይስ ቁማር?” በሚል ርዕስ ባተመው ዜና ላይ ዘገባው እንደሚወጣ በተናገረው መሠረት ባለ 76 ገጽ ሪፖርቱ በሚዲያ አፈና ዙሪያ ዝርዝርና ወቅታዊ መረጃዎችን አውጥቷል፡፡
ኢህአዴግ በሚያደርስባቸው ስልታዊ አፈና፣ ማስፈራሪያ፣ ህይወት የማጥፋት ዛቻ፣ … ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በትንሹ 22 የሚሆኑ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ፤ ከ30 በላይ የሚሆኑ ደግሞ አገር ጥለው መኮብለላቸውን በዘገባው ተጠቁሟል፡፡ እንዲህ ያለው ገለልተኛ ሚዲያን የሚያፍን እና ከሜዳው የሚያስወጣ አሠራር ከወራት በኋላ ይካሄዳል ከሚባለው “ምርጫ” አኳያ የውድድሩን ሜዳ ከማጥበብ አልፎ እንዳይኖር እንደሚያደርገው የዘገባው ሃተታ ያስረዳል፡፡
ድርጅቱ ካወጣው ዘገባ ጋር በተሰራጨው የዜና መግለጫ ላይ የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሌስሊ ለፍኮው ሲናገሩ “በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ምርጫ የኢትዮጵያ ሚዲያ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችል ነበር፤ ሆኖም ግን ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ሊያወጡ የሚፈልጉት ጦማር ወደ እስርቤት እንደሚያስወረውራቸው ስለሚፈሩ” ሙያዊ ተግባራቸው ከመወጣት እንደሚቆጠቡ ተናግረዋል፡፡
ዘገባው ከ70 የሚበልጡ አገር ውስጥና በስደት ከሚገኙ ጋዜጠኞች ጋር ቀጥተኛ ቃለምልልስ በማድረግ የወጣ የአንድ ወገን ሰነድ ሳይሆን ለኢህአዴግ ባለሥልጣናትም ጥያቄዎችን በማቅረብ የሰጡትን ምላሽ ለማመጣጠኛ አቅርቧል፡፡ በመጨረሻም ይበጃሉ ያላቸውን የምክር ሃሳቦች ጠቁሟል፡፡ የመጀመሪያ ጥቆማ ለኢህአዴግ ሲሆን በመቀጠልም የኢህአዴግን ቋት የሚሞሉትን ለጋሽ አገራት በተለይ አሜሪካንና የአውሮጳ አገራትን ተጽዕኖ ማድረግ በሚገባቸው ቦታዎች ላይ ዝምታን ከመምረጥ ይልቅ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉበት ቦታ የት እንደሆነ አውቀው ስለ ሰብዓዊ መብት መከበር ሲሉ ተግባራቸውን እንዲወጡ የምክር ሃሳቡን ለግሷል፡፡ አፈናውን፣ ዛቻውንና እንግልቱን አምልጠው በጎረቤት አገራት ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ የስደት ኑሯቸውን በሚገፉት ጋዜጠኞች ላይ ተጠቃሾቹ አገራት የኢህአዴግ ጓሮ በመሆን የስደተኞቹን መከራ ከማብዛት ይልቅ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ በማድረግ እንዲሁም የጥገኝነት ማመልከቻቸውን በአፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ተገቢውን የሰብዓዊ መብት እንክብካቤ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡
ሙሉ የእንግሊዝኛው ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡
ከዘገባው ጋር በተያያዘ የወጣው አጭር ቪዲዮ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡  ድርጅቱ ያወጣው የማጠቃለያ መግለጫ ክዚህ በታች ሰፍሮዋል፡፡

“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም”

በኢትዮጵያ የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነት ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰት

እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2015 ዓ.ም.

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እ.ኤ.አ. በ2010 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ 99.6 በመቶ የፓርላማ መቀመጫን ካሸነፈ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን እና መረጃ የማግኘት መብትን በመገደብ በግል መገናኛ-ብዙሃን ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አባብሶታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቢያንስ 60 ጋዜጠኞች ሃገር ለቀው የተሰደዱ ሲሆን ሌሎች 19 ጋዜጠኞች ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ መንግስት በደርዘኖች የሚቆጠሩ ህትመቶችን ዘግቷል፤ እንዲሁም አብዛኛዎቹን የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ስርጭቶች በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ኢትዮጵየዊያን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮችን በተመለከተ ነጻ መረጃ እና ትንታኔ የሚያገኙበትን እድል አጣቧል። በግንቦት 2007 በሚካሄደው ምርጫ መገናኛ-ብዙሃኑ ህዝቡን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በማስተማርም ሆነ መረጃ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችሉ ነበር፤ እንዲሁም የመከራከሪያ መድረክ በመሆን ሊያገለግሉ ይችሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ መንግስት በሃገሪቱ ላለው ብቸኛ የበላይነት የግሉን መገናኛ-ብዙሃን እንደ ስጋት አድርጎ በመውሰድ የግሉን መገናኛ-ብዙሃን፣ ነጻ ጋዜተኝነትን እና ተቺ ትንታኔን ለማጥፋት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም የከፋ ውጤት አስከትሏል።
የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆነው የኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (Committee to protect Journalists) መረጃ እና የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከኢራን በመቀጠል በዓለም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችን ለስደት የምትዳርግ ሀገር ሆናለች። የመንግስት አካላት አፋኝ ህጎችን መሰረት አድርገው ጋዜጠኞች በየወቅቱ ያሉ ክስተቶችን እና ጉዳዮችን አስመልከተው በሚሰሩት ዘገባ እና ትንታኔ ምክንያት በተደጋጋሚ ክስ ይመሰርቱባቸዋል፤ ፍርድ ቤቶችም ክሱን ተከትለው የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እስክንድር ነጋን እና ርዕዮት ዓለሙን የመሰሉ ግለሰቦች በአዲስ አበባ እና በክልሎች የሚገኙ ተለይተው የሚታወቁም ሆነ የማይታወቁ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች እየደረሰባቸው የሚገኘውን ፈተና የሚያሳዩ ምልክቶች ሆነዋል። ጋዜጠኞቹ በርካታ ስጋት ውስጥ የሚገኙ፣ ማስፈራሪያ የሚደርሳቸው፣ አልፎ አልፎም አካላዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው እና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው የወንጀል ወይንም የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው፡፡ የፍርድ ቤት ክርክራቸው ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን የሚጥሱ አሰራሮች የሚታዩበት ሲሆን ፍርድ ቤቶቹም በያዟቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ገለልተኛ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የህትመት መገናኛ-ብዙሃን ከመግስት ጋር የቀረበ ትስስር አላቸው፤ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከመንግሰት የተለየ አቋም እምብዛም አያንጸባርቁም።የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን በርካታ ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥማቸዋል እንዲሁም በደህንነት ሰራተኞች ተከታታይ ወከባ ይደርስባቸዋል፡፡ መንግስትን የሚተቹ የህትመት ውጤቶች በየጊዜው ይዘጋሉ፣ የበሰለ ትችት የሚያቀርቡ የህትመት ውጤቶችን የሚያትሙ እና የሚያከፋፍሉ አሳታሚዎች እና አከፋፋዮችም ተዘግተዋል፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞች እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ጭምር የጥቃት፣ የመታሰር እና የገቢ ምንጫቸውን የማጣት ዘላቂ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ መንግስት አብዛኛውን የመገናኛ-ብዙሃን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን የቀሩት ጥቂት የግል መገናኛ-ብዙሃንም በተለይ ለአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚሰጡት ሽፋን ራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ያደርጋሉ ይህም እንዘጋለን ከሚል ፍርሃት የመነጨ ነው፡፡
ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ ጋዜጠኝነትን እና ትንታኔን ለመቆጣጠር እንዲሁም መረጃ የማግኛ መንገድን ለመገደብ የተጠቀማቸውን ዘዴዎች የሚዘግብ ነው፡፡ ሪፖርቱ ከ70 የሚበልጡ የአሁን እና የቀድሞ ጋዜጠኞችን እና የመገናኛ-ብዙሃን ባለሙያዎችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሚገኝበትን አስከፊ ሁኔታ እና በዚህም ምክንያት ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት እና መገናኛ-ብዙሃን ላይ የደረሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ይዘረዝራል፡፡
በስፋት በተዘገቡ ጉዳዮች ላይ ከዓለምዓቀፍ ማህበረሰብ የተሰነዘሩ ውግዘቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መንግስት ለገለልተኛ የመገናኛ-ብዙሃን ድምጽ ምንም አይነት የመለሳለስ ምልክት አላሳየም፤ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም የግል መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ በእጅጉ ተባብሷል፡፡ አስር ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኞችን ዝርዝር ተቀላቅለዋል እንዲሁም አምስት መጽሄቶች እና አንድ ጋዜጣ በመንግስት የዛቻ እና የማስፈራሪያ ዘመቻ ከተካሄደባቸው በኋላ እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡ ዘመቻው በመንግስት በሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያ የህትመት ውጤቶቹ ሽብርን እንደሚደግፉ አስመስሎ ማቅረብ፣ የህትመት ውጤቶቹን የሚያትሙ ማተሚያ ቤቶችን ማዋከብ፣ በህትመት ውጤቶቹ የማከፋፈል ስራ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት በርካታ ዛቻዎችን መሰንዘርን ያካትታል፡፡ ይህም በመጨረሻ በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እና በርካታ የህትመት ውጤቶች ባለቤቶች ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ እና ባለቤቶቹ የወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው በማድረግ ተከናወኗል። ፍርድ ቤቶች ሌላ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሳይቀርብ መንግስትን የሚተቹ ጽሁፎችን ብቻ መሰረት በማድረግ በሶስት የህትመት ባለቤቶች ላይ በሌሉበት እያንዳንዳቸው ከሶስት አመት የሚበልጥ እስር እንዲቀጡ ወስነውባቸዋል፡፡ የሌሎች የህትመት ባለቤቶች ክስም በሂደት ላይ ነው፡፡
መንግስት ከሚፈፅማቸው ትኩረትን የሚስቡ እስሮች በተጨማሪ መገናኛ-ብዙሃንን ለማዳከም እና ለመዝጋት ሌሎች በርካታ በግልጽ የማይታዩ የእጅ አዙር መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ የደህንነት ሰራተኞች በአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ጋዜጠኞች ላይ ተከታታይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ያደርሱባቸዋል፡፡ እነዚህ ዛቻዎች ብዙውን ጊዜ ከጋዜጠኞቹም አልፎ ወደ ቤተሰባቸው እና ጓደኞቻቸው ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያ ተቀብለው በሚሰሩት ዘገባ ላይ ቅድመ-ምርመራ የማያካሂዱት በአብዛኛው ክስም ሳይመሰረትባቸው በዘፈቀደ ይታሰራሉ እንዲሁም ተጨማሪ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ አካባቢዎች በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ያልተገባ አያያዝ እና ድብደባ የተለመደ ሆኗል፤ በአብዛኛው ጊዜም የወነጀል ክስ ተከትሎ ይመጣል። ብዙዎቹ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ የግል ጋዜጠኞች በርካታ ጊዜያት እስር ተፈጽሞባቸዋል፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት፣ ከገዢው ፓርቲ ካድሬዎች፣ እና ከቀድሞው የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ የመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳዮች ቢሮ ከተባለው መስሪያቤት ባለስልጣናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛቻዎችን ተቀብለዋል፡፡
ይህም በመጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በራሳቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ በማድረግ የገዥውን ፓርቲ አጀንዳ ከማራገብ ወይንም ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ዘገባ እና እና ትንታኔ ማቅረብ ከመቀጠል አንዱን የመምረጥ ከባድ ፈተና ውስጥ እንዲወድቁ ያደርጋል።
በግለሰብ ጋዜጠኞች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት በተጨማሪ የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤቶች የህትመት ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙባቸውን ማተሚያ ቤቶች ለማዳከም ባለስልጣናቱ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ፡፡ በመግስት ስር የሚተዳደረው እና በመደበኛነት ጋዜጦችን የማተም አቅም ያለው ብቸኛ ማተሚያ ቤት የግል ህትመት ውጤቶችን ስራ ያዘገያል ወይንም አይቀበልም፣ በአንድ አጋጣሚ መንግስት በጣም አሳሳቢ ነው ባለው ጉዳይ ላይ ዘገባ ያሳተመን ጋዜጣ 40,000 ኮፒ ህትመት አቃጥሏል፡፡ የደህንነት ሰዎች የግል ህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይም የሚያደርጉትን ክትትል እና የሚያደርሱትን ጥቃት ጨምረዋል፡፡ የጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮች በተደጋጋሚ ለጥቃት እየተጋለጡ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ለመነጋገር ፍርሃት የሚያድርባቸው ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
መንግስት የግል ጋዜጠኞች ማህበር ለማደራጀት የሚደረግን ሙከራ ያግዳል እንዲሁም የግል የህትመት ውጤቶች ያላቸውን ፖለቲካዊ ትስስር በተመለከተ የደህንነት ባለስልጣናት ሰፊ የኋላ ታሪክ ጥናት ያካሂዳሉ፡፡ የመንግስት ወይም የገዥው ፓርቲ ሙሉ ደጋፊ ያልሆኑ የግል ህትመቶች ለሚያቀርቡት የህትመት ፈቃድ አሊያም እድሳት ጥያቄ ባለስልጣናት ምላሽ ለመስጠት ይዘገያሉ፡፡
የድረ-ገጽ መገናኛ ብዙሃንም በተሻለ መልኩ የተያዙ አይደሉም፡፡ በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚመሩ በርካታ ጦማሮች እና ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁት በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚያቀርቡ የጦማሪያን ስብስብ 80 ቀናት ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ከቆዩ በኋላ በጸረ-ሽብር አዋጁ እና የወንጀል ህጉ መሰረት ተከሰዋል፡፡ በቀረበው ክስ መሰረት በክስ ዝርዝር ሰነዱ ከተጠቀሰባቸው ማስረጃ መካከል አንዱ ቴክኒካል ቴክኖሎጂ ኮሌክቲቭ በተባለው በኢንተርኔት ላይ የሚገኝ የግላዊ መረጃዎችን ሚስጥራዊነት ለመጠበቅ የሚረዱ ተግባራትን እና መሳሪያዎችን በሚያቀርበው ዓለም ዓቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የዲጂታል ደህንነት ጥበቃ ስልጠና ወስደዋል የሚል ነው፡ ፡ የዞን ዘጠኝ አባላት መታሰር እና መከሰስ በሃገሪቱ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የፍርሃት ድባብ ፈጥሮአል።
ይህም ጦማሪዎች እና የኢንተርኔት ላይ ተሟጋቾች በፌስቡክና በመሳሰሉ እና ሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች በሚለጥፏቸው ትችቶች ምክንያት ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን የሚለውን ስጋታቸውን በእጅጉ ከፍ አድርጎታል፡፡
በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመንግስት ስር የሚገኙ ሲሆን ገለልተኛ የዜና ዘገባ እና ትንታኔ አይቀርብባቸውም፡፡ ከ80 በመቶ የሚበልጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠራማ አካባቢዎች በመሆኑ እና ሬድዮ እስከአሁን ዋናው የዜና እና መረጃ ማግኛ ምንጭ ከመሆኑ አንጻር ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚያቀርቡ ጥቂት የግል ሬድዮ ጣቢያዎች ዝግጅቶቻቸውን አየር ላይ ከማስተላለፋቸው ከቀናት በፊት የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገመግሙት እና እንደሚያጸድቁት ለሂውማን ራይትስ ወች ተናግረዋል፡፡ ተቀባይነት ካገኘው ይዘት የሚያፈነግጡ አሰራጮች በመንግስት ባለስልጣናተ የሚፈጸም እስር እና ወከባ ጋር መጋፈጥ ሊኖርባቸው ይችላል።
በርካታ ጋዜጠኞች ከማያቋርጥ የማዋከብ እና የፍርሃት ሕይወት ለመገላገል ሲሉ ከመንግስት ጋር ትስስር ባለው መገናኛ-ብዙሃን ተቀጥረው መስራት ይመርጣሉ፡፡ አንዳንዶች የመንግስት ባለስልጣናትን እስከማያስቆጣ ድረስ ባለው መለያ መስመር ላይ ሆነው ትችቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የመንግስትን የልማት ውጤቶች በማስተዋወቅ እና በማጋነን የመንግስት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢዎች ሆነው ይሰራሉ፡፡ በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የኢህአዴግ አባልነት እድገት ለማግኘት የሚጠየቅ መስፈርት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙት የውጭ መገናኛ ብዙሃን ውሱን ናቸው። የአሜሪካ ድምጽ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ (ቪኦኤ) እና የጀርመን ድምጽ ዶቼቬሌ የቴሊቪዥን እና የሬድዮ ሽፋን በመስጠት በርካታ የዲያስፖራ ጣቢያዎችን ተቀላቅለዋል፡፡ ሆኖም የአየር ሞገዳቸውን በማገድ፣ በሰራተኞቻቸው እና የመረጃ ምንጮቻቸው ላይ ዛቻ እና ጥቃት በማድረስ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ የዲያስፖራ መሰረት ያላቸውን ስርጭቶች የሚመለከቱ እና የሚያዳምጡ ግለሶቦችን በማጥቃት እና በማሰር ጭምር መንግስት የሃገር ውስጥ ተከታታዮቻቸውን ለመገደብ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማሕበራት ላይ በደረሰው ጫና ምክንያት በርካታ የሲቪል ማሕበራት ስራ ለማቆም የተገደዱ ሲሆን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ጥብቅ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ንቁ እና ነጻ የመገናኛ-ብዙሃን ዘርፍ በመንግስት አስተዳደር ላይ ተሳትፎን ለማበርከት እና የሰብዓዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማገዝ ያለውን አስፈላጊነት የበለጠ ያጎላዋል። አለመታደል ሆኖ በፖለቲካ ሁነቶች ላይ ገለልተኛ ሽፋን እና የዜና ትንታኔ ለመስጠት ያለውም ጥቂት ክፍተት እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. የበለጠ ተጣቧል፡፡ ከግንቦት 2007 ምርጫ መቃረብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ የፖለቲዊ አተያዮች እና ትንታኔዎችን የሚያገኙበት እድል እየተመናመነ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ መገናኛ-ብዙሃን ሁኔታን ለማሻሻል በአጭር እና በረጅም ጊዜ አሁንም ብዙ ሊደረግ ይችላል፡፡ እንደ መጀመሪያ እርምጃ መንግስት ክሶችን በአስቸኳይ በማንሳት የታሰሩ እና የተፈረደባቸው ጋዜጠኞች እና ጦማሪያንን ክስር ሊለቅ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች ንቁ እና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን መኖር ለሃገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ እንዲሁም በመጪዎቹ ሳምንታት እና ወራት መንግስት የጸረ-ሽብር ህጉን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙሃኑ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አፋኝ ህጎችን ማረም አለበት፡፡ የሚወጡ ህጎች እና የሚፈጸሙ ተግባራት የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እና ዓለምዓቀፍ መለኪያዎች ጋር በሚጣጠም መልኩ መሆኑን ባለስልጣናት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡

ምክረ ሃሳቦች

ለኢትዮጵያ መንግስት

  • ሁሉንም ክሶች በአስቸኳይ ማንሳት እንዲሁም በወንጀል መቅጫ ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት ተከሰው በዘፈቀደ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ መፍታት።
  • የጸረ-ሽብር አዋጁ እና የመገናኛ-ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጁ መሰረዝ አሊያም በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እንዲሁም በክልላዊ እና ዓለምዓቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ህጎች ላይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት ከተቀመጡ መስፈርቶች ጋር በሚጣጣም መልኩ ከፍተኛ መሻሻያ ማደረግ፡፡
  • የስም ማጥፋትን የወንጀል ቅጣት እንዲያስከትል ተደርጎ በወንጀል መቅጫ ህጉ አንቀጽ 613 ላይ የተደነገገውን ማሻሻል።
  • በህትመት እና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ላይ መንግስት ያለውን የባለቤትነት ድርሻ መገደብ ፤ እንዲሁም የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤትነትን የሚገድቡ ጉዳዮችን ለማስቀረት እና ገለልተኛ እና ንቁ መገናኛ-ብዙሃንን ለማበረታታት የሚያስችሉ የህግ እና የፖሊሲ ማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ።
  • አዳዲስ የህትመት እና የሬድዮ ስርጭቶች ቁጥጥርና ፈቃድ አሰራር ቀልጣፋ ማድረግ እና ከፖለቲካዊ ይዘት ነጻ ማድረግ። ቁጥጥር አድራጊ ባለስልጣን አካላት ገለልተኛ መሆን አለባቸው፤ እንዲሁም አስተዳደራዊ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ከመንግስት የደህንነት አካላት አና ከመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳች ቢሮ መለየት አለበት፡፡
  • የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለልተኛነትን ለማረጋገጥ ማሻሻያዎች ማድረግ።
  • የሃገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች በመላው ሃገሪቱ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን የሚገድቡ አሰራሮችን ማስወገድ፣ ይህም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ በሚባሉ አካባቢዎች በነጸነት መንቀሳቀስን እንዲጨምር፣ ፖሊስ እና የደህንነት ሰዎች መገናኛ-ብዙሃን በነጻነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ፈቃድ እንዲሰጡ መመሪያ መስጠት፤ በዛቻ፣ በማስፈራራት እና በማሰር የጋዜጠኞችን እንቅስቃሴ የገደበ ማንኛውም ፖሊስ በያዘው የማዕረግ እርከን ልዩነት ሳይደረግ መቅጣት።
  • የፖለቲካ ፓርቲ ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የጦማሪያን ድረ-ገጾችን ማፈን እና ቅድመ ምርመራ ማድረግን ማቆም እንዲሁም ለወደፊት እንደዚህ አይነት ድረ-ገፆችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
  • የሬድዮ እና የቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ማፈን ማቆም ፤ ለወደፊቱም የሬድዮ እና ቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
  • አስተያየት የመስጠት እና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት መብቶችን ለማዳበር እና ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት መንግስታት ልዩ ራፖርተር ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ እና የግል የህትመት እና የብሮድካስት መገናኛ-ብዙሃን ያሉበትን ሁኔታ እንዲገመግም እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ሁኔታ እንዲያጠና ግብዣ ማቅረብ።

የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ለዓለምዓቀፍ የኢትዮጵያ ለጋሾች

  • በዘፈቀደ የታሰሩ እና በወንጀል ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት የተከሰሱ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ እንዲፈቱ በይፋ ጥሪ ማቅረብ አና በተናጥል ጫና ማሳደር።
  • የጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ዓለምዓቀፍ የፍርድ ሂደት መስፈርቶችን ያሟላ መሆኑን ለማረጋገጥ የፍርድ ሂደት ክትትሉን ማሻሻል እና መጨመር።
  • የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሚገኙበትን ሁኔታ ለመገምገም እስር ቤቶችን እና ማቆያ ጣቢያዎችን ለመጎብኘት ጥያቄ ማቅረብ።
  • ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን የተመለከቱ አሳሳቢ ጉዳዮች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ልማትን እና ደህንነትን እንደሚጎዱ ያላቸውን ስጋት ለመንግስት ባለስልጣናት በይፋ እና በግል መግለፅ።
  • ገለልተኛ የጋዜጠኝነት ማህበር የሚፈጠርበትን መንገድ ጨምሮ የኢትዮጵያ መገናኛ-ብዙሃን የሙያ ብቃት እንዲዳብር ድጋፍ ማበርከት፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ለግል መገናኛ-ብዙሃን ጋዜጠኞች የተለዩ እድሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ እና የመገናኛ-ብዙሃን አቅምን ለማሳደግ ያለሙ እንቅስቃሴዎች እንዲካተቱ ልዩ ጥረት ማድረግ።
  • ነጻ ጋዜጦች እና ሌላ አይነት ህትመቶች መንግስታዊ ያልሆኑ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያልገቡ ማተሚያ መሳሪያዎችን የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ድጋፍ ማድረግ።

በመንግስት ለተያዙ እና ከመንግስት ጋር ትስስር ላላቸው ማተሚያ ቤቶች

  • ከመንግስት ጋር የተለየ ትስስር ያላቸው ህትመቶች ከሚታተሙበት የጊዜ ሰሌዳ በሚጣጠም መልኩ ሁሉንም ፈቃድ ያላቸው የግል መገናኛ ብዙሃን ህትመቶችን በተገቢው የጊዜ ገደብ እና አግባብ ባለው ሁኔታ በገለልተኝነት ማተም።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የውጭ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን አስተላላፊዎች

  • የተለየ አደጋ ያለባቸውን የመረጃ ምንጮች ለመለየት የሚጠቀሙበትን አሰራር ማጠናከር እና አደጋውን ለመቀነስ የሚወስዱትን እርምጃ ማዳበር፤ ይህም የግለሰቡ ማንነት እንዳይታወቅ ማድረግ፣ ማንነታቸውን በተመለከተ ያላቸውን መረጃ ሚስጥራዊ አድርጎ ማስቀመጥ እና ከፍተኛ ታዋቂነት ላላቸው ግለሰቦች ያለውን አደጋ እንዲገነዘቡት ማድረግን ይጨምራል፡፡

ለኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ መንግስታት

  • ጋዜጠኞች እና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ ጥገኝነት ጠያቂዎች ለጥገኝነት ማመልከቻቸው በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት እና ሊደርስባቸው ከሚችለው ጥቃት ከለላ እንደተሰጣቸው ማረጋገጥ።
  • Source:goolgule

Ethiopia decimates free press – Human Rights Watch

January 22, 2015
(Human Rights Watch, Nairobi) – The Ethiopian government’s systematic repression of independent media has created a bleak landscape for free expression ahead of the May 2015 general elections, Human Rights Watch said in a report released today. In the past year, six privately owned publications closed after government harassment; at least 22 journalists, bloggers, and publishers were criminally charged, and more than 30 journalists fled the country in fear of being arrested under repressive laws.The Ethiopian government’s systematic repression of independent media
The 76-page report, “‘Journalism is Not a Crime’: Violations of Media Freedom in Ethiopia,” details how the Ethiopian government has curtailed independent reporting since 2010. Human Rights Watch interviewed more than 70 current and exiled journalists between May 2013 and December 2014, and found patterns of government abuses against journalists that resulted in 19 being imprisoned for exercising their right to free expression, and that have forced at least 60 others into exile since 2010.
Ethiopia’s government has systematically assaulted the country’s independent voices, treating the media as a threat rather than a valued source of information and analysis,” saidLeslie Lefkow, deputy Africa director. “Ethiopia’s media should be playing a crucial role in the May elections, but instead many journalists fear that their next article could get them thrown in jail.”
Most of Ethiopia’s print, television, and radio outlets are state-controlled, and the few private print media often self-censor their coverage of politically sensitive issues for fear of being shut down.
The six independent print publications that closed in 2014 did so after a lengthy campaign of intimidation that included documentaries on state-run television that alleged the publications were linked to terrorist groups. The intimidation also included harassment and threats against staff, pressure on printers and distributors, regulatory delays, and eventually criminal charges against the editors. Dozens of staff members went into exile. Three of the owners were convicted under the criminal code and sentenced in absentia to more than three years in prison. The evidence the prosecution presented against them consisted of articles that criticized government policies.

While the plight of a few high-profile Ethiopian journalists has become widely known, dozens more in Addis Ababa and in rural regions have suffered systematic abuses at the hands of security officials.
The threats against journalists often take a similar course. Journalists who publish a critical article might receive threatening telephone calls, text messages, and visits from security officials and ruling party cadres. Some said they received hundreds of these threats. If this does not silence them or intimidate them into self-censorship, then the threats intensify and arrests often follow. The courts have shown little or no independence in criminal cases against journalists who have been convicted after unfair trials and sentenced to lengthy prison terms, often on terrorism-related charges.
“Muzzling independent voices through trumped-up criminal charges and harassment is making Ethiopia one of the world’s biggest jailers of journalists,” Lefkow said. “The government should immediately release those wrongly imprisoned and reform laws to protect media freedom.”
Most radio and television stations in Ethiopia are government-affiliated, rarely stray from the government position, and tend to promote government policies and tout development successes. Control of radio is crucial politically given that more than 80 percent of Ethiopia’s population lives in rural areas, where the radio is still the main medium for news and information. The few private radio stations that cover political events are subjected to editing and approval requirements by local government officials. Broadcasters who deviate from approved content have been harassed, detained, and in many cases forced into exile.
The government has also frequently jammed broadcasts and blocked the websites of foreign and diaspora-based radio and television stations. Staff working for broadcasters face repeated threats and harassment, as well as intimidation of their sources or people interviewed on international media outlets. Even people watching or listening to these services have been arrested.
The government has also used a variety of more subtle but effective administrative and regulatory restrictions such as hampering efforts to form journalist associations, delaying permits and renewals of private publications, putting pressure on the few printing presses and distributors, and linking employment in state media to ruling party membership.
Social media are also heavily restricted, and many blog sites and websites run by Ethiopians in the diaspora are blocked inside Ethiopia. In April, the authorities arrested six people from Zone 9, a blogging collective that provides commentary on social, political, and other events of interest to young Ethiopians, and charged them under the country’s counterterrorism law and criminal code. Their trial, along with other media figures, has been fraught with various due process concerns. On January 14, 2015, it was adjourned for the 16th time and they have now been jailed for over 260 days. The arrest and prosecution of the Zone 9 bloggershas had a wider chilling effect on freedom of expression in Ethiopia, especially among critically minded bloggers and online activists.
The increased media repression will clearly affect the media landscape for the May elections,.
“The government still has time to make significant reforms that would improve media freedoms before the May elections,” Lefkow said. “Amending oppressive laws and freeing jailed journalists do not require significant time or resources, but only the political will for reform.”

Friday, January 16, 2015

ኢህአዴግ የምርጫው ስጋቱ አይሏል

የአማራ ክልል ምርጫውን ተከትሎ አመጽ ይነሳል በሚል ኢህአዴግ “የደፈጣ ውጊያ ስምሪት” ስልጠና ለፖሊስ እየሰጠ መሆኑ ተሰማ
amhara region

* ፖሊሶች የደረጃ እድገት እንደሚደረግላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል
የአማራ ክልል መስተዳደር በግንቦት 2007 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ተከትሎ አመጽ ከተከሰተ ለመቆጣጠር ያስችላል ያለውን ስልጠና ለክልሉ ፖሊስ፣ ለማረሚያ ቤት ፖሊስ፣ ለሚሊሻና ለመከላከያ ሰራዊት አባላት እየሰጠ መሆኑን ሰልጣኞቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ስልጠናውም፤ ለፖሊሶች በዞን እንዲሁም ለሚሊሻና ለፀጥታ ጉዳይ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች እየተሰጠ መሆኑን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ በቀጣዩ ምርጫ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚፈራውን አመጽ መቆጣጠር እንደሆነ የገለጹት የፖሊስ ምንጮች በተለይ ፖሊስና ፀጥታ ጉዳይ ከ“ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ” ጋር በመተባበር የደፈጣ ውጊያን ለመከላከል “የደፈጣ ውጊያ ስምሪት” በሚል አጭር ስልጠና እየወሰዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም አገር ውስጥ አመጽ ያነሳል ተብሎ ከሚፈራው ህዝብ በተጨማሪ መሳሪያ ያነሱ ተቃዋሚዎች በምርጫው ወቅት ጦርነት ይከፍታሉ የሚል ስጋት በመኖሩ ነው ሲሉ ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡ በደብረማርቆስ ውስጥ ስልጠናውን የሚወስዱት ሰልጣኞች ማታ ማታ የተኩስ ልምምድ እንደሚያደርጉ አንድ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
amhara regionበሌላ በኩል ምርጫውን ተከትሎ ይከሰታል ከተባለው አመጽና ታጣቂ ቡድኖች ያደርሱታል ተብሎ ከሚፈራው ጥቃት በተጨማሪ የጥምቀት በዓል ላይ አመጽ እንዳይነሳ መከላከል፣ ከተነሳም መቆጠጠር የስልጠናው የአጭር ጊዜ ግብ ነው ተብሏል፡፡
በስልጠናው ወቅት በተለይ ፖሊሶች ‹‹ልዩ ኃይልና ፌደራል ፖሊስ በስራችን ጣልቃ ስለሚገቡ ነጻነት የለንም፣ ፖሊስ የህዝብ ነው እየተባለ ህዝብ ግን ይጠላናል፣ በህገ መንግስቱ መሰረት የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ ሲገባን እርምጃ እንድንወስድ ከበላይ አካል እንታዘዛለን፣ ከፖለቲካው ገለልተኛ አይደለንም›› የሚሉና ሌሎች ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችንም አንስተዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሶች በቂ ደመወዝና ዩኒፎርም አይቀርብልንም የሚል ቅሬታ እንዳቀረቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በስልጠናው ወቅትም በተለይ ፖሊሶች ጠንካራ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን መሰንዘራቸው ተከትሎ ሁሉም የክልሉ የፖሊስ አባላት አንድ የደረጃ እድገት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል ተብሏል፡፡ ጥር 12007 ዓ.ም የጀመረው የ‹‹ፀጥታ ኃይሎች›› ስልጠና ቅዳሜ ጥር 9/2007 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጥር 7 እስከ ጥር 11/2007 ዓ.ም ለሚሊሻዎች አመራሮች ተጨማሪ ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጾአል፡፡
በታህሳስ ወር የታቦት ማደሪያው ለባለሀብት መሰጠት የለበትም በሚል የባህርዳር ከተማ የክርስትና እምነት ተከታዮች አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማታቸው እንዲሁም በደብረማርቆስና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ስልጠና ላይ የነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስልጠናውን በመቃወም ሰልፍ መውጣታቸው በ“ፀጥታ ኃይሎች” ስልጠና ወቅት መወያያ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ሁለቱ ክስተቶች የአማራ ክልል አስተዳደር በዚህ አመት አመጽ ይነሳል የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሲዳማ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆነው አቶ አንተነህ አሰፋ “ማደራጀት ህገ ወጥ ነው፣ ፓርቲያችሁ ወጣቶችን እየመለመለ ወዳልሆነ አቅጣጫ እየወሰደ ነው” በሚል መታሰሩን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ደም መላሽ አበራ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ አንተነህ አሰፋ በትናንትናው ዕለት ከምሽሩ 12 አካባቢ በፖሊስ ተይዞ አዋሳ ከተማ ውስጥ ሀይቅ ዳር ፖሊስ ጣቢያ የታሰረ ሲሆን “ሰማያዊ ፓርቲ የሚሰራው ስራ ህገ ወጥ ነው፡፡ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ነውጥ ለማምራት እየጣረ ነው፡፡ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ከሚያደርገው ሰማያዊ ፓርቲ መውጣት አለብህ” የሚል ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሆነ ተገልጾአል፡፡
ፖሊስ የሌሎቹን የፓርቲው የሲዳማ ዞን አመራሮች ቤትም እያፈላለገ እንደሆነ የገለጹት ሰብሳቢው ፖሊስና ደህንነቶች አመራሮቹንና አባላትን በማዋከብና በማሰር በህጋዊ መንገድ የሚደርጉትን የማረዳጀት ስራ ለማስቆም ከዚህም አልፎ ከሰላማዊ ትግሉ እንዲያፈነግጡ ጥረት እያደረገ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የፖሊስ ወከባና እስር በህጋዊ መንገድ እያከናወኑ ያለው የፓርቲያቸው ስራ እንደማያደናቅፋቸውና ደህንነትና ፖሊሶቹ እንደሚያስቡት ከሰላማዊ ትግሉ እንደማያፈገፍጉ አቶ ደም መላሽ አክለው ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ ፌስቡክ ገጽ)

Thursday, January 15, 2015

ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በኢቦላ በሽታ ስጋት ተወጥራለች



• ከ10 በላይ ሰዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ በፖሊስ ታግተዋል
ሴራሊዮን ውስጥ በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቶ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ህይወቱ ያለፈውና በሽታው ኢቦላ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የደም ናሙናው ወደ ውጭ ለምርመራ የተላከው ኢትዮጵያው ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የአምቡላንስ ሰራተኛና ከእሱ ጋር ተገናኝተዋል የተባሉ ሌሎች 10 ያህል ሰዎች የሚኖሩበት ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ የሚገኝ ግቢ በፖሊስ ተከቦ ነዋሪዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ተደርገዋል፡፡
ኢሳያስ የተባለና ህይወቱ ያለፈውን ኢትዮጵያዊ በአምቡላንስ ሲያመላልስ የነበር ወጣት ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በተለምዶ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከራይቶ የሚኖር ሲሆን እሱን ጨምሮ ከእሱ ጋር የሚኖሩት እህቱና ባለቤቱ እንዲሁም ተከራይቶ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ከ10 በላይ ሰዎች ከህዝብ እንዳይገናኙ በፖሊስ ታግተዋል፡፡ ግቢው በፖሊስ ተከቦ ሰው ከግቢው እንዳይወጣና ወደ ግቢው እንዳይገባ መከልከሉን ተከትሎ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በኢቦላ በሽታ ስጋት ተወጥሯል፡፡
የጤና ባለሙያዎችና ፖሊሶች ኢሳያስ የተባለው ግለሰብ ሟቹን በአምቡላንስ ሲያመላልስ እንደነበር ከትናንት ጠዋት ጀምረው ቢያረጋግጡም እስከ ትናንት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ ከሰው ጋር እንዳይገናኝ ሳይከለክሉት ቆይተዋል ተብሏል፡፡ የአምቡላንስ ሾፌሩ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ ከ20 በላይ ሰዎች የሚኖሩ ቢሆንም 10 ያህሉ ግለሰቦች ብቻ ከግቢ እንዳይወጡ የተከለከሉት ዛሬ ጠዋት ነው ተብሏል፡፡ ሆኖም ከግቢው ውጭ ከኢሳያስ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች ላይ ምንም አይነት ክትትል ያልተደረገ ሲሆን ግቢው ውስጥ ከሚኖሩት መካከልም በጠዋት በስራና በሌሎች ምክንያች የወጡ ግለሰቦችም ተመልሰው ወደ ግቢ እንዳይገቡ ከመከልከላቸው ውጭ ክትትል እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ታውቋል፡፡
የአምቡላንስ ሾፌሩና ከእሱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉበት ግለሰቦች የሚኖሩበት ግቢ በርከት ባሉ ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች መከበቡን ተከትሎ ስጋት የገባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰባስበው ስለ በሽታው እየተወያዩ አስተውለናል፡፡ ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም የአንቡላንስ ሾፌሩ ከበርካታ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበረው መሆኑ፣ እንዲሁም ግቢው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ከግቢ ውጭ የሚገኙ በመሆኑ በሽታው ከተከሰተ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም አስጊ እንደሆነ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በፖሊስና ደህንነት ከበባ ብቻ አንድ ግቢ ውስጥ ተከሰተ የተባለውን ጉዳይ በአግባቡ መያዝ አለመቻሉን ጠቅሰውም ‹‹መንግስት ዝግጅት ሳያደርግ ዜጎችን መላኩ ትክክል አልነበረም፡፡›› ሲሉ ተችተዋል፡፡
በፖሊስ ከታገቱት መካከል በስልክ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሰዎች ደህንነቶች ‹‹ይህ የአገር ሚስጥር በመሆኑ ለማንም እንዳትናገሩ፡፡›› እብለው እንዳስጠነቀቋቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስና ደህንነቶች ሰው እንዳይወጣና እንዳይገባ በመከልከላቸው እስካሁን ምግብ እንዳልገባላቸውና ‹‹የሟቹ የደም ናሙና ነገ እስኪመጣ ድረስ ከግቢ መውጣት አትችሉም፡፡ ሌሎች ሰዎችም ወደ ግቢ መግባት አይችሉም፡፡ እስከነገ ለማንም መረጃ ባለመስጠት ተባበሩን፡፡›› እንደተባሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ግቢውን በከበበት ወቅት የግቢው ነዋሪዎች ‹‹ችግር ካለ ባለሙያ መጥቶ ያረጋግጥ፡፡ ፖሊስ ለምን ያግተናል?›› በሚል ከግቢው እንወጣለን በማለታቸው ጭቅጭቅ ተፈጥሮ እንደነበርም የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

Tuesday, January 13, 2015

በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣ ዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ መሀል የተደረገውን ውህደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣

በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣ ዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ መሀል የተደረገውን ውህደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በዛሬው ዕለት፣ ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ ለዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ፣ ድርጅቶች፣ ተዋህደን “አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ”፣ በሚባል ሥም መጠራት መጀመራችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስናበስር፣ እጅግ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ባለፉት በርካታ አስርተ አመታት፣ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነጻነት፣ መብትና አንድነት፣ ከፍተኛ ትግል ሲያካሂድ ቆይቷል። በአደረገውም ትግል እጅግ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍሏል። ለከፈለው ከፍተኛ ዋጋ የሚመጥን ግን ምንም ዓይነት ውጤት አላገኘም። እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የመብት ረገጣው፣ አድሎው፣ ማስፈራራቱና ማዋከቡ ተጠናክረው መቀጠል ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልትቀጥል የማያስችል ከፍተኛ የመበታተን አደጋ አንጃቦባት ትገኛለች ።
በሀገራችን ላይ ላንጃበበው ከፍተኛ የመበታተን አደጋ ምክንያት የሆነው በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ የአምባገነን ቡድን ነው። ይህ ዘረኛ አምባገነን ቡድን በሀገራችን ታሪክ በሥልጣን ላይ ከመጡ የገዥ ሃይሎች ጋር ሲወዳደር ሀገርን ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ፣ ሕዝቧን በማወረድ፣ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ዕኩይ ሃይል መሆኑን በበርካታ ተግባራቶቹ ያለ ምንም ጥርጣሬ አረጋግጧል።
በሌላ በኩል ለቀድሞቹም ሆነ ለዛሬው ዘረኛው የወያኔ አምባገነን ገዥ በሕዝብና በሀገር ላይ በደል እየፈጸመ በሥልጣን መቆየት የቻለበት ምክንያት፣ በተቃዋሚነት የሕዝቡን ትግል ለመምራት የተንቀሳቀስን ድርጅቶች፣ የተቋቋምንበት ዓላማ መለያዬት ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ዓይነት ዓላማ ያለንም ብንሆን፣ ከድርጅቶቻችን ጠባብ ፍላጎቶችና ስሜቶች ባለፈ፣ የሀገርና የሕዝብን ጉዳይ በማስቀደም በጋራ መሰባሰብና መታገል ስላቃተን ነው። በዚህም ድርጊታችን የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የወገናችንንም የመከራ ዘመን እያራዘምን እንገኛለን ።
ይህ ሁኔታ በተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶች መሀል ከፍተኛ ጥርጣሬና ፍርሀት ከመፍጠሩ የተነሳ በምንም ዓይነት ሁኔታ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች በጋራ በሀገርና በሕዝብ ደረጃ ትርጉም ያለው ስራ መስራት አይችሉም፣ የሚለው አመለካከት የበላይነት እንዲያገኝ አድርጎታል።
በዛሬው ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ ውህደት የመጣነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣፡ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ መዋሃድ መወሰናችንን ፣ ስንገልጽ በተናጠል ከሚደረጉ በጋራ የሚደረጉ የትግል ጥረቶች ውጤታማ ይሆናሉ በሚል ብቻ ሳይሆን፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ በሀገርና በሕዝብ ደረጃ ትርጉም ያለው ሥራ በጋራ መስራት አይቻሉም የሚለውን፣ አስከፊ ተመክሮና አመለካካት ለመስበርም ነው።
በእኛ እምነት ከትናናሽ ድርጅቶች ዙሪያ ከሚሽከረከሩ ሀሳቦችና ስሜቶች ለመውጣትና ሀገራዊና ሕዝባዊ የሆነው ጉዳይ ለማስቀደም የወሰነ ማንኛውም ድርጅት፣ አርበኞችና ግንቦት7፣ የደረሱበት የውህደት ውሳኔ ወይም በሌሎች በጋራ ሊያሰሩ በሚችሉ ስምምነቶች አብሮ ለመስራት መወሰን የማይችልበት ምንም ምክንያት አይታየንም። በወያኔ አድሎ ስርዓት የተንገፈገፈና ትግሉን ለመቀላቀል የቆረጠ ማንኛውም ዜጋ፣ የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ትግሉን መቀላቀል ይችላል፣ የኢትዮያ ሕዝብ በአንድነት የተነሳ ቀን ደግሞ፣ የወያኔ ግብዓተ መሬት ይፈጸማል፣ ብለን ከልብ እናምናለን።
ይህም በመሆኑ፣
ለተቃዋሚ ድርጅቶች፣
ዛሬ በአርበኞችና በግንቦት 7፣ የተጀመረው ጉዞ ውጤታማ በመሆን ሀገራዊና ታሪካዊ ትርጉም እንዲኖረው፣ ሌሎችም በተግባር የምትንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ወያኔን የማስወገድንና ብሎም ሀገር የማረጋጋቱን ሀላፊነት በጋራ እንድንወጣ የሚያስችል መቀራረብ እንድናደርግ ፣ በውህደት በመሰረትነው፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ለወታደራዊና የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣
የወያኔ ዘረኛና አምባገነን ቡድን ዕድሜን ለማሳጠርና ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ሀገር እንድትኖር ፣ በየቦታው የሚደረገውን ትግል፣ የሰሞኑን ቆራጥ የዓየር ሃይል መኮንንኖች ያሳዩትን ዓርያነት በመከተልና በተገኘው አጋጣሚና ሁኔታ በመጠቀም፣ እንድትቀላቀሉ በውህደቱ ድርጅት፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣
በረጅም ታሪክህ አይተሄው ለማታውቀው፣ ውርደት፣ ክፋት፣ የመከፋፈልና የመጋጨት አደጋ፣ የመብት እረገጣና አፈና፣ ሀገርና ሕዝብን የማራከስና የመሸጥ፣ ዕኩይ ተግባር፣ የተጠናወተው ወያኔ እና የግብር አበሮቹን፣ ጠራርጎ ለማስወገድ በተጀመረው የጋራ ትግል ውስጥ በቀጥታ እንድትሳተፍም ሆነ በምትችለው ሁሉ እርዳታ እንድታደርግ፣ በዛሬው ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም የአርበኞችና የግንቦት 7 ውህደት በወለደው፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣
ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ምርጫ መቆመሪያ ተቋም ገመና

በዳንኤል ተፈራ
ያሳለፍነው ሳምንት በሕወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ተሰልተው፣ ታስቦባቸው ይፋ ከተደረጉና አሻንጉሊቱ ምርጫ ቦርድ እንዲፈጽመው በህወሃት ሰዎች ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጥቶት ገቢራዊ እንዳደረገው የሚጠረጠረው የፖለቲካ ጉዳይ ይፋ የተደረገበት ነበር፡፡ ይሄው ጉዳይ በአይረቤ ሰበብና በምክንያት አልባ ሁነት ግን ዳግም ከቤተ-መንግስት በወጣ ትዕዛዝ በሚመሰል መልኩ አንድነት እና መኢአድ ወደ ምርጫ ፍክክሩ እንዳይገቡ አይን ያወጣና የሰዎችን የስልጣን ብልግና ባጋለጠ መልኩ መግለጫ የሰጡበት ነው፡፡
እንደዚህ ዓመቱ ምርጫ ቦርዱ የተጋለጠበት ጊዜ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ይሄው የምርጫ መቆመሪያ ተቋም እንደ ጫጩት ፍፁም ጠቅላላ ጉባዔ አድርገው የሚያውቁ፣ ቢሮም ሆነ ስራ አስፈፃሚ የሌላቸውን ተቃዋሚ ተብዬዎች በጉያው ሸጉጦ በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ እያላገጠ መሆኑ ሳያንስ የገዥውን ፓርቲ ኃላፊነት የጐደለው ተግባር ተቋቁመው ለሃገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እየደከሙ ያሉ ፓርቲዎችን እየገፉ ያለበት አግባብ ተቋሙን ከምርጫ መቆመሪያ ማዕከልነት ባለፈ ፋይዳ የሌለው፣ በህወሃት/ኢህአዴግ ማንቁርቱ የታነቀና የራሱ ሳንባ የሌለው ምስኪን ተቋም እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
ይሄው የተጨመደደ ቦርድ ተብየ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ገለልተኛነቱ አጠራጣሪ ቢሆንም እንደ ሰሞኑ ገለልተኛ አለመሆኑን በይፋ ያረጋገጠበት ወቅት ያለ አይመስለኝም፡፡ የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ቦርዱ በዋናነት የሚመራው በፕ/ር መርጋ በቃና ሳይሆን በምክትልነት በተቀመጠው የትግራዩ ሰው ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር ነው፡፡ ለዚህም ነው በኢህአዴጉ አፈ-ቀላጤ ፍና እና ሌላው ቀላጤ ኢቲቪ በኩል ፓርቲዎችን በህገ ወጥ መንገድ መገፋታቸውን እየገለፀ ያለው፡፡ ሰውየው የቦርዱን ህገ ወጥ ተግባር ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚችል ሰው ነው፡፡ ዶ/ር አዲሱ የፓርቲዎችን የፋይናንስ ክፍፍል ቀመር አዘጋጅቶ ያቀረበ፤ በዚህ ቀመርም በፓርላማ መቀመጫና በክልል ም/ቤት መቀመጫ 55% እንዲይዝ ለማሳመን የጣረ የህወሃት የቁርጥ ቀን ልጅ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም 55% ጠቅልሎ የሚወሰደው ኢህአዴግ ነው፡፡
ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም ስንል እንዲሁ በግብታዊነት ሳይሆን ተጨባጭ መከራከሪያዎችን የማቅረብ አቅም ስላለን ነው፡፡ አንድ ወዳጄ የኢትዮጵያውን ምርጫ ቦርድ በማገዝ ከመቆሪያ ተቋምነት መገላገል እንደሚገባ ስነግረው ተስፉ በቆረጠ ስሜት ግን ደግሞ በምፀት ፈገግ ብሎ “ወዳጄ ቦርዱ እኮ ግንባሩን ከመሰረቱ ፓርቲዎች አምስተኛው ፓርቲ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ቦርዱን ማገዝ ሳይሆን አፍርሶ እንደገና መስራት ነው፡፡ በታሪክ ከሚጠየቁ ተቋማት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡” ነበር ያለኝ፡፡ እውነትም መፍረስ የሚገባው አይረቤ ተቋም ነው፤ ራሱን ነፃ ያላወጣና የምርጫ መቆመሪያ ተቋም እንደሆነ ግብሩ አረጋገጠ፡፡
አንድነት ፓርቲ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ አንድነት በመዋቅሩ በአመራርነት የማያውቃቸው ግለሰቦች ተሰባስበው ኢ/ር ግዛቸውን የተካውን አመራር ህግ የጣሰ ለማስመሰል ጥረት ጀመሩ፡፡ የቦርዱ የፖለቲካ ቁማርም ከዚህ ሁነት ይጀምራል፡፡ አንድነትን አስቀድሞ ከምርጫው ለማስቀረት እነዚህን ተራ ግለሰቦች “ጐሽ፣ ጐሽ” ማለት ጀመሩ፡፡ እነዚህ “አንድነት ነን፣ መርህ ይከበር” የሚሉ ጥቂት ግለሰቦች የተንኮል ፖለቲካው አድራሽ ፈርሶች እንጅ በራሳቸው ምንም አይደሉም፡፡ የእነዚህ አፍራሽ ግለሰቦች ያላቸው ብቃት የሚለካው ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባፈነገጠ መልኩ ለመዋሸት የማይሳቀቁ፤ ተልዕኳቸውን ለመፈፀም አይናቸውን በጨው ያጠቡ የዘመናችን ባንዳዎች መሆናቸው ነው፡፡
ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው የመቆመሪያው ተቋም ሳያፍር “አመራር” እያለ የሚጠራው የማነአብ አሰፋ የሚባል የትግራይ ተወላጅ ሲሆን ዕድሜው በሃያዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ፣ በተግባሩ ስለሚያፍር በቆብና በጃኬት ራሱን ደብቆ የሚዞር ወጣት ነው፡፡ ይሄ ልጅ አንድነት ቤት ተቀጣሪ ሆኖ ለተወሰኑ ወራት የድርጅት ጉዳይ ተላላኪ ሆኖ ሰርቷል፡፡ አንገት ደፊና አይናፋር በመምሰል የተወነው ትወና አስደናቂ ነው፡፡ የኢህአዴግ ክትትል እንዳላስቀመጠውና ስራ መቀጠር እንኳን እንዳልቻለ እንባ እየተናነቀው ለመናገር የሚችለው ይሄ ወጣት ምርጫ ሲደርስ እንዲፈነዳ ህወሃት አቀባብሎ ያስቀመጠው ፈንጂ እንደሆነ ያወቅነው ቦርዱ “አመራር” እያለ ቢሮው ጐልቶት ስናገኘው ነው፡፡ ወደ ነጥቡ ስንመለስ እነዚህ “አንድነት ነን” የሚሉ በተግባር ግን የአንድነት ወገን ያልሆኑ ስብስቦች ም/ቤቱ በደንቡ መሰረት የተካውን አመራር “ህገ-ወጥ ነው” በማለታቸው ብቻ የምርጫ መቆመሪያው ተቋም በችኮላ አንድ ደብዳቤ ለፓርቲው ፃፈ፡፡ ይሄ የመጀመሪያው ደብዳቤ ኢ/ር ግዛቸውን ፕሬዝዳንት አድርጐ የመረጠውን ጉባኤ ዕውቅና በመንፈግ ዶ/ር ነጋሶን እንደሚያውቅ የሚጠቅስ ነው፡፡ ቦርዱ በችኮላ በየዋህነት የፃፈው ደብዳቤ ለቁማሩ በጆከርነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግበት መሆኑን ሲረዳ ምናልባትም አለቃቸው ህወሃት /ኢህአዴግ ለአንድነት ቦርድ የፃፈውን ዝርዝር ደብዳቤ ሲመለከት ለሴራ ፖለቲካ እንደማይመች ሲረዳ በአስቸኳይ ቀይር ብሎት ይመስለኛል፡- “እሱን ደብዳቤ ተውት” ከሚል መልዕክት ጋር ሌላ 3 ነጥቦችን የያዘ ደብዳቤ ላከ፡፡
የመጀመሪያውን ደብዳቤ ተውት ያለበት ምክንያት ለአፍራሽ ተልዕኮ የተዘጋጁ ገልቱ ግለሰቦች ከጨዋታ ውጭ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ግለሰቦች በዶ/ር ነጋሶ የአመራር ዘመን አይታወቁም ወይም የሉም ነበርና፡፡ ባለ ሦስቱ ነጥብ ደብዳቤ ሲመጣ ግን አንድነት የፖለቲካ ዕደንድምታውን በጥንቃቄ ገምግሟል፡፡ ምነው ቢሉ ይሄ ከቦርዱ በስተጀርባ የሚደንስ አካል እንዳለ በመረጋገጡ ነው፡፡ ዳንሰኞቹ ምርጫን ለማስመሰያና ማወናበጃ እንጅ በትክክል ሊጠቀሙበት አይፈልጉም፡፡
የደብዳቤው ሦስት ነጥቦች የሚከተሉት ነበሩ አንደኛው ም/ቤቱ የጠቅላላ ጉባኤ ውክልና እንዳለውና ም/ቤቱ ፕሬዘዳንት መምረጥ እንደሚችል አብራሩ፤ ሁለተኛው የጠ/ጉባኤ ሪፖርት በጊዜ አስገቡና የመጨረሻው የጠቅላላ ጉባኤ የኮረም ቁጥር ግለጹልን የሚል ነበር፡፡ በጣም ቀላልና ተራ ጥያቄ የሚመስል ነበር፡፡ አንድነት በፍጥነት ምላሽ ሰጠ፡፡ የመቆመሪያው ተቋምም የሰጠነውን ምላሽ “በቅንነት” እንደተቀበለው ገልጾ ነገር ግን የጠ/ጉባኤ ቁጥር በደንቡ እንድናካትት የሚጠይቅ ደብዳቤ ፃፈ፡፡ በቅንነት የምትለውን ግን በቅንነት አልተመለከትነውም፡፡ ጉባኤ በፍጥነት መጠራት እንዳለበትና ምርጫ ቦርዱ የጠየቀውን አሟልተን በሙሉ ልብ ወደ ምርጫ መግባት እንደሚገባ በመታመኑ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ የምርጫ ቦርድ ተወካይ ባለበት በስኬት ተጠናቀቀ፡፡
አንድነትም ገዥዎች ባዳፈኑት የፖለቲካ ምህዳር እና ልፍስፍሱ ቦርድ ቢኖርም ህዝቡን አንቀሳቅሽ በ2007 ዓ.ም የአምባገነኑ ስርዓት ፍፃሜ ይሆናል በሚል ፅኑ እምነት ሙሉ ለሙሉ በስራ ተጠመደ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም የህዝብ ታዛቢዎችን ምርጫ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ቢሮዎቹን በመዝጋት በንቃት ተከታተለ አጋለጠ፡፡ ህዝቡ የምርጫ ካርድ የሚወስድበትንና በካርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ የሚሆንበትን ስትራቴጂ መንደፍንና ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ ይፋ ማድረጉ ተከትሎ የ40 እና 50 ዓመት የመግዛት ህልም ያላቸው “ነፃ አውጭዎች” መንደር ጫጫታና ጭንቀት ፈጠረ፡፡
ይህንን ጭንቀት ለማርገብ አንድነትን ከምርጫ ጫወታ ማስወጣት እንደሚገባ ታመነበት፡፡ ለዚህ ማስፈፀሚያ የመቆመሪያው ተቋም አለ፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው ተወካዩን የላከው ቦርዱ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ለመስራት ደፈረ፡፡ ከቦርዱ በስተጀርባ ያሉ ዳንሰኞች ማንቁርቱን ስላነቁት ምርጫ አልነበረውም፡፡ ይሄ ተራ ጨዋታ በፋና እና ኢቲቪ ታጅቦ ለህዝብ ቀረ፡፡ ድራማው “የውስጥ ችግሮቻቸውን ካልፈቱ ወደ ምርጫ አይገቡም” የሚል ነው፡፡ የውስጥ ችግር ከማን ጋር? እንዴት? መልስ የላቸውም፡፡ ኢ/ር ግዛቸው በፈቃዳቸው ለቀው ወደ ግል ጉዳያቸው ገብተዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ አመራር ተብየዎች እነማን ናቸው? እነዚህ የአንድነት አመራር እንዲደራደራቸውና ችግሩን እንዲፈታ የተጠየቁት ግለሰቦች በፓርቲው የአመራር መዋቅር የማይታወቁ፤ ከየመንገዱ ተለቃቅመው የመጡ ተራ ሰዎች ናቸው፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ በቦርዱ በኩል ይህንን ተራ ድራማ እየሰራ ያለው አንድነት ወደ ምርጫ እንዳይገባ ለመከልከል የወሰነው የፖለቲካ ውሳኔ ስጋ ለማልበስ ነው፡፡ የእርኩም ስጋ፡፡ ሁሉም በሰፈረው ቁና የሚሰፈርበት ቀን እንደሚመጣ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ትግል ከዚህ ዓይነት ተራ ድራማ በላይም ነው፡፡ ትግሉ የነፃነት የመውጣትና ተደፍቆ የመኖር ነው፡፡ ወደ ምርጫ እንገባለን ስንላቸው በዚህ ደረጃ ተርበትብተዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም ያለውድድር ለኢህአዴግ ተጨማሪ የአገዛዝ ዘመን ለመስጠት ዝግጅቱን የጨረሰ ይመስላል፡፡ ይሄ የስርዓቱን የውድቀት ፖለቲካ የሚያሳይ ነው፡፡ የዚች ሀገር ትግል የቦርድ ወይም የሌላ ትግል አይደለም፡፡ ትግሉ በሕዝቡ እጅ ላይ የወደቀበት ታሪካዊ ወቅት ነው፡፡ ታሪካዊ ጊዜ ዴሞክራሲን እናሰፍናለን የሚሉ ሰዎች በግብራቸው ያፈሩበት ታሪክ፡፡ ይህንን በአደባባይ ቆመን የምንናገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ 2007 ለለውጥ!!!

ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ውሳኔ አስተላለፈ

• ለሰማያዊ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የውስጥ ችግራቸውን መፍታት አልቻሉም በሚል በዛሬው ዕለት ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ የነበረው ምርጫ ቦርድ ሁለቱ ፓርቲዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ የውስጥ ችግራቸውን ፈትተው ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ገልጾአል፡፡ ቦርዱ ዛሬ ከሰዓት በሰጠው መግለጫ በአንድነትና መኢአድ ስም የተለያዩ ጉባኤዎች በመደረጋቸው ሁለቱ ፓርቲዎች ጥር 3 ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አለመገኘቱን፣ አንድነት የ2004 ዓ.ም እንዲሁም የመኢአድን የ2001 ዓ.ም ደንብን እንጅ ከዛ በኋላ ያሉትን የፓርቲውን ደንቦች እንደማያውቅ በመግለጽ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ችግራቸውን እንዲፈቱ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል መድረክ ረግጦ በመውጣት፣ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያድሙ በማድረግ፣ ቦርዱ የማያውቀው ትብብር በመመስረት በሚል በምርጫ ቦርድ ክስ የቀረበበትና ይቅርታ እንደማይጠይቅ በደብዳቤ ለገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውን የማያከብር ከሆነም ቦርዱ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡
የቦርዱ ባለስልጣናት ‹‹ሰማያዊ ፓርቲን ህገ ወጥ ትብብር በመመስረት ስትከሱ ሌሎቹን የትብብሩን አባል ፓርቲዎች ለምን አልከሰሳችሁም?›› በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ፓርቲዎቹ 9 መሆናቸውን የሰማሁት አሁን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹እስካሁን ሌሎች ትብብሮችን ምርጫ ቦርድ አያውቃቸውም ብላችሁ ከሳችሁ አታውቁም›› በሚል የ9ኙን ፓርቲዎች ትብብር ህገ ወጥ ነው ካሉ ገዠው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነትን ለምን ህገ ወጥ ነው እንደማይሉ ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ አጋር ፓርቲዎች ሊኖሩት ይቻላል፡፡ እንደ ገዥ ፓርቲ ከአጋሮች ጋር መስራት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮችን ቦርዱ አይመለከተውም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡
አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን እንዲፈቱ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቻለሁ ያለው ምርጫ ቦርድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን ካልፈቱ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔውን ያሳውቃል ብሏል፡፡